ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘ጥይት መከላከያ’ አስማት የተሞከረበት ናይጄሪያዊ ታዳጊ ሕይወቱ አለፈ
ናይጄሪያ ውስጥ አንድ ግለሰብ የገዛውን ባህላዊ ‘የጥይት መከላከያ’ ወንድሙ ላይ ከሞከረ በኋላ የታዳጊው ሕይወት ማለፉን ፖሊስ ገለጸ።
የካዋራ ግዛት ፖሊስ እንደገለጸው ሁለቱ ወንድማማቾች በገዙት ባህላዊ ‘ጥይት መከላከያ’ ራሳቸውን በአስማት ከጥይት መከላከል እንደሚችሉ ያምኑ ነበር ብሏል።
በዚህም አቡበከር የተባለው ታላቅ ወንድም የሱፍ የሚባለውን ዕድሜው 12 የሆነውን ታናሽ ወንድሙን በአባታቸውን ጠመንጃ እንደገደለው ተገልጿል።
ፖሊስ ወንደሙን ገድሏል የተባለውን ተጠርጣሪ አያፈላለገ ይገኛል።
በናይጄሪያ ምንም አይነት ማረጋገጫ ሳይኖር በርካታ ሰዎች አንገት ላይ የሚንጠለጠል ‘አስማት’ በማድረግ ራሳቸውን ከመጥፎ ዕድል እንደሚጠበቁ ያምናሉ።
“የጥይት መከላከያ” ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ጌጥ መሰል ነገሮቸን እና መድኃኒቶችን በሚሞከሩበት ወቅት በርካታ ናይጄሪያውን ሕይወታቸን እንደሚያጡ በተደጋጋሚ ይዘገባል።
ሁለቱ ወንድማማቾች የጥይት መከላከያ የፈለጉበት ምክንያት እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የሱፍ የተባለው ታዳጊ የ“ጥይት መከላከያው” እንደተሞከረበት ወዲያው ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን ታላቅ ወንድሙ አካባቢውን ለቆ መሸሹን ፖሊስ አሳውቋል።
የሁለቱ ወንድማማቾች አባት አዳኝ እንደሆነም ተዘግቧል።
ፖሊስ ወላጆች የልጃቸውን እንቅስቃሴ እንዲከታተሉ ከእንዲህ አይነት ካለተረጋገጠ አጉል እምንት እንዲታቀቡም መክሯል።