ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያው ፕሬዝዳንት በግል ጄት ወደ አሜሪካ መጓዝ ‘ርካሽ ነው’ ማለታቸው አስተቻቸው
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ወደ አሜሪካ የተጓዙበት የግል የኪራይ ጄት ወጪ በአገሪቱ አየር መንገድ አውሮፕላን ከመጓዝ አንጻር ዋጋው እንደሚያንስ መናገራቸው እያስተቻቸው ነው።
በግል የኪራይ ጄት መጓዝ ወጪው ይቀንሳል ማለታቸው ትችት ቢያሰነዝርባቸውም፣ ለጉዟቸው ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጡ ወይም በኬንያ አየር መንገድ ቢጓዙ ኖሮ ምን ያህል ሊያወጡ እንደሚችሉ በይፋ አልተናገሩም።
ጉዳዩን በተመለከተ የፖለቲካ ተንታኙ ሔርማን ማንዮራ “ሕዝብ የሚያውቀው እውነታ ያሳሰባቸው አይመስልም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ዩጂን ዋማላዋ የፕሬዝዳንቱ ንግግር “የአገር ፍቅር የጎደለው” ነው በማለት፣ ፕሬዝዳነቱ ቢዘህ አጋጣሚ የኬንያ አየር መንገድን ማስተዋወቅ ይችሉ ነበር ሲሉ ተችተዋል።
ለሦስት ቀናት ወደ አሜሪካ ለይፋዊ ጉብኝት የሄዱት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በ15 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ የሥራ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ ደማቅ መንግሥታዊ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ ቆይታቸው በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠሩ ኢንቨስትመንቶችን ለኬንያ አስገኝተዋል።
ኬንያ የሰሜን አትላንቲን ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ያለሆነች አጋር የሚል ማዕረግም ከአሜሪካ አግኝታለች።
ሆኖም ግን ፕሬዝዳንቱ ቅንጡ የኪራይ ጄት መጠቀማቸው እያስተቻቸው ነው።
ከጉዟቸው ከተመለሱ በኋላ “የሕዝብ ንብረት ጠባቂ ነኝ” ሲሉ ራሳቸውን ተከላክለዋል።
“በአቅማችን እንድንኖር ለማድረግ ቁርጠኛ ነኝ። ያንን ለማድረግም በኬንያ አየር መንገድ ከመጓዝ ይረክሳል” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የኬንያ አየር መንገድ ፕሬዝዳንቱ ያሉትን በተመለከተ አስተያየት አልሰጠም።
አየር መንገዱን መጠቀም ዋጋው ይቀንሳል በሚል በስፋት እየተሰራጨ ያለውን ሐሰተኛ መረጃ ግን አስተባብሏል።
ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ሩቶ እንዴት የግል ጀት ዋጋው እንደሚረክስ ለሕዝቡ የተሻለ ማብራሪያ መስጠት ነበረባቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሰዎችን “ዕይታ ከግምት ውስጥ ማስገባት ነበረባቸው” ሲሉም አክለዋል።
በሌላ አገር የሚተዳደር አውሮፕላን መጠቀማቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይም አነጋጋሪ ሆኗል።
“ብሔራዊ አየር መንገዳችንን ፕሬዝዳንታችን አለመጠቀማቸው ያሳፍራል” ሲል አልኑር መሐመድ የተባለ ኬንያዊ ቁጣውን ገልጿል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን፣ ለፕሬዝዳንቱ ሠራተኞቻቸው የወጣውን የግል የኪራይ ጄት ወጪን በማስላት የኬንያ አየር መንገድን መጠቀም ዋጋው እንደሚቀንስ ዘግበዋል።
ፕሬዝዳንቱ የተጓዙት በዱባዩ ሮያልጄት ነው። አብረዋቸው 30 ሰዎች ተጉዘዋል።
ይህ ጀት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣል። በኬንያ አየር መንገድ ቢዝነስ ክፍል ለመጓዝ የሚያስፈልገው 300,000 ዶላር ነው።
ሩቶ ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ ምልልስ ለጉዟቸው ወጥቷል የተባለው ገንዘብ “የተጋነነ ነው” ሲሉ አስተባብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጡ ሲጠየቁ በቀጥታ ባይመልሱም “ስለማወጣው ወጪ ጠንቃቃ ነኝ” ሲሉ መልሰዋል።
የመንግሥት ቃል አቀባይ አይዛክ ማዋውራ ለቢቢሲ “የጉዞው ዓላማ የበለጠ ዋጋ አለው” ሲሉ ከወጪው በላይ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል።
በኬንያ መሠረታዊ መገልገያዎች ላይ የተጣለው ግብር ከፍተኛ ሆኖ ለባለሥልጣናት ቅንጡ ኑሮ እየዋለ ነው የሚል ትችት ሲሰነዘር ቆይቷል።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ወደተለያዩ አገራት 50 ጉብኝት አድርገዋል። ይህም በሦስት ወር አንዴ ይጓዛሉ ማለት ነው።
መንግሥት እነዚህ ጉዞዎች አስፈላጊ እንደሆኑ እና ወጪ ለመቀነስ ውሳኔ እንደተላለፈ ገልጿል።