የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ጾታ እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ ጣለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ዓለም አቀፍ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የአደባባይ እንቅስቃሴ” ጽንፈኛ ድርጅት ነው በማለት እንቅስቃሴዎቹ የተከለከሉ ናቸው ሲል አወጀ።
በሩሲያ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እውቅና የለውም። በሩሲያ ትዳር ማለት የወንድ እና የሴት ጥምረት ማለት ስለመሆኑ ትርጉም ለመስጠት የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከሦስት ዓመታት በፊት ተቀይሮ ነበር።
ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በይፋ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የተመለከቱ እንቅስቃሴዎችን የሚከለክል ሲሆን፣ ሕጉን የሚተላለፍ በእስር ይቀጣል።
ውሳኔው በአገሪቱ የሚገኙ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን እና ደጋፊዎቻቸውን አላስደሰተም።
ባለፈው ዓመት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ መሆኑን በይፋ የገለጸው የሴንት ፒተርስበርግ ምክትል ከንቲባ ሰርጌይ ትሮሺን ውሳኔው በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪን ማኅብረሰብ ውስጥ የእስር ስጋት መፍጠሩን እና ሩሲያን ጥለው የሚወጡ ዜጎች መበራከታቸውን ተናግሯል።
“ይህ ማለት መንግሥት የተመሳሳይ ጾታ አቀንቃኝ ነው ብሎ የሚያስበውን ማንኛውም ሰው ረዥም የእስር ጊዜ ሊጠብቀው ይችላል። ይህ ጭቆና ነው። ትልቅ መደናገጥ አለ። ሰዎች በፍጥነት ከአገር እየወጡ ነው። ...ከራሳችን አገር ለመሰደድ እየተገደድን ነው” በማለት ሐዘኑን እና ስጋቱን ገልጿል።
እራሱን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ማኅብረሰብ አካል አድርጎ የሚቆጥረው ማክሲም ጎልድማን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ከሩሲያ ወጥቷል።
“በራሴ አገር እንደተገፋሁ ይሰማኛል። ...ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳለን ነው የምናስበው። ሥልጣን ላይ የምናወጣቸው ሰዎች ሊጠብቁን ይገባቸዋል። ይሁን እንጂ በተቃራኒው ነው እየሆነ ያለው። እየቀጡን ነው። ...በኃይል ከአገር እያስወጡን ነው” ብሏል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሩሲያ መንግሥት በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን እና በእንቅስቃሴያቸው ላይ ጠንከር ያለ እርምጃን እየወሰደ ይገኛል።
እአአ በ2013 ላይ “ከተለመደው ውጪ ስላለ ጾታዊ ግንኙነት የሚደረግ ፕሮፖጋንዳን” የሚከለክል ሕግ ወጥቶ ነበር።
የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያንን የሚያመለክቱ ይዘቶች ከመጽሐፍት፣ ከፊልሞች፣ ከማስታወቂያዎች እና ከቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ተሰርዘዋል።
የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን እና እንቅስቃሴያቸው በሕግ እንዲገደብ በመከራከር የሚታወቁት የአገሪቱ ምክር ቤት አባል ቪታሊ ሚሎኖቭ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ከግል ጾታዊ ፍላጎታቸው በላይ የምዕራባውያን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ድብቅ አጀንዳዎች አሏቸው ይላሉ።
“የራሳቸው ዓላማ አላቸው። የፖለቲካ ቅርጽ ኖሯቸው እና ዓላማ ኖሯቸው እንደ የፖለቲካ ኃይል ነው የሚንቀሳቀሱት። ...የትኛውም የተመሳሳይ ጾታ እንቅስቃሴ እንዲገደብ እንፈልጋለን። አያስፈልጉንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ሥር በሩሲያ ጾታዊ ግንኙነቶችን በተመለከተ ወግ አጥባቂ አስተሳሰቦች የሰረጹ ሲሆን፣ “የተለመዱ የቤተሰብ እሴቶችን” ማስጠበቅ የሚሉ አመለካከቶች ተጠናክረዋል።
የሩሲያ መንግሥት ባለሥልጣናት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እንቅስቃሴዎች ከምዕራባውያን የተቀዱ እና ለአገሪቱ አደጋን የሚደቅኑ አድርገው ይገልጻሉ።












