ታላቁ ጀርመናዊ የእግር ኳስ ኮከብ ፍራንዝ ቤከንባወር በ78 ዓመቱ አረፈ

ቤከንባወር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከታላላቅ እግር ኳሰኞች ተርታ የሚመደበው ጀርመናዊው ፍራንዝ ቤከንባወር በ78 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ቤከንባወር በአውሮፓወያኑ 1974 የጀርመን አምበል ሆኖ ዋንጫ ሲያነሳ በ1990 ደግሞ በአሠልጣኝነት ደግሞታል።

ቤከንባወር ለባየርን ሙኒክ 582 ጊዜ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን የሙኒክ አሠልጣኝ ሆኖም ቡድንስ ሊጋውን አንስቷል።

‘ደር ካይዘር’ በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ቤከንባወር ሁለት ጊዜ የባለን ደ ኦር አሸናፊ ሲሆን በ1972 የአውሮፓ ቻምፒዮንሺፕ አሸናፊ ነበር።

“ቤከንባወር አልጋው ላይ ሳለ በሰላም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ስንገልጥ በከባድ ሀዘን ነው” ሲሉ ቤተሰቦቹ መግለጫ አውጥተዋል።

የጀመርኑ ውጤታማ ከለብ ባየርን ሙኒክ ባወጣው መግለጫ ታላቁ ቤከንባወር በመሞቱ የተሰማውን ሐዘን ገልጧል።

በ1966 የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ እንግሊዝ ከጀርመን ሲፋለሙ አማካዩ ቤከንባወር እንግሊዛዊው ሰር ቦቢ ቻርልተንን እንዲመክት ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር።

ቤከንባወር ከዚህ ፍልሚያ በኋላ ታዋቂነት ወዳተረፈበት የተከላካይ መስመር ተመለሰ።

በ1966 የዓለም ዋንጫ ቤከንባወር በ20 ዓመቱ 4 ጎሎች በማስቆጠር የውድድር ምርጥ ወጣት ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።

ደር ካይዘር ለጀመርን ብሔራዊ ቡድን 103 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል።

ቤከንባወር በእግር ኳስ ታሪክ የዓለም ዋንጫን በተጫዋችነት እና በአሠልጣኝነት ካነሱ ሶስት እግር ኳሰኞች አንዱ ነው። የብራዚሉ ማሪዮ ዛጋሎ እና የፈረንሳዩ ዲዲዬ ዴሾ ሌሎቹ ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዛጋሎ ባለፈው ሳምንት በ92 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ አይዘነጋም።

ቤከንባወር የባየር ሙኒክ ተጫዋች ሳለ አራት ጊዜ ዋንጫ ያነሳ ሲሆን ሙኒክ በ1974፣ 75 እና 76 በተከታታይ የአውሮፓ ዋንጫን ሲያነሳ አምበል ነበር።

በ1982 ደግሞ ከሀምቡርግ ጋር ቡንደስሊጋውን ማንሳት ችሏል።

ቤከንባወር ከጀርመን ኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት የኒው ዮርክ ኮዝሞስ ተጫዋች ሆኖ ከሌላኛው ታላቅ ብራዚላዊ ፔሌ ጋር ተጫውቷል።

በ1983 ጫማ የሰቀለው ቤከንባወር ከአንድ ዓመት በኋላ የረባ ልምድ ሳያካብት የምዕራብ ጀርመን አሠልጣኝ ሆኖ ተሾመ።

በ1986 ሀገሩን ይዞ ወደ ሜክሲኮ በማቅናት ለፍፃሜው ቢበቃም ዋንጫ ያነሳው ግን ከአራት ዓመት በኋላ በፍፃሜው አርጀንቲናን በመርታት ነው።

በ1986 እና 90 ሀገሩ እንግሊዝን ወክሎ የዓለም ዋንጫ የተጫወተው ጋሪ ሊኒከር በቤከንባወር ሞት ሐዘናቸውን ከገለጡ መካከል ነው።

ሌላኛው ጀመርናዊው የባየርን ሙኒክ የእግር ኳስ ኮከብ ቶማስ ሙለርም እንዲሁ በቤከንባወር ሞት ማዘኑን ገልጧል።

በ1990 ለጥቂት ጊዜያት የፈረንሳዩን ክለብ ማርሴ ያሠለጠነው ቤከንባወር ሁለት ጊዜ የባየርን አሠልጣኝ ሆኖ አገልግሏል።

የአሠልጣኝነት ሕይወቱን ትቶ ወደ አስተዳደር ያመራው ቤከንባወር መጀመሪያ የባየርን ሙኒክ ፕሬዝደንት ቀጥሎ የጀመርን እግር ኳስ ማሕበር ምክትል ፕሬዝደንት ነበር።

ጀመርን በአውሮፓውያኑ 2006 የዓለም ዋንጫ ስታዘጋጅ ሙስና በልተዋል ተብለው ከተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች መካከል አንዴ ቤከንባወር ቢሆንም ክሱ ያለምንም ፍርድ በ2020 ውድቅ ሆኗል።

የፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር አለቃ አሌክሳንደር ቼፌሪን፣ ኬኒ ዳግሊሽ፣ የእንግሊ ፕሪሚዬር ሊግ እና ዶርትመንድ በታላቁ ጀመርናዊ ሞት ሐዘናቸውን ገልጠዋል።