የጋዛ ዋነኛ የሰብአዊ እርዳታ ማሳለፊያ የሆነችው ራፋህ

የተባበሩት መንግስታት እና ምዕራባውያን አስከፊ ሰብአዊ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ቢያስጠነቅቁም እስራኤል ግን ለወራት በደቡባዊ ጋዛዋ ራፋህ ዘመቻ ልታደርግ መሆኑን ስትዝት ቆይታለች።

ከ2.2 ሚሊዮን የጋዛ ህዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በከተማዋ ተጠልሏል። ብዙዎች በድንኳን እና በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እየኖሩ ነው።

የጦርነት ዓላማዋን ለማሳካት እስራኤል በአካባቢው ያለውን የሐማስ ጦር ማጥፋት አለብኝ እያለች ነው።

በራፋህ በኩል ወደ ግብጽ የሚያቋረጠውን የጋዛ መንገድ ለመቆጣጠር እስራኤል ታንኮቿን አስጠግታለች።

ይህ ማቋረጫ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ የእርዳታ አቅርቦቶች ቁልፍ መስመር ነው።

100 ሺህ ሰዎች ከምስራቃዊ ራፋህ ለቀው እንዲወጡ ቴል አቪቭ አዛለች። ይህም የሚካሄደውን “መጠነኛ” ወታደራዊ ዘመቻ ለማከናወን ነው።

ቀጥለን ስለከተማዋ፣ ህዝቡ እና ስለሰደተኞች እንመለከታለን።

ራፋህ የት ትገኛለች?

ራፋህ በደቡባዊ ጋዛ የምትገኝ ከተማ ነች። የራፋ ጠቅላይ ግዛት ግብጽን እና እስራኤልን ያዋስናል። ከተማዋም በራሷ በጋዛ-ግብጽ ድንበር ላይ ከትማለች።

ወደ 1.4 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን እንደሚኖሩባት ይገመታል። ይህ ቁጥር መስከረም 26 ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ ከአንድ ሺህ 200 በላይ ሰዎችን ከገደለበት እና 250 ሰዎችን አግቶ ከወሰደበት ጥቃት በፊት ከነበረው በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ነው።

የራፋህ ስፋት 60 ካሬ ኪሎ ሜትር ያህል እንደሆነ ይገመታል።

በጋዛ ሰርጥ እና በግብጽ መካከል ያለው የማቋረጫ ድንበር ስትሆን ለአስርት ዓመታት ለጋዛ እርዳታ ለማቅረብ ሲያገለግል ቆይቷል።

ከጦርነቱ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪናዎች በየቀኑ ወደ ጋዛ ሰርጥ ለመግባት ይህንን መንገድ ይጠቀሙ ነበር።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ከድንበሩ በታች በደርዘን የሚቆጠሩ የኮንትሮባንድ ዋሻዎች ተቆፍረው ነበር።

እነዚህም የእስራኤል እና የግብጽ ክልከላዎችን በመጣስ ዕቃዎች ለማስገባት የተገነቡ ናቸው። ይህም ራፋህን በንግድ እና በኢኮኖሚው ወሳኝ ቦታ እንዲኖራት አድርጎታል።

የእስራኤል ጦር ከአካባቢው በተተኮሰ ሞርታር አራት የእስራኤል ወታደሮች መሞታቸውን ተከትሎ አካባቢውን መቆጣጠሩን ተናግሯል።

በራፋህ አካባቢ ሦስት ዋሻዎችን ማግኘቱን ጦሩ የገለጸ ሲሆን ይህንን ተጠቅሞ ሐማስ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ሲያመላልስ እንደነበር የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ ገልጿል።

የግብጽ መንግስት ግን እስራኤል የኮንትሮባንድ ንግድ እየተካሄደ ነው ስትል ያነሳችውን ክስ ውድቅ በማድረግ ዋሻዎቹን አፈራርሶ የኮንትሮባንድ ዝውውሩን ለዓመታት እንዳቆመ ተናግሯል።

አሁን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ፍልስጤማዊያን ከጋዛ ሰርጥ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንዲሸሹ እስራኤል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቋን ተከትሎ በርካታዎቹ መጨረሻቸው ራፋህ ሆኗል።

የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ በበኩሉ በዚህ ምክንያት “አስጨናቂ” ሁኔታ ተፈጥሯል ብሏል።

ተፈናቃዮች በየጎዳናው፣ በትምህርት ቤቶች እና በድንኳኖች እየኖሩ ሲሆን የምግብ፣ የመድኃኒት እና የመሠረታዊ መገልገያዎች እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።

የበጋው ሙቀት መጨመር የውሃ እጥረቱን እና የንፅህና አጠባበቅ ችግርን ያባብሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ ዩኒሴፍ በበኩሉ በራፋህ ከሚኖሩት መካከል 600 ሺህ ያህሉ ህጻናት ሲሆኑ ብዙዎቹም በተደጋጋሚ የተፈናቀሉ ናቸው ብሏል።

ይህም የተጎዱ፣ የታመሙ ወይም አካል ጉዳተኛ የሆኑ ህጻናትን ያጠቃልላል ብለዋል።

ስምንት ሺህ የሚሆኑት ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ እና ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ናቸው።

ራፋህ ምን ያህል ለሰብዓዊ ድጋፍ አስፈላጊ ነው?

ራፋህ የጋዛ ቀዳሚ የሰብዓዊነት መንገድ ናት ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲ ኦቻ ቃል አቀባይ የንስ ላርክ እንደገለጹት ከሆነ እስራኤል በራፋህ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ለአካባቢውን የእርዳታ ሥራዎች “ትልቅ ጥፋት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በጦርነቱ ጊዜ ሁሉ ማቋረጫው ለእርዳታ መኪናዎች ዋና መግቢያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።

ተጨማሪ ዕርዳታዎች ከእስራኤል በከረም ሻሎም በኩል የሚገቡበት ነበር።

እስራኤል የራፋህ ማቋረጫን ስትቆጣጠር ነዳጅ በራፋህ በኩል ብቻ ይገባ እንደነበር የገለጹት ላርክ ማቋረጫው መዘጋቱ “የሰብዓዊ ድጋፉን ሙሉ ለሙሉ የሚዘጋ ነው” ብለዋል።

የነዳጅ አቅርቦቶችን በመላው ጋዛ ዕርዳታ ለማድረስ ወሳኝ መንገድ ነው።

አንተግሬትድ ፉድ ሴኪውሪቲ ፌዝ ክላሪፊኬሽን (አይፒሲ) በመጋቢት ወር ባደረገው ግምገማ ረሃብ እያንዣበበ ነው ሲል አስጠንቅቆ ነበር።

ማቋረጫው በአሁኑ ጊዜ ከጋዛ መውጫ ብቸኛው መንገድ ነው።

አንዳንድ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው እና የታመሙ ጋዛውያንን ለህክምና ለማውጣት የሚቻልበት መንገድ ነው።

የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በራፋህ የሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ በከተማዋ የሚገኙ እና በከፊል ሲሠሩ የነበሩ ሦስት ሆስፒታሎችን ጨምሮ በደቡባዊ ጋዛ የሚያገለግለውን ጠቃሚ የሕክምና ተቋማትን እንደሚያቋርጥ አስጠንቅቋል።

“ቀድሞውንም የተሰበረውን የጤና ስርዓት የበለጠ ያዳክማል” ሲል የበሽታዎችን እና የሟቾችን ቁጥር ይጨምራል ሲል ተናግሯል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ “ሰብዓዊ ዕርዳታ እያደገ” እና ወደ ጋዛ የሚደርሱትን ድጋፍ ለማስገባት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።

የራፋህ ታሪክ

ራፋህ ከጋዛ ጥንታዊ ታሪካዊ ከተሞች አንዷ ናት።

በፈርዖኖች፣ አሦራውያን፣ ግሪኮች እና ሮማውያን ቁጥጥር ስር ወድቃ ታውቃለች።

የእስራኤል መንግስት እስከታወጀበት ጊዜ ድረስ ከአውሮፓውያኑ 1917 እስከ 1948 ድረስ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ነበረች።

ከአረብ አገራት ጋር ጦርነት ሲያበቃ ራፋህ ከቀሪው የጋዛ ሰርጥ ጋር በግብጽ ቁጥጥር ስር ዋለች።

ከዚያም በ1967ቱ ጦርነት (የስድስቱ ቀን ጦርነት ተብሎ ይታወቃል) እስራኤል ጋዛን፣ የግብጿን የሲናይ ባሕረ ገብ መሬት፣ ዌስት ባንክን፣ የጎላን ኮረብታዎች እና ምስራቅ እየሩሳሌምን በተቆጣጠረችበት ወቅት ከተማዋን ይዛታለች።

በ1979 ግብጽና እስራኤል የሠላም ስምምነት ተፈራርመው ሲናይ ለግብጽ ተመለሰ።

ራፋህ ተከፋፍሎ ግማሹ በግብጽ ቀሪው ደግሞ በእስራኤል ቁጥጥር ስር በምትገኘው ጋዛ ስር ሆነ።

በሽቦ የተከለለው ድንበር ከተማዋን አቋርጦ ቤተሰቦችን ለሁለት ከፍሏል።

ልክ እንደሌሎች የጋዛ ክፍሎች ሁሉ ራፋህም በ1948 ጦርነት ወቅት የሸሹ ወይም ከቤታቸው የተባረሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ስደተኞች መኖሪያ ሆነ።