ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳምንታትን በፍርሃት፣ በእንግልት እና በረሃብ ያሳለፉት የሐማስ ታጋቾች ታሪክ
ባዶ አግዳሚ ወንበሮች እንደ አልጋ ያገለግላሉ። “የታፈኑ” አየር የሌላቸው ክፍሎች ውስጥ ይታጎራሉ። ትንሽ አንዳንዴም ምንም ምግብ አይቀርብላቸውም። በሐማስ የታገተው ታዳጊ የመስከረም 26ቱን ጥቃት ያደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ቪዲዮ ቪዲዮን እንዲመለከት ተደርጓል።
ጋዛ ታግተው የተፈቱ ሰዎች በመጥፎ፣ በጥርጣሬ እና በፍርሃት ያሳለፏቸውን ሳምንታት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። የአብዛኛዎቹ ታሪክ በዘመዶቻቸው በኩል የወጣ ነው።
ሩቲ ሙንደር 78 ዓመት አዛውንት ናቸው። ልጃቸው እስራኤል ውስጥ መገደሉን የሰሙት አጋቾቿ የሚጠቀሙበትን ሬዲዮ በመስማት እንደሆነ ይገልጻሉ።
ዲቦራ ኮኽን የወንድሟ ልጅ 12 ዓመቱ ነው። ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ያደረሰውን ጥቃት የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን እንዲመለከት መደረጉን ተናግራለች።
በሐማስ ታግተው የነበሩት ሰዎች ቁጥር 240 ይደርሳል። በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረሰው ስምምነት ከ60 በላይ የሚሆኑት ተፈተዋል።
ስላሳለፉት ቀናት በቀጥታ የተናገሩ ጥቂቶች ናቸው። ያሳለፉትን በቀጥታም ሆነ በቤተሰቦቻቸው በኩል የገለጹት ብዙ ስሜታዊ እና አካላዊ ጠባሳ እንዳስከተለባቸው ነው።
ኮኽን ከፈረንሳዩ ቢኤፍኤም የቴሌቭዢን ጣቢያ ጋር ቆይታ አድርገዋል። የ12 ዓመቱ የወንድሟ ልጅ ኢታን ያሃሎሚ በእገታ ያሳለፋቸውን 52 ቀናት ገልጻለች።
“ጋዛ ሲደርስ በርካታ የጋዛ ነዋሪዎች ደበድበውታል። አስቡት ገና 12 ዓመቱ ነው” ብላለች። የሚያለቅስ ሕጻን ደግሞ “በመሣሪያ ማስፈራሪያ ይፈጸምበታል” ስትል አክላለች።
ኮኽን አክላም ኢታን ቢያንስ አንድ ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉበትን “የሐማስን አስፈሪ የጥቃት ቪዲዮዎችን እንዲመለከት አስገድደውታል” ብላለች።
“ኢታን ሲፈታ በጣም ደስ ብሎን ነበር። የደረሰበትን ሳውቅ መጨነቅ ጀምሬያለሁ። ይህ ከአእምሮ በላይ ነው። ሊታሰብ የማይቻል ነው። ማን እንዲህ አይነት ነገር ሊያደርግ እንደሚችል አላውቅም።”
“ኢታንን በአግባቡ እንደሚይዙት ማመን ፈልጌ ነበር። ግን አልሆነም። እነዚያ ሰዎች ጭራቆች ናቸው” ብላለች።
ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል እንደዘገበው የኤታን አባት ኦሃድ በተኩስ እሩምታ መካከል በጥይት ተመትቶ ቆስሏል። አሁንም ጋዛ ውስጥ ታግቶ ይገኛል።
ሌሎች ታጋቾችም በተጨናነቁ የመሬት ውስጥ ዋሻዎች እና አነስተኛ የኤሌክትሪክ ብርሃን ባለባቸው ክፍሎች ውስጥ መቆየታቸውን ለዘመዶቻቸው ነግረዋቸዋል።
በመካከላቸው በድብቅ ለመነጋገር እንዳይሞክሩ በሚል እስክሪብቶ እንዳያገኙ በጠባቂዎቻቸው ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸው ነበር።
የ78 ዓመቷ ሩቲ ሙንደር አርብ ዕለት ከ54 ዓመት ሴት ልጃቸው ካረን ጋር ተለቀዋል። የዘጠኝ ዓመት የልጅ ልጃቸው ኦሃድ ሙንደር-ዚችሪም አብሯቸው ተለቋል።
አጋቾቹ ፍራሽ ሌለው አግዳሚ ወንበር ላይ እንዲተኙ እንዳስገደዷት ተናግራለች። ያውም “በታፈነ” እና ጠባብ ነገር ግን ንጹህ አየር ባለው ክፍል ውስጥ ቆይተዋል።
እሷ አንሶላ በማግኘቷ ዕድለኛ ነበረች። አብዛኞቹ ወጣቶች ይህን አላገኙም።
“እኛ ራሳችንን በአንሶላ ሸፍነናል። ወንዶቹ ወንበሮቹ ስር፣ መሬት ላይ ተኝተዋል። ምክንያቱም ከጎናችን እንዲሆኑ ስለፈለግን ነው” ስትል ለእስራኤል ቻናል 13 ተናግራለች።
ሐማስ ቤተሰቦችን የከፋፈለ ይመስላል። መስከረም 26 በዘመዶቻቸው ላይ ስለደረሰው ነገር ብዙዎች የሚያውቁት አልነበረም።
በሙንደር ቤተሰብ በተለቀቀው ቪዲዮ አንድ ቤተዘመድ ባለቤታቸው የ78 ዓመቱ አቭራም አሁንም ታግተው እንዳሉ ስትናገር ይሰማል። ከረን ሙንደር “ስለዚህ አልተገደለም” ስትል መልሳለች።
ሙንደር ታግተው በነበረበት ወቅት ሬድዮ በማዳመጥ ልጃቸው ሮይ በኒር ኦዝ ኪቡትዝ አካባቢ በሐማስ መገደሉን አውቀዋል።
የተለያየ ምግብ ይቀርባል። የ78 ዓመቷ እስራኤላዊት መጀመሪያ ላይ ዶሮ እና ሩዝ እንዲሁም ሻይ ደግሞ በቀን ሁለት ጊዜ ይቀበሉ እንደነበር ይናገራሉ።
“ደህና ነበርን” ስትል ተናግራለች። ነገር ግን የሚሰጣቸው ነገር ብዙም ሳይቆይ ተቀይሯል። “የኢኮኖሚው ሁኔታ ጥሩ ስላልነበረ ሰዎች ይራቡ ነበር” ስትል አክላለች።
ሌላኛዋ ዘመዳቸው ሜራቭ ራቪቭ በበኩሏ ሙንደር እና ሴት ልጇ ወደ 7 ኪሎ እንዴት እንደቀነሱ ገልጻለች።
ከእገታ የተለቀቁ ሕፃናትን በመንከባከብ ላይ ከተሳተፉት ብዙዎች በሥነ ልቦና ችግር እየተሠቃዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አንድ የኪቡትዝ ቢ ኤሪ ነዋሪ በበኩላቸው ለሳምንታት በአጋቾቻቸው ድምጻቸውን እንዲቀንሱ ከተነገራቸው በኋላ ሁለት ከእገታ የተፈቱ ሴቶች አሁንም በሹክሹክታ እየተናገሩ ነው ብለዋል።
እሑድ ከእገታ የተፈታችው የ9 ዓመቷ አየርላንዳዊ-እስራኤላዊት ኤሚሊ ሃንድ አባት ቶማስ ሃንድ በበኩሉ ሴት ልጁ ማታ ለመተኛት ስታስብ ታለቅሳለች ብሏል።
“ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተዋት ነው” ሲል ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
“ከእሷ ጋር በተገናኘንበት ወቅት በጣም የሚያስደነግጠው እና የሚያስጨንቀው ነገር በሹክሹክታ መናገሯ ብቻ ነበር። እሷን መስማት አልቻልኩም። ጆሮዬን ወደ አፏ ማስጠጋት ነበረብኝ” ሲል ተናግሯል።
“ምንም ድምጽ እንዳታሰማ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣት ቆይቷል” ብሏል።
የ84 ዓመቷ ኤልማ አቭራም እሑድ ከእገታ ተለቀቀች። “ባለባት ከባድ እና ለሕይወት አስጊ በሆነ ምክንያት” በፍጥነት በሄሊኮፕተር ወደ ቤርሼባ ሆስፒታል ተዘዋውራለች።
ልጇ ታሊ አማኖ ቀደም ሲልም ከባድ የጤና ችግር ያለባትን እናቷን ሐማስ የያዘበት መንገድ አስፈሪ የሚባል ነው።
ለ50 ቀናት ያህል አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶች ተከልክላለች ስትል አክላ “እሷን ከማጣታችን ከሰዓታት በፊት እናቴ ተመልሳለች” ስትል ተናግራለች።
የታጋጆች እና የጠፉ ሰዎች ቤተሰቦች ማኅበር የሕክምና ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ሃጋይ ሌቪን በበኩላቸው አቭራም “ለ52 ቀናት...ማንም ሰው ሊያሳልፈው በማይገባ ሁኔታ... ያለ ሰብዓዊ ክብር” ተይዛለች ብለዋል።
ከሳምንታት በፊት የተለቀቁት የ85 ዓመቷ ታጋች ዮቼቭድ ሊፍሽትስ በገሃነም ውስጥ እንደነበሩ በወቅቱ ተናግረዋል።
አያት እና የሠላም ታጋይ የሆኑት እስራኤላዊት በሐማስ በሞተር ሳይክሎች ታግተው፤ በዱላ ተደብድበው እንደ ሸረሪት ድር ወደተወሳሰቡት የጋዛ ዋሻዎች ተወስደዋል።
ታጋቾቹ እንዲተኙበት ወለሉ ንፁህ ሆኖ ፍራሾች መዘጋጀታቸውን በመጥቀስ “በጥሩ ሁኔታ መያዝ እንደቻሉም” ገልጸዋል።
“እንዳንታመም ይከታተሉን ነበር። በየሁለት ወይም ሦስት ቀኑ ሐኪም ይጎበኘን ነበር” ብለዋል።