በዲሞክራቲክ ኮንጎ በበረታው ጦርነት በከተሞች ውስጥ ከፍተኛ ዘረፋ እየተፈጸመ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቡካቩ ውስጥ የኤም 23 አማፂ ቡድን በአካባቢው ጥቃቱን በቀጠለበት ወቅት ምስቅልቅል ያሉ ትዕይንቶች እየታዩ ነው።
ቅዳሜ ዕለት በከተማው አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጥ እና ከፍተኛ ዘረፋ እንደተፈጸመ ሪፖርት ተደርጓል።
ከፍተኛ ዘረፋ ከተፈጸመባቸው መካከል የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ይገኝበታል።
ዘረፋው የተጧጧፈው በሩዋንዳ የሚደገፉ አማፂያን ከሚያደርጉት ግስጋሴ በኋላ ቡካቩ ዋና ከተማ መግባታቸውን የሚገልጹ እርስ በርሱ የሚጋጩ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
ዐርብ ዕለት የኤም23 ተዋጊዎች ከቡካቩ በስተሰሜን የሚገኘውን የካቩሙን አየር ማረፊያ ተቆጣጥረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ኅብረት እየተባባሰ የመጣው ግጭት እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
የኡጋንዳ ጦር አዛዥ በኮንጎ ከተማ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዛታቸውን ተከትሎ ግጭቱ ወደ ሰፊ ቀጣናዊ ጦርነት ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቅዳሜ ዕለት በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት ቀጠናዊ ውዝግብ "በተቻለው ሁሉ" መወገድ አለበት ካሉ በኋላ በምንም ዓይነት "ወታደራዊ መፍትሄ ሊኖር አይችልም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ጉቴሬዝ ጨምረውም "የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር እንዳለበት" አሳስበዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ከቡካቩ የተሰማውን ዜና ተከትሎ ሁሉንም አማራጮች "በአስቸኳይ" እያጤንኩ ነው ብሏል።
"በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሉኣላዊነት ላይ እየደረሰ ያለው ጥሰት ቸል የምንለው ጉዳይ አይሆንም" ሲል አስጠንቅቋል።
የኮንጐ መንግሥት፣ ሩዋንዳ የአገራችንን የተፈጥሮ ሀብት ለመዝረፍ ስትል ''በአካባቢው ትርምስ ትዘራለች'' ሲል ይከሳል፤ ሩዋንዳ ይህን ክስ አስተባብላለች።
ባለፉት ሳምንታት በአማፂያኑ ጦር ግስጋሴ የተነሳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
ቅዳሜ ዕለት ነዋሪዎቹ በቤታቸው ተደብቀው ወደ ቡካቩ ጎዳናዎች ዝር ሳይሉ ነው የዋሉት።
በከተማዋ የምትኖር አንዲት ሴት ለቢቢሲ እንደተናገረችው ሰዎች ወደ ውጭ እንዳይወጡ የተኩስ ድምፅ እየተሰማ ሲሆን ወጣቶች ሱቆችን ሲዘርፉ እና ሲያወድሙ ነበር።
"ለሦስት ቀናት ያህል የሚበቃኝ ምግብ ብቻ ነው ያለኝ፣ እንደ ሴትነቴ ወደ ውጭ መውጣት ይከብደኛል ምክንያቱም በዘራፊዎች ወይም በታጣቂ ቡድኖች ልደፈር እችላለሁ። መሪዎቻችን እኛን ረስተውናል ''ስትል ተናግራለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት የእርዳታ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ደግሞ መጠነ ሰፊው ዘረፋ 6,800 ሜትሪክ ቶን ምግብ የያዘውን በቡካቩ የሚገኘውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዴፖን ያጠቃልላል።
ቃል አቀባዩ ክላውድ ካሊንጋ ይህ ዘረፋ የተቸገሩትን ይበልጥ ለሌላ ችግር የሚያጋልጥ ነው ብለዋል።
ኤጀንሲው የጸጥታው ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ ለሳምንታት ሥራውን አቋርጦ ነበር።
የኤም 23 ተዋጊዎች ቡካቩ መግባታቸውን በተመለከተ እርስ በእርስ የሚጋጩ ዘገባዎች ሲወጡ ነበር።
በሰሜናዊ ቡካቩ ከተማ በባጊራ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ነዋሪዎች በየመንገዱ አማፂያን ማየታቸውን እና ምንም ዓይነት የውጊያ ምልክት እንደሌለ ተናግረዋል።
ሆኖም የኤም 23 ምንጮች፣ ሁለት የኮንጎ ጦር መኮንኖች እና በርካታ የቡካቩ ነዋሪዎች ቅዳሜ ለሮይተርስ እንደተናገሩት አማፅያኑ ወደ መሀል ከተማ አልዘለቁም።
ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይኖርባታል ተብሎ የሚገመተውን የቡካቩ ከተማን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሞከረ ያለው ኤም23 አማጺ ቡድን ይህን ወታደራዊ እርምጃ በድል ከተወጣ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ የግዛት መስፋፋት ሆኖ ይመዘገባል።
ቡካቩ ከሩዋንዳ ጋር የሚያዋሰንና በኪቩ ሐይቅ ደቡባዊ ጫፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን ለአካባቢው የማዕድን ንግድ አስፈላጊ መሸጋገሪያ ሆኖ ይታያል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ቅዳሜ ዕለት የኡጋንዳ መከላከያ ኃይል አዛዥ ጀነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ በኤክስ ጋዜጣ ላይ በለጠፉት ጽሑፍ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘውን ቡኒያ ከተማ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ገልፀው፣ በ24 ሰአታት ውስጥ "ሁሉም ሃይሎች" እጃቸውን እስካልሰጡ ድረስ የከፋ ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ጄኔራል ሙሁዚ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልጅ የበኹር ልጅ ናቸው።
የኡጋንዳ ጦር እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ የኮንጎ ጦርን በምሥራቅ ግዛት ይንቀሳቀሳሉ የሚባሉትን እስላማዊ ታጣቂዎችን በመዋጋት ረገድ ድጋፍ አድርጓል።
ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ዩጋንዳ የኤም 23 ቡድንን እንደምትደግፍ ተናግረዋል ።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ግዛት በማዕድን የበለፀገው አካባቢ ከ1994 ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት እልቂት ጀምሮ ከ30 ዓመታት በላይ በግጭት ሲታመስ ቆይቷል።
አለመረጋጋት በአጎራባች አገሮች ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።
በተለይም በ1990ዎቹ ሁለት ግዙፍ ግጭቶች 'የአፍሪካ የዓለም ጦርነት' በሚል ይጠራል። በዚህ ጦርነት ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።












