ትራምፕ በዩክሬን ላይ በያዙት አቋም የተሸበሩት የአውሮፓ መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ አውሮፓን ገሸሽ አድርጋ ከፑቲን ጋር በድርድር መግፋቷን ተከትሎ የአውሮፓ መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ።
ጉባኤው በሚቀጥለው ሳምንት በፈረንሳይ ይካሄዳል።
ዩክሬን በትራምፕ የተናጥል ውሳኔ ደስተኛ እንዳልሆነች ገልጻለች።
ፕሬዝዳንት ዘለነስኪ እኛን ያላማከለ ድርድርን አንደግፍም ብለዋል።
የአውሮፓ አገራትም በትራምፕ አህጉሩን ገሸሽ ያደረገ የድርድር ሐሳብ ተደናግጠዋል።
በቀጣይ ሳምንት በፓሪስ በሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቀው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬይር ስታርመር "ለአህጉራዊ ደኅንነታችን እጅግ ወሳኝ ጊዜ አሁን ነው" ያሉ ሲሆን ሳይውል ሳያድር 'አውሮፓ በኔቶ ላይ' ትልቅ ሚና መጫወት እንዳለባት አሳስበዋል።
ይህ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የሆነው በዩክሬን የዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ የአውሮፓ መሪዎች ከፑቲን ጋር በሚደረገው ንግግር እንደሚማከሩ፣ ነገር ግን ጦርነቱን ለማስቆም በዩኤስ እና በሩሲያ መካከል በሚደረጉ ማናቸውም ንግግሮች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደማይኖራቸው መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
የዋይት ሐውስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመጪዎቹ ቀናት ከሩሲያ እና ከዩክሬን ተደራዳሪዎች ጋር በሳዑዲ አረቢያ እንደሚገናኙ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በዩክሬን እና በአውሮፓ አጋሮች ዘንድ ስጋት ሊፈጥር የቻለው የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ኪት ኬሎግ ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ድርድሮች 'ብዙ ተሳታፊ ወገኖች ስለገቡበት ነው ያልተሳኩት' ማለታቸውን ነው።
በፈረንጆቹ 2015 ሩሲያና ዩክሬንን የሸመገሉት ፈረንሳይና ጀርመን የሚኒስክ ስምምነት እንዲፈራረሙ አድርገው ነበር። ይህ ስምምነት ግን ብዙ አልዘለቀም።
ሆኖም በምሥራቃዊ ዩክሬን በዶንባስ ግዛት ያለውን ጦርነት በወቅቱ ማስቆም ቻሎ ነበር።
በተለይ የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር በዩክሬን ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት አሜሪካንና አውሮፓ ለማቀራረብ እንደሚጥሩ ተመላክቷል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ወር መጨረሻ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ትራምፕን በዋይት ሀውስ እንደሚያገኟቸው ይጠበቃል።
በዚያን ወቅት ዋናው አጀንዳቸው የሚሆነው የአውሮፓ መሪዎች በዩክሬንና በኔቶ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አስተያየት ለትራምፕ ማስረዳትና ማሳመን ነው።
ሰር ኬር ከዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላ ደግሞ የአውሮፓ መሪዎች፣ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር ተገናኝተው ተጨማሪ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ሰር ኬር ዩናይትድ ኪንግደም "አሜሪካን እና አውሮፓ በአንድ እንዲሆኑ ለማድረግ ትሠራለች" ሲሉ ተናግረዋል።
አሜሪካና አውሮፓ በውጫዊ ጠላት የተነሳ መሀላቸው ንፋስ ሊገባ አይገባም ብለዋል።
በዚህ ሳምንት መጨረሻ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ 'የተባበሩት አውሮፓ ጦር' እንዲቋቋም ጠይቀው ነበር።
ይህም የሆነው አሜሪካ ለዩክሬን ከዚህ በኋላ ወታደራዊ ድጋፍ እንደማታደርግ ከገለጸች በኋላ ነው።
ዘለንስኪ በሙኒክ የሰላም ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በጉባኤው ያሰሙት አስደጋንጭ ሐሳብ ከዚህ ወዲያ አሜሪካና አውሮፓ እንደከዚህ ቀደሙ እንደማይቀጥሉ ፍንጭ ሰጥቷል ብለዋል።
ስለዚህም አውሮፓ አህጉር ከአዲሱ እውነታ ጋር ራሱን ማስታረቅና ለአዲሱ እውነታ አይኑን መግለጥ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።
ዘለንስኪ፣ አሜሪካና ሩሲያ ከዩክሬን ጀርባ መደራደር መጀመራቸውን ነቅፈዋል።
ትራምፕና ፑቲን ከሰሞኑ ዘለግ ያለ የስልክ ውይይት ማድረጋቸው አይዘነጋም።
በዚህ የስልክ ንግግራቸው የዩክሬንን ጦርነት በአስቸኳይ ማስቆም እንደሚገባ ተማምነዋል።
ምናልባትም ሁለቱ መሪዎች መጀመርያ በሳኡዲ ሊገናኙ እንደሚችሉ መረጃዎች ጠቁመዋል።
ምናልባትም ሁኔታዎች ከሰመሩ ፑቲን ዋሺንግተንን፣ ትራምፕ ደግሞ ሞስኮን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል።
ዶናልድ ትራምፕ ይህን ለ90 ደቂቃ የዘለቀ ከፑቲን ጋር ያደረጉትን የስልክ ውይይታቸውን ለፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አስረድተዋቸዋል።
ሆኖም ዩክሬን በዚህ ድርድር ቀጥተኛ ተደራዳሪ እንደትሆን የተፈለገ አይመስልም።
ዶናልድ ትራምፕ ነገሩን በቀጥታ ለመጨረስ የፈለጉ ይመስላል። መከላከያ ሚኒስራቸው ብራስልስ ላይ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ዩክሬን ኔቶን የመቀላቀሉ ሐሳብ 'የማይጨበጥ እና ከእውነታው የራቀ' ሲሉ ተችተውት ነበር።
ሩሲያ በኃይል የያዘቻቸውን ሰፋፊ የዩክሬን ግዛቶችን ለ'ቃ የመውጣቷም ነገር 'የማይመስለ' ብለውታል።
ይህ ማለት ዩክሬን በዚህ ድርድር ተሸናፊ ሆና የምትጨርስ ይመስላል።
ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓ አገራት በተለይም ከኔቶ አባል አገሮች ጋር ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም።
በመጀመርያው የግዛት ዘመናቸውም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር። ከታሪፍ ጋር በተያያዘና ከኔቶ መዋጮ ጋር ተያይዞ ዶናልድ ትራምፕ የአውሮፓ አገራት የሚጠበቅባቸውን እያደረጉ አይደለም ብለው ያምናሉ።
ትራምፕ 23 የኔቶ አባል አገራት መዋጮ ከ2% ወደ 5% እንዲያሳድጉ ይፈልጋሉ። ኔቶ በአሜሪካ ጫንቃ ላይ ወድቋል የሚል አቋም አላቸው።
ከትናንት በስቲያ በተደረገው የሙኒክ የሰላም ጉባኤ የአውሮፓ መሪዎች ከፍ-ዝቅ እያደረጉ የወረፉት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ አውሮፓዊያን ትልቁ ስጋታችሁ የሚመነጨው ከቻይና ወይ ከሩሲያ አይደለም ብለዋል።
"ትልቁ አደጋ የተደቀነው ከራሳችሁ ከውስጣችሁ ነው፣ የመናገር ነጻነት ትገድባላችሁ" ሲሉ አክራሪ ፓርቲዎችን በመንግሥታቸው እንዲያሳትፉ መክረዋል።
ቫንስ ከዚህ ሌላ በጀርመን ዋና ቀኝ አክራሪ ከሚባለው ፓርቲ መሪ ጋር መነጋገራቸውም ድንጋጤን ፈጥሯል።
ቫንስ አውሮፓ በስደተኞች ላይ ጥብቅና የማያዳግም እርምጃ እንድትወስድም አሳስበዋል።












