በትግራይ የተለያዩ ከተሞች ጊዜያዊ አስተዳደሩን እና የሠራዊት አዛዦችን የሚደግፉ ሰልፎች ተካሄዱ

ለወራት በውዝግብ ውስጥ የቆዩት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች አለመግባባት እየተካረረ ባለበት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ሁለቱን ወገኖች የሚደግፉ ሰልፎች ተካሄዱ።

በሁለቱ የህወሓት ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት የበለጠ ሰፍቶ ወደ አደባባይ ድጋፍ እና ተቃውሞ የተሸጋገረው ከቀናት በፊት የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራውን ወገን በመደገፍ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።

በሁለት ወገን የቆሙትን የህወሓት ቡድኖች የሚደግፉ እና የሚቃወሙ ወገኖች ከሳምንቱ ማብቂያ አንስቶ አደባባይ በመውጣት አቋማቸውን ለመግለጽ እየተዘጋጁ መሆናቸው በተገለጸበት ጊዜ፣ የክልሉ አስተዳደር ምንም ዓይነት ሰልፍ እንደማይካሄድ አስጠንቅቆ ነበር።

ነገር ግን እሁድ ጥር 18/2017 ዓ.ም. የክልሉ ዋና ከተማ መቀለን ጨምሮ በአዲግራት፣ ወቅሮ፣ ዓድዋ እና ማይጨው ከተሞች ሰልፎች ተካሂደዋል።

በተጨማሪም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳር እና በደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት በፌስቡክ ገጾቻቸው ላይ በበርካታ ከተሞች እና ወረዳዎች ውስጥ የደጋፊዎቻቸው ሰልፎች መደረጋቸውን በምሥል አስደግፈው ገልጸዋል።

እነዚህ ሰልፎች የተካሄዱት የክልሉ የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ እንዲሁም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፎች እንደሌሉ እና መካሄድ እንደሌለባቸው የሚያሳስቡ መግለጫዎች ካወጡ በኋላ ነው።

በህወሓት አመራሮች መካከል ልዩነት መፈጠሩ ይፋ የወጣው ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ሲሆን፣ የበለጠ ወደ መካረር የደረሰው ነሐሴ ወር ላይ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ነበር።

በህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ወገኖች ሲካሰሱ ቆይተዋል። በቅርቡም ሊቀመንበሩ የሚመሩት ቡድን ባካሄደው ስብሰባ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች የህወሓትን የውክልና ቦታ የያዙ በመሆናቸው ቦታውን እንዲለቁ መጠየቃቸው ይታሳል።

ይህንንም ተከትሎ በውዝግቡ ውስጥ ከየትኛው ወገን እንደቆሙ ሳያሳውቁ የቆዩት የትግራይ ወታደራዊ ኃይል አመራሮች ናቸው የተባሉት መኮንኖች ከሳምንት በፊት ህወሓት በወሰነው መሠረት 'የተዳከመ' ነው ያሉት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከኃላፊነት ተነስቶ በሌላ እንዲተካ መወሰናቸውን ገልጸው ነበር።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም ይህ መግለጫ "የመንግሥት ግልበጣ" እና በሕግም በሞራልም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመገልጽ፣ ወታደራዊ መኮንኖቹ ለአንድ ቡድን በመወገን በክልሉ እና በሕዝቡ ላይ ችግርን የሚያስከትል መግለጫ አውጥተዋል ሲል አውግዟል።

ይህ የሁለቱ ወገኖች መካረር ወደ ኃይል እርምጃ እና ወደ ግጭት እንዳያመራ የተሰጋ ሲሆን፣ በተካሄዱት ሰልፎች ላይም በሕዝቡ ውስጥ ከሁለቱ ወገኖች አንጻር የመሰለፍ ሁኔታ ታይቷል።

ከከባድ ጦርነት ውስጥ ወጥቶ በማገገም ሂደት ላይ ባለው በትግራይ ክልል ውስጥ ይህ አለመግባባት ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት በነዋሪዎች ዘንድ ፈጥሯል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ጉልህ ሚና ያለው የፌደራል መንግሥቱ ምርጫ እስኪካሄድ ለውጥ እንደማይኖር ቀደም ሲል ያሳወቀ ሲሆን፣ ውዝግቡ በተካረረባቸው ባለፉት ቀናት ያለውን ቋም በተመለከተ በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም።