የፍሬንድስ ፊልም ተዋናዮች በማቲው ፔሪ ሞት ልባችን ተሰብሯል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፍሬንድስ ተከታታይ ፊልም ተዋናዮች ቻንድለር ቢንግ በሚሰኘው ገጸ ባህርይ ዝናን ያተረፈው አጋራቸው ማቲው ፔሪ ህልፈት ልባችን ተሰብሯል አሉ።
ለአስር ዓመታት ያህል በተላለፈው ፍሬንድስ አብረው የተወኑት ጄኔፈር አኒስተን፣ ኮርተኒ ኮክስ፣ ማት ለ ብላንክ፣ ዴቪድ ሽዊመር እና ሊዛ ኩድሮው ባወጡት የጋራ መግለጫ “በቃላት በማይገለጽ ሁኔታ አጥተነዋል” ብለዋል።
ማቲው ፔሪ ሎስ አንጀለስ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በሚገኝ የመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ሞቶ መገኘቱም ተዘግቧል።
በተዋናዩ አሟሟት ላይ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል።
“በማቲው ህልፈት ልባችን ተሰብሯል” ሲሉም የፍሬንድስ ተዋናዮች ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
“አብረን ብቻ መተወን ብቻ አይደለም። ቤተሰብ ነን። ብዙ የምንናገረው ነገር አለ። በአሁኑ ወቅት ግን የደረሰብንን ከፍተኛ ኃዘን እንወጣ። በጊዜው የምንለው ይኖራል። በአሁኑ ወቅት ልባችን ከማቲ ቤተሰቦች፣ ጓደኞቹ እና በአለም ዙሪያ ከሚወዱት ሁሉ ጋር ነው” ብለዋል።
ማቲው ፔሪ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ነው ፓስፊክ ፓሊሳዴስ መኖሪያው በሚገኘው ቤቱ ውስጥ በመታጠቢያ ገንዳ (ጃኩዚ) ውስጥ የተገኘው።
የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ ቢሮ የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎች ከውሃ ድንገተኛ አደጋ ጋር በተያያዘ እርዳታ ለመስጠት መሄዳቸውን እና ህይወቱ አልፎ እንዳገኙት መግለጫ ቢያወጣም የተዋናዩን ስም አልጠቀሱም።
የእሳት አደጋ ተከላካዮች ተዋናዩን በጃኩዚ ውስጥ ካገኙት በኋላም ምርመራ ቢያደርጉም ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል።
በርካታ አድናቂዎቹ እና ወዳጆቹ የ90ዎቹ ሲትኮም በሆነው ፍሬንድስ ፊልም ላይ አይረሴ ገጸ ባህርይ የነበረውን ቻንድለር ቢንግን በተለያዩ መንገዶች እየዘከሩት ይገኛሉ።
ተዋናዩ ለብዙዎች የፈገግታ ምንጭ ቢሆንም ከፍተኛ ታዋቂነትን ባገኘበት ወቅት ከህመም ማስታገሻዎች እና የአልኮል ሱስን እየታገለ ነበር። በርካታ ጊዜያትም የመልሶ ማገገሚያ ክሊኒኮችም ገብቶ ነበር።
ፍሬንድስ ተከታታይ ፊልም በሚቀረጽበት ወቅት በመጠጥ እና በአደንዛዥ ዕጽ ለሶስት ዓመታት ያህል ቀረጻውን እንደማያስታውስ ከቢቢሲ ጋር ከአውሮፓውያኑ 2016 ባደረገው ቆይታ ገልጾ ነበር።
በዚህም የተነሳ በርካታ የጤና ዕክሎች የገጠሙት ሲሆን ከነዚህም መካከል አንጀቱ በመፈንዳቱ ለሰባት ሰዓታት ቀዶ ጥገኛ አድርጎ ነበር። ለሁለት ሳምንታትም ያህል በጽኑ ህሙማን ማቆያ አሳልፏል።
ማቲው ፔሪ በሌሎች ፊልሞች ላይ ቢተውንም ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ለአስር ዓመታት ከአውሮፓውያኑ 1994- 2004 በታየው ተወዳጁ ሲትኮም ‘ፍሬንድስ’ ነው።
በስድስት ጓደኞች ላይ የሚያተኩረው ‘ፍሬንድስ’ በጓደኝነት ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ከተሰራበት አሜሪካ ውጪም በርካታ የዓለማችን የፊልም አፍቃሪዎች ተወዳጅነትን አግኝቷል።
የመጨረሻው የፊልሙ ክፍል በ52.5 ሚሊዮን ህዝብ የታየ ሲሆን በ2000ዎቹ በከፍተኛነት በመታየት የመጀመሪያ ደረጃ ተቀምጧል።












