ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሕንዳውያንን ፀጉር እያረገፈ ድንጋጤን የፈጠረው ፀጉር የሚመልጠው ወረርሽኝ
በሕንዷ ማሀራሻትራ ግዛት የሚኖሩ ሰዎች ድንገት በተፈጠረ የፀጉር መመለጥ ወረርሽኝ ተጠቅተዋል።
ካለፈው ጥር ጀምሮ ሕፃናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች ፀጉራቸው ድንገት እንደረገፈ የአካባቢው ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
አንዳንዶቹ ሙሉ በመሉ መላጣ ሆነዋል። ይህ ክስተት ብዙዎችን አሸብራል። የሕንድ የጤና ዘርፍ ባለሥልጣናት ጉዳዩን መመርመር ይዘዋል።
የፓሁጂራ መንደር ነዋሪ የሆነው አናንድ (ስሙ የተቀየረ) በወረርሽኙ ፀጉራቸውን ካጡ ሰዎች መካከል ነው።
ፀጉሩን ማጣት የጀመረው በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ ሲሆን፣ ወደ ፀጉር ቤት ሄዶ ሙሉ በመሉ ተላጭቶታል። ፀጉር ድጋሚ ማደግ ጀመረ። ትንሽ ቆይቶ እንደ አዲስ መመለጥ ያዘ።
ምንነቱ ያልታወቀው ወረርሽኝ የሚጀምረው በማሳከክ ነው። ቀጥሎ ፀጉር መነቀል ይጀምራል። አንዳንዶች ከተላጩት በኋላ ፀጉራቸው መልሶ አድጎላቸዋል። ምክንያቱ ግን አሁንም አልታወቀም።
አዩሽ የተባለው የሕንድ የአማራጭ ሕክምና ሚኒስቴር ለተጠቂዎች እንደሁኔታው መድኃኒት ማዘዝ ጀምሯል።
የተለያዩ የሀገሪቱ የጤና ምርምር ተቋማት በጋራ በመሆን ክስተቱን እየመረመሩ ይገኛሉ። ወደ ሥፍራው አቅንተው ያመጡት ናሙና ላይ ምርመር ጀምረዋል።
የአኮላ ሜዲካል ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሚናክሺ ጋጅቢዬ "ሁኔታው በፈንገስ የተሰከተ አይደለም። በሽታም ተብሎ አይመደብም" ይላሉ።
የአካባቢው ሰው የተጠቀመው ምርት ካለ እንዲሁም ውሀው እንደሆነ በሚል ምርመራ ማድረግ መጀመራቸውን ገልፀዋል።
ፀጉር ማጣት እና መገለል
በክስተቱ ምክንያት ፀጉራቸውን ያጡ አንዳንድ ሰዎች በአካካቢው ማኅበረሰብ እየተገለሉ ነው።
ቢቢሲ ሥፍራውን ሲጎበኝ ሕፃናት ወደ ውጭ ወጥተው ማውራት በመፍራት ቤት ውስጥ ተሸሽገው እንደነበር ተመልክቷል።
በአካባቢው ለትዳር መተጫጨት ቆሟል። ፀጉራቸውን ያጡ ከማኅበረሰባዊ ስብስብ ተገልለዋል። ተማሪዎች ደግሞ ትምህርት ቤት ውስጥ መሰላቂያ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የ55 ዓመቷ ፓርቫቲ (ስሟ የተቀየረ) "የልጄ ፀጉር ረግፏል። ለማጨት ያሰበውንም ትቶታል" ትላለች።
"ልጄ ወደ ውጭ ለመውጣት ስለሚሳቀቅ ቤት ነው የሚውለው። የአካባቢው ሰው እንዲያየው አይፈልግም።"
የ60 ዓመቷ ካቬሪ ዳሎካር ዞማ ፀጉሯ ወርዶ ወገቧን ይሸፍን ነበር።
"አንድ ቀን ፀጉሬን ሳበጠር በርካታ ፀጉር ረገፈ። ሳጥበው ጭራሽ በብዛት መርገፍ ያዘ። ይህን ሁሉ ፀጉር ማጣት በጣም ያሳዝናል" ትላለች።
የቆዳ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ሶሜሽ ጉፕታ አካባቢውን ጎብኝተዋል። ለአካካቢው ሰው ስለፀጉር ማጣት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሞክረዋል።
"ሙሉ በሙሉ ፀጉራቸውን ያጡ ሰዎች ድጋሚ እያደገላቸው ነው። ይህ ችግር ይቆያል ብዬ አላስብም። እንደ አዲስ የሚያድገው ፀጉር ጥሩ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
አክለው "በፍጥነት የሚዛመት አይመስልም። ከሰው ሰው የመተላለፍ ዕድሉን ዝቅተኛ ይመስላል" ይላሉ።
ዶ/ር ሺላ የአካባቢው ነዋሪ ስለሚጠቀመው ሻምፑ እና ቅባት እንዲጠነቀቅ ይመክራሉ። አክለውም ማበጠሪያ መዋዋስ እንዲቀር እና ሰዎች እንዳይደናገጡ ያሳስባሉ።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ፀጉራቸው እንደረገፈ ሲናገሩ ተሰምቷል።
አንዳንዶች በጊዜያዊነት የፀጉር መርገፍ ተከስቶባቸዋል። በሕንድ አንዳንድ አካባቢዎችም መሰል ሁኔታ ታይቶ ነበር።
የዘርፉ ሰዎች በሕንድ ለተፈጠረው ክስተት ቀንደኛ ምክንያት አድርገው የሚያስቀምጡት የአካባቢ መበከል ነው። ነገር ግን ባለሥልጣናት የሥፍራውን ውሀ ሌሎች ካባቢያዊ ምክንያቶች መርምረዋል።
የሥፍራው የምንጭ ውሀ ናሙና ተወስዶ ተመርምሯል። ውሀው ለመጠጥ እንዲሆን ለማድረግም በክሎሮኪን መታከሙ ተሰምቷል።