ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እሑድ ዕለት ከትራምፕ ጋር ተገናኝተው የሩሲያን ጦርነት ስለ መቋጨት ሊነጋገሩ ነው

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ፤ አገራቸው ከሩሲያ ጋር እያደረገች ያለውን ጦርነት ለመቋጨት ለሚደረገው ንግግር ነገ እሑድ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደሚገናኙ አስታወቁ።

ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ፤ በአሜሪካ በተዘጋጀው የሰላም ዕቅድ እንዲሁም አሜሪካ የደኅንነት ዋስትና ስለምትሰጥበት ሁኔታ በሚያትተው ሌላ ዕቅድ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። አንድ ከፍተኛ የሩሲያ ባለሥልጣን ግን ሞስኮ ከአሜሪካ ጋር ድርድር እያደረገችበት ያለው የሰላም ዕቅድ "ፍጹም የተለየ" እንደሆነ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ፤ ሩሲያ ወታደሮቿን የምታስወጣ ከሆነ ዩክሬንም ምሥራቃዊውን ዶምባስ ግዛት እንደምትለቅቅ በመግለጽ የድርድር ሀሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል። የሩሲያ መንግሥት እስካሁን ድረስ ስለዚህ የድርድር ነጥብ አስተያየት አልሰጠም።

ቅዳሜ ዕለት ሩሲያ በዩክሬን ኪዬቭ ግዛት በከፈተችው አዲስ ጥቃት ቢያንስ አንድ ሰው ጉዳት እንደደረሰበት የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል። የጥቃቱ ፍንዳታ ድምጽ ዋና ከተማዋ ኪዬቭ ድረስ ተሰምቷል።

የዩክሬን የአየር መከላከያ ኃይሎች ጥቃቱን እያከሸፉ መሆኑን የተናገሩት የኪዬቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትሽኮ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደተዘጋጁላቸው መጠለያዎች እንዲገቡ አሳስበዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የከፈተችው በየካቲት 2014 ዓ. ም. ነበር። በአሁኑ ሰዓት ሞስኮ 75 በመቶ የሚሆነውን የዶኔትስክ ግዛት እና የአጎራባቹን ሉሃንስክ 99 በመቶ ትቆጣጠራለች። እነዚህ ግዛቶች በጥቅሉ ዶንባስ ተብለው ይጠራሉ።

ዩክሬን ጦርነቱን ለመቋጨት በሚደረገው የሰላም ስምምነት ውስጥ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጣት ትሻለች። ዜሌንስኪ ያቀረቡት አንዱ አማራጭ፤ ሩሲያ በኃይል ለመያዝ ሞክራ ባልተሳካላት የዶንባስ አካባቢዎች ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነ "ነጻ የኢኮኖሚ ዞን" ማቋቋም የሚል ነው።

ዜሌንስኪ አርብ ዕለት 20 ነጥቦችን የያዘው የሰላም ዕቅድ 90 በመቶ መጠናቀቁን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። "ሥራችን ሁሉም ነገር 100 በመቶ ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥ ነው" ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባጋሩት ልጥፍ ደግሞ፤ "አንድም ቀን እያባከንን አይደለም። በቅርቡ በከፍተኛ አመራር ደረጃ፤ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ለመገናኘት ተስማምተናል። አዲሱ ዓመት ከመግባቱ በፊት ብዙ ሊወሰን ይችላል" ሲሉ ጽፈዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው አርብ ዕለት በታተመው የፖለቲኮ መጽሔት ላይ በወጣ ቃለ መጠይቃቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት "እኔ እስከማጸድቀው ድረስ ምንም ነገር የለውም" ማለታቸው ተዘግቧል።

የሰላም ሂደቱ በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር በኩል በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሆነ እንደሚያስቡ የተናገሩት ትራምፕ፤ "በቅርቡ" ከፑቲን ጋር ንግግር አደርጋለሁ ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

የክሬምሊን ልዑክ የሆኑት ኪሪል ዲሜትሪቭ ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ፍሎሪዳ የነበራቸውን ስብሰባ አጠናቅቀው ወደ ሩሲያ ከተመለሱ በኋላ፤ የፕሬዝዳንት ፑቲን ረዳቶች ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ተጨማሪ ንግግር በስልክ አድርገዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሰርጌይ ርያብኮቭ በተደረገው ንግግር ጥሩ መሻሻሎች መታየታቸውን ጠቅሰዋል። ነገር ግን ዩክሬን በአሜሪካ ዕቅድ ላይ የሚደረገውን ንግግር "ለማበላሸት" እየሞከረች ነው በማለት ከስሰዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው አርብ ዕለት በሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥን በሰጡት አስተያየት፤ "ታኅሣሥ 25/2025 በእውነትም ለመፍትሔ አንድ ደረጃ የተቃረብንበት ዕለት ሆኖ በሁላችንም አዕምሮ ውስጥ የሚኖር ይመስለኛል። የመጨረሻውን ግፊት አድርገን ስምምነት ላይ መድረስ የመቻላችን ጉዳይ ግን በምናከናውነው ስራ እና በሌላኛው ወገን ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ላይ ይወሰናል" ብለዋል።