ፑቲን፣ ምዕራባውያን ሩሲያን በአክብሮት ከያዙ ጦርነት እንደማይኖር ቃል ገቡ

አዳራሽ ውስጥ የተካሄደው ዝግጅት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ለፑቲን የሚቀርቡ ሦስት ሚሊዮን ጥያቄዎች ቀድመው መግባታቸውን የፕሮግራሙ አዘጋጆች አስታውቀዋል

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ምዕራባውያን ሩሲያን በአክብሮት ከያዙ በዩክሬን ላይ ጦርነት እንደማይኖር ቃል ገቡ።

ፕሬዚዳንቱ ሞስኮ የአውሮፓ አገራት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እያቀደች ነው መባሉንም " ትርጉም አልባ" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

ፑቲን ይህን ያሉት የአራት ሰዓት ተኩል ገደማ ርዝመት ባለውና በቴሌቪዥን በተላለፈ ዝግጅት ላይ ከጋዜጠኞች እና ከማኅበረሰቡ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።

ከሩሲያ ሚዲያ እና ከሕዝቡ የቀረበላቸው ጥያቄዎች ፑቲንን የሚፈትኑ ባይሆኑም ከውጭ ሚዲያዎች የአሜሪካው ኤንቢሲ እና ቢቢሲ ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ተፈቅዶላቸው ነበር ።

በፕሮግራሙ ላይ የቢቢሲው ስቲቭ ሮስንበርግ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ በፈፀመችበት ወቅት ፑቲን የተጠቀሙትን ቃል በመጠቀም "ልዩ ወታዳራዊ ኦፕሬሽን" ይኖር እንደሆነ ጠይቋቸው ነበር።

"ካከበራችሁን፣ ልክ እኛ ሁል ጊዜ እናንተን ለማክበር እንደምንሞክረው ሁሉ እናንተም ፍላጎታችንን ካከበራችሁልን ሌላ ኦፕሬሽን አይኖረም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም ፑቲን፣ ሩሲያ ከአውሮፓ ጋር ጦርነት ለመግጠም እያቀደች እንዳልሆነ፣ ነገር ግን አውሮፓውያን ከፈለጉ "ዝግጁ እንደሆነች" ተናግረው ነበር።

ፕሬዚዳንት ፑቲን አርብ ዕለት በነበረው ዝግጅት ከቢቢሲ የሩሲያ አርታኢ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም "ልክ ኔቶ ምሥራቃዊ ክፍል መስፋፋት ላይ እንዲኖር እንደደገፈው ካላታለላችሁን በዩክሬን ላይ ሌላ ወረራ አይኖርም" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፑቲን እንደ አውሮፓውያኑ 1990 ሶቭየት ኅብረት ከመፈራረሷ በፊት በወቅቱ የሶቭየት ሕብረት መሪ ሚካሂል ጎርባቾ ደግፏል ሲሉ ኔቶን ይወቅሳሉ። በኋላ ላይ ግን ጎርባቾቭ ይህንን አስተባብለዋል።

በርካቶች በተገኙበትና በቀጥታ በተላለፈው በአርብ ዕለቱ ዝግጅት ላይ ፑቲን ክሪሚያን ጨምሮ የተያዙትን የዩክሬን ግዛቶች የሚያሳይ የሩሲያ ሰፊ ካርታ ከጀርባቸው ታይቷል።

ፑቲን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የዩክሬንን ጦርነት በሰላም ለማቆም " ዝግጁ እና ፈቃደኛ" መሆናቸውን ቢገልጹም እንዲሳካ ያሳዩት ጥረት ግን ትንሽ ነው።

አሁንም እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 ባደረጉት ንግግር ላይ ያነሷቸውን መርሆች ደግመውታል። ፑቲን በዚያ ንግግራቸው የዩክሬን ኃይሎች ሩሲያ በከፊል ከያዘቻቸው አራት ክልሎች እንዲወጡ እና ኪዬቭ የሰሜን የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶን ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት እንድታቆም ጠይቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም እያደረጉ ባለው ጥረት ባቀረቡት የሰላም ዕቅድ ላይ በዩክሬን አዲስ ምርጫ መካሄድ መካተት አለበት ብለዋል። ምርጫ ከተካሄደ ደግሞ ዩክሬን ላይ ጥቃት እንደሚቆም አክለዋል።

የኤንቢሲው ሳይሞንስ፣ ፑቲን የትራምፕን የሰላም ዕቅድ ካልተቀበሉ ለዩክሬንያውያን እና ሩሲያውያን ሞት ኃላፊነት ይወስዱ እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ የትራምፕን የሰላም ጥረት አድንቀው "ስምምነቱን እንዳይሳካ ያደረገችው ሩሲያ ሳትሆን ምዕራባውያን ናቸው" ብለዋል።

"ኳሱ በምዕራባውያን እጅ ነው" ያሉት ፑቲን፣ በዋናነት የኪዬቭ አስተዳደር መሪዎችን እና አውሮፓውያን ደጋፊዎቻቸውን ለዚህ ተጠያቂ አድርገዋል።

ሆኖም ፕሮግራሙ ከተላለፈ ከአንድ ሰዓት በኋላ የዩክሬን ባለሥልጣናት ሩሲያ በዩክሬን ደቡባዊ ኦዴሳ ክልል በፈፀመችው ጥቃት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 15 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

በቀጥታ በተላለፈው ፕሮግራም ላይ ከማኅበረሰቡ ጥራት የጎደለው የቧንቧ ውሃ አቅርቦት፣ የሞባይል ኢንተርኔት መቋረጥን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል። ለኢንተርኔት መቋረጡ ባለሥልጣናት የዩክሬን የድሮን ጥቃትን ምክንያት አድርገዋል።

የአገሪቱን ኢኮኖሚን እና የውጭ ፖሊሲን በተመለከተም ፑቲን ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥን እንዳለው በዚህ ዝግጅት ላይ ለፑቲን ለማቅረብ ከ3 ሚሊዮን በላይ ጥያቄዎች ተልከዋል።