የሱዳን ጦር የፕሬዚደንቱን ቤተ መንግሥት መልሶ መቆጣጠሩ የአገሪቱን ጦርነት አቅጣጫ ይቀይራል?

የሱዳን ጦር ወታደሮች የፕሬዝዳንቱን ቤተ መንግሥት መቆጣጣራቸውን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚያሳዩት ፈንጠዝያ እንዲሁም በቅርብ ወራት ውስጥ የተለያዩ ግዛቶችን መቆጣጠራቸው ወሳኝ የማጥቃት እርምጃ ላይ መሆናቸውን ያሳያል።

የሱዳን ጦር ኃይሎች በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ዋና ከተማይቱን መቆጣጠር ተስኗቸው ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (RSF) እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት ለሁለት ዓመታት ሲዋጉ ቆይተዋል።

አሁን የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት በእጃቸው አስገብተዋል፤ የተቀረውን የዋና ከተማውን ክፍል ደግሞ በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል እየተዋጉ ነው።

ይህ ይሁን እንጂ ጦርነቱን ለማሸነፍ በጣም ሩቅ መንገድ ላይ ናቸው።

ታሪካዊው የሪፐብሊካን ቤተ መንግሥት የአገሪቱ ስልጣን እና የሉዓላዊነት ምልክት ነው።

ወታደራዊ የአገሪቱ መንግሥት ቅቡልነት ያለኝ የአገሪቱ ብቸኛ ገዢ እኔ ነኝ ለሚለው ትርክቱ እንዲሁም ከ"አሸባሪ ሚሊሻዎች" ጋር እየተዋጋ ስለመሆኑ ትዕምርት ሆኖ የቆመ ነው።

ከዚህ ሁሉ ባለፈ ደግሞ ቤተ መንግሥቱን መቆጣጣር መቻል ስልታዊ ድል ነው።

የሱዳን ጦር ከካርቱም አቅራብያዎች አማፂያኑን ካስወገደ በኋላ፣ ሠራዊቱ አብዛኛውን የከተማውን መሀል ተቆጣጥሮ የፈጥኖ ደራሹ አማፂያን ተዋጊዎችን ከመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ከወታደራዊ ጄነራሎች ዋና መሥሪያ ቤት እንዲርቅ ለማድረግ እየተዋጉ መሆኑን የሠራዊቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ይህ ማለት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ምንም እንኳን ተዋጊዎቹ አሁንም በካርቱም ቢገኙም ዋና ከተማውን መቆጣጠር አቅቶታል ማለት ነው።

ይኹን እንጂ የጦርነት ቀጠናው ምን ያህል ከዋና ከተማዋ ካርቱም ፈቀቅ እንዳለ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች አሁንም በመሀል ከተማ ዙሪያ ተበታትነው የሚገኙ ሲሆን፣ በአውሮፕላን ማረፊያው በከፊል ሰፍረዋል።

ከቤተ መንግሥቱ በስተደቡብ ያለውን ግዛትም በቁጥጥራቸው ስር እንዳዋሉ ናቸው።

ሠራዊቱ በከተማዋ የቀሩትን የፈጥኖ ደራሹ (RSF) ኃይሎች ለማስወጣት ሲሞክር ደም አፋሳሽ ውጊያ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ምንም እንኳ የመከላከያ ሃይሉ ቢዳከምም መልሶ ማጥቃት እንደሚችል ከወዲሁ አሳይቷል። በቤተ መንግሥት ውስጥ በሰው አልባ አውሮፕላኖች በመጠቀም ጥቃት በማድረስ በርካታ የሱዳን ጋዜጠኞችን እና የጦር መኮንኖችን ገድሏል።

የሱዳን ጦር በዋና ከተማው ሙሉ ድልን ከተቀዳጀ የጦርነቱን አቅጣጫ ይቀይረዋል አልያም በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የግዛት ክፍፍል በመፍጠር የበለጠ ልዩነቱን ያሰፋዋል ተብሎ ይገመታል።

በጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይንም ሄምቲ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጦር በምዕራብ ሱዳን አብዛኛው የዳርፉርን ክልል እና አንዳንድ የደቡብ ክፍሎችን ይቆጣጠራል።

በጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው እና በአገሪቱ ወታደሮች የሚደገፈው መንግሥት በበኩሉ ምሥራቃዊ እና ሰሜናዊ ሱዳንን ይቆጣጠራል።

እአአ ሚያዝያ 2023 በመካከላቸው የነበረው የስልጣን ሽኩቻ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከማምራቱ በፊት ሁለቱ የጦር አዛዦች በጋራ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ነበር።

ሠራዊቱ ካርቱምን መቆጣጠሩ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተወሰደበትን ማዕከላዊ ሱዳን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ያስችለዋል።

ምናልባትም ይህ ድል የሱዳን ጦር በጄኔራል ሄምቲ ጠንካራ ይዞታ በሆነው ዳርፉር በተለይም ለአንድ ዓመት ያህል በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከበባ ውስጥ ያለችውን ኤል ፋሸር ነጻ ለማውጣት እንዲነሳሳ ሊያደርግ ይችላል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች እና ደጋፊዎቻቸው ጠንካራ ድጋፍ ባላቸው ይዞታዎች ላይ ብቻ ተገድበው በቆዩ ቁጥር ሱዳን ወደ መከፋፈል ልታመራ ትችላለች።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ትይዩ መንግሥት ለመመስረት አጋር ቡድኖችን በኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ በመሰብሰብ የፖለቲካ ቻርተር እና ሕገ መንግሥት ተፈራርሟል።

ዓላማው በጦር ሜዳ ድል ባይቀናውም ተገዳዳሪ ኃይል ሆኖ እንደሚቀጥል እና አገሪቱን ለመቆጣጠር ያለው ፍላጎት አሁንም እንደማይቀንስ ለማሳየት ነው።

በዚህ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በሱዳን ከፍተኛ ሞት፣ ውድመት እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ረገጣ ደርሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ከዓለም የከፋው ሰብዓዊ ቀውስ ሲል ገልጾታል።

ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቅቀው ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ለአስከፊ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፤ የአገሪቱ የተወሰኑ ክፍሎችም ለረሃብ ተዳርገዋል።

በፈጥኖ ደራሽ አማፂያኑ ከፍተኛ ዘረፋ የተፈጸመባት እና የሱዳን መንግሥት ዕርዳታ ላይ እገዳ ጥሎባት የነበረችው ካርቱም በቅርቡ የረሃብ ወላፈን ይገርፋታል ተብሎ ይሰጋል።

ስለዚህ በከተማው ውስጥ ያለው የኃይል አሰላለፍ ለውጥ በሰብዓዊ ሁኔታዎች ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

ይህ ግን ለአብዛኛው የሱዳን ሕዝብ ትንሽ የለውጥ ዕድል ማለት ብቻ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊዎች ሁለቱንም ተዋጊዎች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታን በማደናቀፍ ይከስሷቸዋል።

ምንም እንኳን ተቺዎች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ነጥለው በጅምላ አስገድዶ መድፈር እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቢከስሱም፣ ሁለቱም ተዋጊዎች በጦር ወንጀሎች ይወነጀላሉ።

የሱዳን ጦር የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ማስመለሱ ለሰፊ ወታደራዊ ድል ትልቅ ማሳያ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋል።

ነገር ግን ምንም እንኳን የሱዳን ጦር ከፍተኛ ነው የተባለውን ድል ቢያስመዘግብም ሁለቱም ወገኖች መላውን ሱዳን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ድል የማግኘታቸው ጊዜ ግን ሩቅ መሆኑን ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች በከሸፉበት በዚህ ወቅት፣ ሁለቱም ወገኖች በቀሪው የአገሪቱ ክፍል ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።