ፑቲን ከወሳኙ ውይይት በፊት የዩክሬን ግዛትን በተመለከተ ከአቋማቸው ፍንክች እንደማይሉ አሳወቁ

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ያለውን ጦርነት የሚቆመው የኪየቭ ወታደሮች ከሞስኮ ግዛት ሲወጡ ብቻ መሆኑን በመግለጽ በአቋማቸውን ጸንተዋል።

ፑቲን በኃይል በያዟቸው የዩክሬን ግዛቶች ላይ ሕጋዊ ዕውቅና ለማግኘት ለረዥም ጊዜ ሲጥሩ ቆይተዋል።

እነዚህም በ2014 ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችውን የክራይሚያ ባሕረ ገብ መሬት እና በጦርነቱ ወቅት ለረዥም ጊዜ በሞስኮ እጅ የቆየውን አብዛኛውን የምሥራቅ ዶንባስ ክልልን ያካትታሉ።

አሁንም የተወሰነውን የዶንባስን ክልል ለምትቆጣጠረው ዩክሬን ወረራውን ለጀመረችው ሩሲያ ግዛቶቿን መስጠት የሚዋጥ አይደለም።

የፑቲን ንግግር ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ፤ ሩሲያ "ጦርነቱን ለማስቆም" የሚደረገውን ጥረት "እንዳቃለለች" ተናግረዋል።

ፑቲን ወደ ኪርጊስታን ባደረጉት ጉዞ ላይ ለጋዜጠኞች ኪየቭ "አንድ ሰው እስኪቀራት" መዋጋት ትፈልጋለች ሲሉ ከስሰዋል።

"በመርህ ደረጃ" ሩሲያም ይህንን ለማድረግም ዝግጁ ነች ብለዋል።

ሩሲያ ጦርነቱን የመግፋት አቅም እንዳላት እና ውጊያው የሚያበቃው የዩክሬን ወታደሮች ከዶንባስ ሲወጡ ብቻ እንደሆነ ያላቸውን አመለካከት ደግመዋል።

ዶንባስ ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ በሚባሉ ክልሎች የተዋቀረው ነው።

"ካልወጡ ግን ይህንን የምናሳካው በጦር መሣሪያ ኃይል ይሆናል" ብለዋል።

ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን የምታስመዘግበው ስኬት በርካታ የሰው ሕይወት አስከፍሏታል። በአሜሪካ የሚገኘው የጦርነት ጥናት ተቋም እንደሚለው ከሆነ፤ አሁን ባለው ፍጥነት ቀሪውን የዶኔስክ ክልል ለመቆጣጠር ሞስኮ ሁለት ተጨማሪ ዓመታት ያህል ይፈጅባታል።

ፑቲን በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት በጥቅምት ወር በአሜሪካ እና በሩሲያ ባለስልጣናት በተዘጋጀው የሰላም ዕቅድ ላይ በአሜሪካ እና በዩክሬን መካከል ከተደረጉ አድካሚ ውይይቶች በኋላ ነው።

መጀመሪያ ላይ ወደ ሞስኮ አድልቶ የነበረው ዕቅድ በጄኔቫ በዩክሬን እና በአሜሪካ ተደራዳሪዎች መካከል በተደረገው ውይይት ላይ ማሻሻያ ተደርጎበታል። የአውሮፓ ተወካዮችም በስዊዘርላንድ ተገኝተው ነበር።

አዲስ ረቂቅ ዐዕቅድ ለሩሲያ መሰጠቱን እና ጦርነቱን ለማቆም ለሚደረገው ስምምነት "መሠረት" ሊሆን እንደሚችል ፑቲን ተናግረዋል።

"በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ መቀመጥ ያለባቸው የተወሰኑ ነጥቦች" ላይ መወያየት "ፍፁም አስፈላጊ" እንደሆነ አክለዋል።

ክሬሚያ እና ዶንባስ በሩሲያ ቁጥጥር ስር እንደሆኑ ቢታወቅም በሕጋዊ መንገድ ዕውቅና ላያገኙ እንደሚችሉ የተጠየቁት ፑቲን "ይህ ከአሜሪካ አቻዎቻችን ጋር የምንወያየው ነጥብ ነው" ብለዋል።

በአሜሪካው ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍን የሚመራው ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ ላይ በሞስኮ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ዊትኮፍን አማቻቸው ጃሬድ ኩሽነር ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ ሐሙስ ዕለት በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር የዩክሬን እና የአሜሪካ ልዑካን "በጄኔቫ ያቀረቧቸውን ነጥቦች ወደ ሠላም እና ደህንነት ዋስትናዎች በሚወስደው መንገድ ለመተርጎም" እንደሚገናኙ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ምንም ዓይነት ስም ባይጠቅሱም የጦር አዛዡ አንድሪ ይርማክ ግን የአሜሪካ የጦር ሚንስቴር ዳን ድሪስኮል በሳምንቱ መጨረሻ ኪየቭን እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት እንደገለጹት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል "ጥቂት የቀሩ አለመግባባቶች ብቻ" እንዳሉ ተናግረዋል።

እነዚህን ነጥቦች ለመወያየት ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር የሚደረግ ማንኛውም ስብሰባ በተስማሙበት የሰላም ስምምነት ላይ የሚመሠረት መሆኑን ያሳያል።

ፑቲን ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ለዩክሬን ሕገወጥ ነው ብለው እንደሚቆጥሩት በመግለጽ አስተዳደሩን እንደማይቀበሉ በድጋሚ ተናግረዋል፤። ስለዚህም ምንም ዓይነት ውል ከእነሱ ጋር መፈራረም "ጥቅም የለውም" ሲሉ አክለዋል።