በጀርመን የገና ገበያ ላይ በተፈጸመ የመኪና ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካቶች ቆሰሉ

በጀርመን ማግደቡርግ ከተማ ህዝብ በተሰበሰበት የገና ገበያ ላይ በተፈጸመ የመኪና ጥቃት ህጻንን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን ባለስልጣናቱ ተናገሩ።
አንድ ግለሰብ መኪናውን ህዝብ በተሰበሰበት ስፍራ ላይ እንደነዳባቸው የተነገረ ሲሆን በዚህም 68ቱ ቆስለዋል። የ15ቱ የከፋ ጉዳት እንደሆነ ባለስልጣናቱ አክለዋል።
ጥቃቱን የፈጸመው የሳዑዲ ዜግነት ያለው የ50 ዓመት ዶክተር መሆኑን የሳክሆኒ አንሃልት ግዛት አስተዳዳሪ ሬይነር ሃዜሎፍ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2006 ወደ ጀርመን የመጣው ዶክተር በቁጥጥር ስር እንደዋለም ተገልጿል።
ግለሰቡ ብቻውን ጥቃቱን እንደፈጸመ የመጀመሪያውን ምርመራ ዋቢ ማሳየቱን ዋቢ አድርገው የተናገሩት አስተዳዳሪው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር በማየት ተጨማሪ ሞቶች ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
ተጠርጣሪው ጥቃቱን ለምን እንደፈጸመ ግልጽ አይደለም።
ከእስልምና ጽንፈኝነት ጋር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም ተብሏል።
ዶክተሩ በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች በይነ መረብ ድረገጾች እስልምናን እንደሚነቅፍ የሚጠቁሙ ጽሁፎችን ዋቢ አድርገው የጀርመን ሚዲያዎች በዘገባቸው ይዘው ወጥተዋል።
ጥቃቱ ከደረሰበት ስፍራ የተገኘ ቪዲዮ በርካቶች መሬት ላይ ተኝተው እንዲሁም በርካታ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እርዳታ ሲያደርጉላቸው አሳይቷል።
ቢቢሲ አንድ ያላረጋገጠው ቪዲዮ አንድ መኪና ገበያውን ደረማምሶ ህዝብ ወደተሰበሰበት ስፍራ ሲያቀና በማህበራዊ ሚዲያ ወጥቷል።

የማግደቡርግ ከተማ ቃል አቀባይ በአካባቢው ያሉ ሁሉም ሆስፒታሎች ለ"ጅምላ የከፋ አደጋ ወይም ሞት" በዝግጅት ላይ መሆናቸውን መናገራቸውን የሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
100 የሚሆኑ የእሳት አደጋ ተከላካዮች እና 50 የነፍስ አድን አገልግሎት ሰራተኞች በስፍራው መሰማራታቸውን የከተማው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ከማግደቡርግ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች "የከፋ ነገር እንደሚያጋጥም የሚያሰጋን ነው" ብለዋል።
አክለውም "ሃሳቤ ሁሉ ከተጎጂዎች እና ከሚወዷቸውን ሰዎች ጋር ነው። ጉዳት ከደረሰባቸው እንዲሁም ከሁሉም የማግደቡርግ ነዋሪዎች ጎን ነን። በእነዚህ ፈታኝ ሰዓታት ውስጥ ጥረት እያደረጉ ላሉ የድንገተኛ አደጋ አገልግሎቶች ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።
ቻንስለሩ ቅዳሜ ዕለት ከተማዋን ይጎበኛሉ ተብሏል።
በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1፡20 ላይም የገና ገበያው መዘጋቱን አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።
ከጥቂት ቆይታ በኋላም ሸማቾች ከገበያው እንዲርቁ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን "እባካችሁ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ገበያውን በስርዓት ለቃችሁ ውጡ" ሲሉ አስተባባሪዎቹ በማህበራዊ ሚዲያ ጽፈዋል።












