የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ በፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸውን አስታወቁ

ከሁለት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ተደርገው ተሹመው የነበሩት አቶ ማሞ ምህረቱ በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ።
ከጥር 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው የተሾሙት አቶ ማሞ፣ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግስ መሥራች ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩ ሲሆን ለሰባት ዓመታት በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይም ሠርተዋል።
አቶ ማሞ ምህረቱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን የወሰዱት እርምጃ ዋነኛው ነው።
አቶ ማሞ በኤክስ ገጻቸው ላይ ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ባሳወቁበት መልዕክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ውስጥ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ እና አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ለውጥ ፕሮግራምን በመተግበር ውስጥ በመሳተፍ አገራቸውን በማገልገላቸው ኩራት እንደሚሳማቸው ገልጸዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ በነበሩበት ጊዜ ወሳኝ የሆኑትን የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ፣ብሔራዊ ባንክ ነጻነት እንዲኖረው የሚያስችል አዲስ ሕግ እንዲወጣ በማድረግ፣ የፋይንናስ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት በማድረግ፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ከመሳሰሉ ተቋማት 10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማስገኘት በኩል የነበራቸውን ሚና ጠቅሰዋል።
በ50 ዓመታት ውስጥ ጉልህ የሆኑት ለውጦችም የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ይዞታ በሦስት ዕጥፍ ማሳደጉን፣ በሰባት ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛ ግሽበት መመዝገቡን፣ የዲጂታል የገንዘብ ዝውውር በአስር እጥፍ ማደጉን እና የፋይናንስ ዘርፉም በከፍተኛ የሃብት መጠን መጠናከሩን አመልክተዋል።
ለዘመናት የውጭ ምንዛሪ በመንግሥት ሲተመን የነበረውን አሠራር የቀየረው ውሳኔ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ተግባራዊ ሲሆን የብር የመግዛት አቅም ለማሽቆልቆሉ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ እርምጃ በመደበኛው እና በትይዩው የምንዛሪ ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ የገበያ መረጋጋት ይፈጠራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም አሁንም ልዩነቱ እንዳለ ቀጥሏል።
አሁን የብሔራዊ ባንክ ኃላፊነታቸው የለቀቁት አቶ ማሞ ምህረቱ ቦታውን የተረከቡት የቀደሙት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይነገር ደሴ (ዶ/ር) ቦታቸውን በፈቃዳቸው ወይም በመንግሥት ይነሱ ሳይታወቅ ነበር።
አቶ ማሞ የብሔራዊ ባንክ ገዢነነትን መልቀቃቸውን ባሳወቁበት የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት ላይ ከመንግሥት ሥራ ጭምር እንደሚለቁ ያመለከቱ ሲሆን፣ ሌሎች ነገሮችን ለመሞከር ማቀዳቸውንም ገልጸዋል።
ስለ አቶ ማሞ ምሕረቱ ከኃላፊነት መልቀቅም ሆነ ስለሚተካቸው ግለሰብ እስካሁን ድረስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተሰጠ አስተያየት የለም።
ከጥር 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩት አቶ ማሞ ምህረቱ በ2014 ዓ.ም. በ100 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ሠርተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ግዙፎቹን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ኢትዮቴሌኮምን ጨምሮ ታላላቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በማካተት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማራ ነው።
አቶ ማሞ ቀደም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት አማካሪ እና የንግድ ጉዳዮች ተደራዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ ከዚያ በፊት ደግሞ በዓለም ባንክ ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት ሠርተዋል።
አቶ ማሞ ምህረቱ በትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ ዲግሪ፣ ከኔዘርላንድስ አምስተርዳም ዩኒቨርስቲ በዓለም አቀፍ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማ እንዲሁም በሕዝብ አስተዳደር ከሃርቫርድ የሥነ መንግሥት ትምህርት ቤት የሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።















