በትይዩ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ላይ የተሰማሩ የ138 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሂሳብ መታገዱ ተገለጸ

ዶላር እና ብር

በትይዩ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ላይ የተሰማሩ የ138 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሂሳብ መታገዱን የአገሪቱ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ማስታወቁን መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

የ138 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሂሳብ መታገዱ የተገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ በትይዩ የውጭ ምንዛሪ ገበያ የተሰማሩ አካላት "ከድርጊታቸው ካልታቀቡ" ገንዘባቸው እንደሚወረስ ካስጠነቀቁ ከቀናት በኋላ ነው።

የአገሪቱ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አንዳንድ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች "ህገወጥ የውጭ ምንዛሪን" እንደ መደበኛ የንግድ ስራ በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆኑን ክትትል ሲደረግባቸው መቆየቱን ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አትቷል።

ከነዚህም መካከል በክትትል የተደረሰባቸው እና በትይዩ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ላይ የተሰማሩ ተቋሙ ዋነኛ ሲል የጠራቸው 138 ተጠርጣሪዎች የገንዘብ እንቅስቃሴ መታገዱን ዘገባዎቹ አስፍረዋል።

የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት በመደበኛው የውጭ ምንዛሬ ገበያ በባንኮች በኩል እንዲከናወን ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የገንዘብ ማስተላለፍ ስርዓት የሚመራበት ህግና አሰራር እንዳላት የጠቆመው መግለጫው፤ ይህንን ተላልፈው "በሕገ-ወጥ መንገድ የምንዛሪ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ላይ ጠንካራ የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል" ነው ብሏል።

በትይዩ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ላይ ተሰማርቶ መገኘት የንብረት መወረስን ጨምሮ በከፍተኛ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ መደበኛ የባንክ ስርዓት እንዲጠቀም ሲያሳስብ መቆየቱም ተገልጿል።

"ይህ የወንጀል ድርጊት የሀገርን የፋይናንስ ስርዓት ጤናማነት በማወክ የማክሮ-ኢኮኖሚውን ዓላማና ግቦች ከማደናቀፍ ባሻገር የሽብር ተግባራትን የሚያበረታታ እና ለሌሎች የፋይናንስ ወንጀሎች መስፋፋት ጭምር በር የሚከፍት በመሆኑ" ህጋዊ እርምጃው እንደሚጠናከር ጠቅሷል።

አቶ ማሞ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ እና "የትይዩ ገበያውን የሚያስፋፉ ህገወጥ ድርጅቶች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ በዚህ ሳምንት ረቡዕ፣ ሐምሌ 30/ 2017 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳስበው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ግብይትን በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ መሰረት በገበያ እንዲመራ በተወሰደው እርምጃ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተቋሙ መግለጹ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱም ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮች ለንግዱ ማኅበረሰብ የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሪ መጠን "በእጥፍ ጨምሯል" ያሉ ሲሆን፤ ሁሉም ባንኮች በድምሩ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ በየወሩ እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል።

አብዛኛው የንግዱ ማኅበረሰብ መደበኛውን የባንክ ሥርዓት እንደሚጠቀሙ በመግለጽም "አንዳንዶቹ ግን ይህን አካሄድ እየተከተሉ ባለመሆናቸው ከትይዩ ወይም ከሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ገበያዎች ይልቅ ወደ መደበኛው የባንክ ሥርዓት እንዲመለሱ አበክረን እናስገነዝባለን" ብለዋል።

የማዕከላዊ ባንክ ገዢው አክለውም "በተለይ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በዱባይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከገበያ ሁኔታ ያፈነገጠ የትይዩ ገበያውን የሚያስፋፉ ሕገ ወጥ ድርጅቶች እንዳሉ በውል ስለተረዳን ይህን ተከታትለን ጠንካራ እርምጃዎችን እንወስዳን" ብለዋል።

ባንኩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም. "በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ የማስመሰል እና ሕገ ወጥ ተግባራትን ፋይናንስ በማድረግ" ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ያላቸውን አራት የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ይፋ አድርጎ ነበር።

ተቀማጭነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት እነዚህ ድርጅቶች ሸገይ ገንዝብ አስተላለፊ፣ አዱሊስ ገንዝብ አስተላለፊ፣ ራማዳ ፔይ እና ታጅ ገንዘብ አስተላላፊ እንደሚባሉ ባንኩ በመግለጫው ጠቁሟል።

ባንኩ በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት የሚላክ ገንዘብ "በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ድርጊት ጋር በተያያዘ ምክንያት ሊወረስ የሚችል" መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም ባንኩ እያከናወነ ያለውን ምርምራ በመቀጠል "እንደ አስፈላጊነቱ ተገቢ እርምጃዎችን" እንደሚወስድም አስጠንቋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ 10.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት በተደረገው ስምምነት መሰረት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ተግባራዊ በማድረግ ብሯን ማዳከሟ ይታወሳል።

ለአስርት ዓመታት መንግሥት በሚወስነው የውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓትን (ፊክስድ ፎሬይን ኤክስቸንጅ ማርኬት) ይመራ የነበረውን አሠራር በመቀየር በገበያ ፍላጎት የሚመራ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል።

ተግባራዊ በተደረገም በአንድ ሳምት ብቻ የብር የመግዛት አቅም በ57 በመቶ መዳከሙ ይታወሳል።

ጭማሪውን ተከትሎ በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና ቸርቻሪዎች የሸቀጦች እና የግብዓቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል።

አዲሱ ማሻሻያ ገቢራዊ ከመሆኑ በፊት አንድ የአሜሪካን ዶላር ግብይት 57.48 ብር የነበረ ሲሆን፤ ከሰሞኑ ብሔራዊ ባንክ ባካሄደው ጨረታ 150 ሚሊዮን ዶላር ለ28 ባንኮች መሸጡን እንዲሁም በአማካኝ አንድ ዶላር 138 ብር እንደሆነ አቶ ማሞ አብራርተዋል።