በትይዩ የውጭ ምንዛሪ ገበያ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ እንደሚወረስ የብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

አቶ ማሞ ምህረቱ

የፎቶው ባለመብት, National Bank of Ethiopia/YouTube

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ትይዩ ውጭ ምንዛሪ ገበያ የሚጠቀሙ ሰዎች "ከድርጊታቸው ካልታቀቡ" ገንዘባቸው እንደሚወረስ አስጠነቀቁ።

አቶ ማሞ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ እና "የትይዩ ገበያውን የሚያስፋፉ ሕገ ወጥ" ድርጅቶች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቁመዋል።

አቶ ማሞ ይህን ያሉት ወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እንቅስቃሴን በተመለከተ ረቡዕ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ዘጠኝ ደቂቃ ገደማ በፈጀው የባንኩ ገዢ መግለጫ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የተካሄደው የውጭ ምንዛሪ ጨረታ እና የውጭ ምንዛሪ ገበያ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ነው።

በመግለጫው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ገለጻ የተደረገው በውጭ ምንዛሪ ጨረታው ላይ ሲሆን፣ ባንኩ ባኬሄደው ጨረታ 150 ሚሊዮን ዶላር ለ28 ባንኮች መሸጡን እንዲሁም በአማካኝ አንድ ዶላር 138 ብር እንደሆነ አቶ ማሞ አብራርተዋል።

"ሁሉም የተሳተፉ ባንኮች የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሬ [መጠን] እንዳገኙ" የጠቆሙት አቶ ማሞ "ጨረታ አሸንፈው የውጭ ምንዛሪ ያገኙ ባንኮች በጨረታ ያገኙትን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ጨምረው በሚቀጥሉት ሳምንታት ለደንበኞቻቸው በበቂ ሁኔታ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል" ብለዋል።

ባንኩ "እንደ አስፈላጊነቱ" የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ማካሄዱን ለመቀጠል መወሰኑንም የብሔራዊ ባንኩ ገዢ አመልክተዋል።

ከዚህ ውሳኔ ጀርባ ያለው አመክንዮ "ባለፈው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ክምችት በሦስት እጥፍ ስለጨመረ እንዲሁም ይህ አበረታች ሁኔታ በአዲሱ የበጀት ዓመት በመቀጠሉ" መሆኑን አብራርተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ በተጨማሪም ማዕከላዊ ባንኩ "የውጭ ምንዛሪ ፍሰት እና ግኝት ከተጠበቀው በላይ ማደጉን" በተጨማሪ ምክንያትነት ጠቅሰዋል።

አቶ ማሞ አብዛኛውን ደቂቃ ወስደው ማብራሪያ የሰጡበት ሁለተኛው ጉዳይ ወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እንቅስቃሴ ነው።

በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮች ለንግዱ ማኅበረሰብ የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሪ መጠን "በእጥፍ ጨምሯል" ያሉት ገዢው ሁሉም ባንኮች በድምሩ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ በየወሩ እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል።

አብዛኛው የንግዱ ማኅበረሰብ መደበኛውን የባንክ ሥርዓት እንደሚጠቀሙ በመግለጽም "አንዳንዶቹ ግን ይህን አካሄድ እየተከተሉ ባለመሆናቸው ከትይዩ ወይም ከሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ገበያዎች ይልቅ ወደ መደበኛው የባንክ ሥርዓት እንዲመለሱ አበክረን እናስገነዝባለን" ብለዋል።

የባንክ ሥርዓቱን የማይጠቀሙ የንግዱ ማኀበረሰብ አባላት "በአፋጣኝ" በባንክ ሥርዓት እንዲገለገሉ አበክረው ያሳሰቡት አቶ ማሞ፣ ባንኩ ወደ ትይዩ ገበያው "የሚገባውን እና የሚዘዋወረውን የገንዘብ እንቅስቃሴ" የሚከታተልበትን ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።

ይህ ሥረዓት "ጠንካራ በቴክኖሎጂ የታገዘ" መሆኑን የጠቀሱት ገዢው "በሕገ ወጥነት በዚህ ኢ-መደበኛ ገበያ የሚጠቀሙ ወገኖች ከድርጊታቸው ካልታቀቡ በስተቀር በቅርብ ክትትል ገንዘባቸውን እስከመውረስ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ" አስገንዝበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት ታማኝነት "ሆነ ብሎ ለመሸርሸር እና የገበያ ዋጋን ለማዛባት በማለም መቀመጫቸውን ውጭ አገር ያደረጉ ሌሎች ሕገ ወጥ የገንዘብ አስተላላፊዎች [ላይ] የሚወስደውን ተጨማሪ እርምጃዎች አሁንም ይቀጥላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የማዕከላዊ ባንክ ገዢው አክለውም "በተለይ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በዱባይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከገበያ ሁኔታ ያፈነገጠ የትይዩ ገበያውን የሚያስፋፉ ሕገ ወጥ ድርጅቶች እንዳሉ በውል ስለተረዳን ይህን ተከታትለን ጠንካራ እርምጃዎችን እንወስዳልን" ብለዋል።

ባንኩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም. "በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ የማስመሰል እና ሕገ ወጥ ተግባራትን ፋይናንስ በማድረግ" ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ያላቸውን አራት የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ይፋ አድርጎ ነበር።

ተቀማጭነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት እነዚህ ድርጅቶች ሸገይ ገንዝብ አስተላለፊ፣ አዱሊስ ገንዝብ አስተላለፊ፣ ራማዳ ፔይ እና ታጅ ገንዘብ አስተላላፊ እንደሚባሉ ባንኩ በመግለጫው ጠቁሟል።

ባንኩ በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት የሚላክ ገንዘብ "በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ድርጊት ጋር በተያያዘ ምክንያት ሊወረስ የሚችል" መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም ባንኩ እያከናወነ ያለውን ምርምራ በመቀጠል "እንደ አስፈላጊነቱ ተገቢ እርምጃዎችን" እንደሚወስድም አስጠንቋል።