በቅርቡ የተለቀቀ እስራኤላዊ ታጋች በጋዛ የእስር ቆይታው ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመበት ተናገረ

እገታ ላይ የነበረው ሮም ብራስላቭስኪ

የፎቶው ባለመብት, Channel 13 via Reuters

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ዘገባ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ገለጻዎችን ይዟል

ጋዛ ውስጥ ሁለት ዓመት በእገታ ያሳለፈ እስራኤላዊ፤ የወሲብ ጥቃት ተፈጽሞበት እንደነበር ከአንድ የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናገረ።

ቻናል 13 በተባለው ጣቢያ ቀርቦ ቃለ መጠይቅ የሰጠው የ21 ዓመቱ ሮም ብራስላቭስኪ፤ 'ፓለስቲኒያን ኢስላሚድ ጂሃድ' የተባለው ታጣቂ ቡድን አባላት እርቃኑን አስረውት እንደነበር ገልጿል።

"ወሲባዊ ጥቃት ነበር፤ ዋነኛ ዓላማውም ማዋረድ ነበር። ግባቸው እኔን ማዋረድ፣ ክብሬን መሰባበር ነበር" ሲል ተናግሯል።

እስራኤላዊው፤ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰበት በይፋ የተናገረ የመጀመሪያው ወንድ ታጋች ነው።

የእስራኤል ሠራዊት አባል የሆነው ሮም ብራስላቭስኪ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት፤ ከወታደራዊ አገልግሎቱ እረፍት ወስዶ በኖቫ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ በጥበቃነት እያገለገለ ነበር።

ሐማስ እና አጋሩ የሆኑት የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች በዕለቱ በፈጸሙት ጥቃት 1,200 ገደማ ሰዎችን ገድለው 251 ታጋቾችን ወስደዋል። እስራኤል ይህንን ጥቃት ተከትሎ ጋዛ ውስጥ በከፈተችውን ወታደራዊ ዘመቻ 68,000 ሰዎችን ገድላለች።

ብራስላቭስኪ፤ እስራኤል እና ሐማስ በአሜሪካ አደራዳሪነት የደረሱበትን የተኩስ አቁም ተከትሎ ከተለቀቁ በሕይወት ያሉ 20 እስራኤላዊ ታጋቾች አንዱ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሐሙስ ዕለት በተላለፈው ቃለ መጠይቅ እንደተናገረው 'ፓለስቲኒያን ኢስላሚድ ጂሃድ' የተባለው ታጣቂ አያያዝ እየከፋ የመጣው በ2016 መጋቢት ወር ላይ ሃይማኖቱን ከአይሁድ ወደ እስልምና እንደማይቀይር ከገለጸ በኋላ ነበር። እስራኤል እና ሐማስ ከዚህ ቀደም ደርሰውበት የነበረው የተኩስ አቁምም ስምምነት የፈረሰውም በዚህ ወቅት ነበር።

ለሦስት ሳምንታት ዐይኑ ተሸፍኖ እንደነበር የሚናገረው የቀድሞው ታጋች፤ የመስማት አቅሙን ለመገደብ ሲባል ጆሮው ውስጥ ድንጋይ ይከተት እንደነበር ገልጿል። የሚሰጠው ምግብ እና ውሃም እንዲቀንስ መደረጉን አስታውሷል።

ቀጥሎም አጋቾቹ ስቅይት እንዲፈጽሙበት ትዕዛዝ እንደደረሳቸው ተናግሯል። እንደ ብራስላቭስኪ ገለጻ አጋቾቹ አስረው ደብድበውታል፣ በብረት ገመድም ገርፈውታል። ይህ ስቅይት በቀን ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ሲፈጸም እንደነበር አክሏል።

"አዙሪት ውስጥ ገባሁ፤ በሕይወት ለመውጣት መቻሌን ተጠራጠርኩ" ሲል በወቅቱ የተሰማውን አስታውሷል።

ታጣቂ ቡድኑ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ በለጠፈው አንድ ቪዲዮ ላይ ብራስላቭስኪ እያለቀሰ ምግብ እና ውሃ እንዳለቀበት ሲናገር ታይቷል። መቆምም ሆነ መራመድ እንደማይችል እንዲሁም "በሞት ደጃፍ ላይ" እንደሚገኝ ሲናገርም ተደምጧል።

ይሄ ቪዲዮ ከተለጠፈ በኋላ አጋቾቹ ወሲባዊ ጥቃተ ይፈጽሙበት እንደጀመሩ በቻናል 13 ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግሯል።

"ሁሉንም ልብሴን፣ ፓንቴን፣ ሁሉንም ነገር ገፈፉኝ። አሰሩኝ... ሙሉ በሙሉ እርቃኔን ስሆን አለቀስኩ። ያለ ምግብ እየሞትኩ ነበር። እናም 'አድነኝ፣ አሁኑኑ ከዚህ አውጣኝ' ብዬ ወደ ፈጣሪ ጸለይኩ" ሲል የደረሰበትን ዘርዝሯል።

አጋቾቹ "እንደዚህ ዓይነት ተጨማሪ ነገሮችን" ፈጽመው እንደሆ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥም፤ "አዎ፤ ስለዚህ ሁኔታ በዝርዝር ማውራት ለእኔ ከባድ ነው። ስለዚህ [ጉዳይ] ማውራት አልወድም። ከባድም ነው። አሰቃቂ ነገር ነበር" ብሏል።

ከዚህ ቀደም ቢያንስ ታግተው የነበሩ አራት ሴቶች በራሳቸው እና በሌሎች ታጋቾች ላይ ስለደረሰ ወሲባዊ ጥቃት በይፋ መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

አንድ የ'ፓለስቲኒያን ኢስላሚድ ጂሃድ' አመራር፤ ብራስላቭስኪ ደርሶብኛል ያለው ወሲባዊ ጥቃት "ስህተት" ነው ሲሉ ተጨማሪ ማብራሪያ ሳይሰጡ አስተባብለዋል።

በግጭቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ወኪል፤ እርሷ እና በሥሯ ያለው የባለሙያ ቡድን ጋዛ ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ ታጋቾች ላይ መደፈር እና ወሲባዊ የሆነ ስቅይት ስለመፈጸሙ "አሳማኝ መረጃ" መገኘቱን መጋቢት 2016 ዓ. ም. ተናግራ ነበር።

በመስከረም 26ቱ ጥቃት ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ መደፈር እና በቡድን መደፈርን ጨምሮ ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመ ለማመን የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት መኖሩንም ገልጸዋል። ሐማስ በበኩሉ የሪፖርቱን ግኝቶች "መሠረት የለሽ" ሲል አጣጥሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ጠያቂ ኮሚሽን ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ያወጣው ሌላ ሪፖርት ደግሞ እስራኤል "ፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰውን ወሲባዊ፣ መራቢያ አካላዊ እና ሌሎች ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ጨምራለች" የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን አስታውቋል።

ፍልስጤማውያኑ ላይ ይደርሳሉ ከተባሉት ጥቃቶች መካከል "የግዳጅ ልብስ ገፈፋ እና እርቃን መሆን፣ የመድፈር ዛቻን ጨምሮ ወሲባዊ ትንኮሳ፣ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት" ይገኙበታል። እስራኤል እነዚህን ውንጀላዎች "መሰረተቢስ" ብላቸዋለች።

ባለፈው ዓመት አንድ ፍልስጤማዊ ታሳሪ በእስራኤል ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በወታደሮች ወሲባዊ ጥቃት ሲፈጸምበት ያሳያል የተባለ ቪዲዮ ሾልኮ ወጥቶ ነበር። ቪዲዮው እንዲወጣ ማድረጓን ያመነችው የእስራኤል ጦር ዋና አቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ከኃላፊነቷ ለቅቃለች።

ፊንጢጣው የተወጋው ፍልስጤማዊው እስረኛ፤ የደረሰበትን ከፍተኛ ጉዳት ለማዳን ሕክምና ሲከታተል ነበር። ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ አምስት ወታደሮች ክስ ተመስርቶባቸዋል።