ሁለት የጋና ሚኒስትሮች በሂሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸውን አጡ

የፎቶው ባለመብት, Ghana Armed Forces + Ministry of Science
በጋና ወታደራዊ ሂሊኮፕተር ተከስክሶ የአገሪቱ የመከላከያ እና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች ከሌሎች ስድስት ሰዎች ጋር መሞታቸውን የመንግሥት ቃል አቀባይ ገለፁ።
የሂሊኮፕተር መከስከሱ ያጋጠመው በአገሪቱ ማዕከላዊ ክልል አሻንቲ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ኤድዋርድ ኦማኔ ቦአማህ እና የአካባቢ፣ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ኢብራሂም ሙርታላ መሀመድ በአደጋው ሞተዋል።
ይህንንም የአገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ጁሊየስ ዴብራህ "ብሔራዊ ሐዘን" ሲሉ ገልፀውታል።
ቀደም ሲል የጋና ጦር ኃይሎች ሦስት ሠራተኞችን እና አምስት ተሳፋሪዎችን አሳፍሮ የነበረው ዜድ9 ሄሊኮፕተር "ከራዳር" መጥፋቱን ተናግሮ ነበር።
ከዋና ከተማው አክራ የተነሳው ሂሊኮፕተሩ ሕገ ወጥ ማዕድን ማውጣትን ለመከላከል ወደ ኦቡአሲ ከተማ እያመራ ነበር ተብሏል።
የተቃጠለውን የሄሊኮፕተሯን አካል የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተሰራጩ ነው።
የአገሪቱ ባለስልጣናት የአደጋውን መንስዔ እስካሁን አላረጋገጡም።
የአገሪቱ ጦር አዛዥ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ በግማሽ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አዝዘዋል።
በፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ እና በመንግሥታቸው ስም "አገራቸውን በማገልገል ላይ ሳሉ ሕይወታቸውን ላጡት ሠራተኞች" ሐዘናቸውን ገልፀዋል።
የጋና ብሔራዊ ደህንነት አስተባባሪ እና የቀድሞ የግብርና ሚኒስትር አልሃጂ ሙኒሩ መሀመድ፣ የገዥው ናሽናል ዴሞክራቲክ ኮንግረስ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ሳሙኤል ሳርፖንግ ከሟቾቹ መካከል ይገኙበታል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ሃሩና፣ ፕሬዚዳንት ማሃማ "አዝነዋል፤ ስሜታቸው ተጎድቷል" ሲሉ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ቦአማህ በቀድሞው የማሃማ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር እና ከዚያ በፊት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት በቡርኪናፋሶ ሰሜናዊ ድንበር ላይ እየተስፋፋ የነበረውን የጂሃዲስት እንቅስቃሴ ተከላክለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 ፈረንሳይ መቀመጫውን ያደረገው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ ፕሮሜዲያሽን፣ ባደረገው ጥናት የጂሃዲስት ቡድኖች ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ ወጣት ጋናውያንን መመልመላቸውን ይፋ አድርጓል።
በአካባቢው ግጭቶች እየበዙ የመጡ ሲሆን በሰሜን ጋና በሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል የሚደረገውን ግጭት ለመጠቀም እየሞከሩ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት ቀስቅሷል።
ቦአማህ ስለቀድሞው ፕሬዝደንት ጆን አታ ሚልስ የጻፉት መጽሐፍ በሚቀጥለው ዓመት ለንባብ ይበቃል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
ሙሀመድ ሕገ ወጥ የወርቅ ማዕድን ማውጣትን ለመከላከል በሚወሰደው እርምጃ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል።
በጋና ሕገ ወጥ የወርቅ ማዕድን ማውጣት አካባቢን፣ ወንዞችን እና ሐይቆችን እያወደመ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት ማሃማ ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ ይህንን የሕገወጥ ማዕድን ማውጣት የሚቃወሙ ሰልፎች ተካሂደው ነበር።















