ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብፅ በናይል ተፋሰስ ላይ "ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ የተናጠል እርምጃን" እንደማትቀበል ለበርካታ የአፍሪካ አገራት አስታወቀች
የሕዳሴ ግድብ በመጪው መስከረም ይመረቃል መባሉን ተከትሎ ግብፅ "የዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ መልኩ በምሥራቃዊ ናይል ተፋሰስ የሚደረግ የተናጠል እርምጃን" እንደማትቀበል ለበርካታ አፍሪካ አገራት አሳወቀች።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ የናይል ተፋሰስ አገራት ከሆኑት ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኡጋንዳ፣ ከኬንያ እንዲሁም ከተፋሰሱ ውጭ ካሉት ከጂቡቲ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በተናጠል ባደረጉት የስልክ ውይይት ነው ይህንን ያስታወቁት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት 14 ዓመታትን የፈጀው እንዲሁም አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪን የጠየቀው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር ሙሌት ተጠናቆ ምረቃው በመጪው መስከረም እንደሚካሄድ ኢትዮጵያ በቅርቡ ማሳወቋን ተከትሎ ነው።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ስትወተውት የቆየችው ግብፅ ይህንኑ በመድገም ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።
ይህንን አቋሟን በተለይም ኢትዮጵያ የሕዳሴን ግድብ አስመርቃለሁ ባለች ማግስት ያጠናከረች ሲሆን፤ ሚኒስትሩ "በናይል ወንዝ ላይ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚቃረኑ የተናጠል እርምጃን ውድቅ ማድረጋቸውን" የግብፅ ሚዲያዎች አጽንኦት ሰጥተውታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ የግብፅ ባለሥልጣናት የሚያንጸባርቁትን በመድገም የውሃ ደኅንነት ለግብፃውያን የህልውና ጥያቄ እንደሆነ ገልጸው፤ የጋራ የውሃ ሃብቶችን በተመለከተ የዓለም አቀፍ ሕጎችን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከሰሞኑ የግብፁ አብደል ፋታህ አል ሲሲ አገራቸው በናይል (አባይ) ያላትን የውሃ ድርሻ እንዲነካ እንደማትፈቅድ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ከላይኛው የናይል ተፋሰስ አገራት አንዷ ከሆነችው የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ከሰሞኑ በጣምራ በሰጡት መግለጫ "በድጋሚ ለግብፃውያን ማረጋገጥ የምፈልገው 105 ሚሊዮን ዜጎቻችን እና 10 ሚሊዮን የሚሆኑ በአገራችን ያሉ እንግዶቻችን በሕይወት የሚያቆየው ውሃ እንዲነካ ፈጽሞ እንደማንፈቅድ ነው" ሲሉ ፕሬዚዳንት አልሲሲ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጅምሩ እንዲሁም የተካሄዱ አምስት ውሃ ሙሌቶችን በጽኑ ያወገዙት አልሲሲ፤ ከሰሞኑም በነበረው የጋራ መግለጫም በናይል ላይ የሚደረግ የተናጠል እርምጃን አገራቸው ውድቅ እንደምታደርግ አቋማቸውን አስታውቀዋል።
"ግብፅ በውሃ ደኅንነቷ ላይ የተደቀነን የኅልውና ስጋት ችላ ትለዋለች ብሎ የሚያስብ ማንኛውም አካል ተሳስቷል። ሁኔታውን መከታተላችንን እንቀጥላለን፤ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የሕዝቦቻችንን የኅልውና ሃብቶች ለማስጠበቅ ማንኛውንም እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ አልሲሲ አስጠንቅቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የአፍሪካ ሚኒስትሮች ጋር ያደረጉት ውይይትም ይህንን የፕሬዚዳንቱን አቋም ያንጸባረቀ ሲሆን፤ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ውሃዎች እና ተፋሰስ አገራት የሚተዳደሩበት መርህ የጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአገራቱ ጋር ባደረጉት ውይይት የአለም አቀፍ መርሆች ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የትብብር አስፈላጊነትን አጽንኦት መስጠታቸው ተገልጿል።
እንዲሁም በደቡባዊ የናይል ተፋሰስ አገራት ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች በግብጽ የልማት አጋርነት ኤጀንሲ (ኢኤፒዲ) የሚደረገው መርሃ ግብር እና እገዛ ላይ ላይ ውይይት መደረጉን የግብፅ ሚዲያዎቸ ዘግበዋል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመውና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ ብላ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርኅ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት በመጥቀስ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ትቃወማለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሃዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።
በየዓመቱ ከሚፈሰው 84 ቢሊዮን ኩየቢክ ውሃ 12 በመቶው በትነት የሚያልቅ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት በዋነኝነት ግብፅን ትገዛ የነበረችውን ብሪታንያን ለጥጥ ምርቷ በዋነኝነት ተጠቃሚ አድርጓታል።
የነጭ ናይል መነሻ እና 15 በመቶ የሚሆነውን ውሃ ድርሻ የምታበረክተው የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ከአልሲሲ ጋር ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ይህንን የግብፅን ታሪካዊ ተጠቃሚነት በጠቀሰ መልኩ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
"የናይል ሁኔታ ሰፋ ባለ መልኩ ልናየው ይገባል። አንዳንዴ ችግሮች የሚመነጩት ከአቀራረባችን ነው። በታሪካዊ መብቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ፤ የናይል ተፋሰስ አገራት ዓለም አቀፍ ፍላጎትን ልናጤን ይገባል" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ሙሴቪኒ አክለውም "ዓላማችን ለሁሉም ብልጽግና፣ የመብራት አገልግሎተ ተደራሸነት፣ መስኖ እንዲሁም የመጠጥ ውሃ ለሁሉም በሚደርስበት መሆን አለበት" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው "እነዚህን ዓላማዎች በሙሉ በማዕቀፋችን በማካተት ሳይንሳዊ እና ፍትሃዊ መንገዶችን በመጠቀም ማሳካት ይቻላል" ብለዋል።
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ቆይታለች።