ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ላይ "ፍትሃዊ ስምምነት" እንዲደረስ ጥሪ አቅርበዋል ሲሉ የግብፁ ፕሬዚዳንት አወደሱ
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ በሰጡት አስተያየት "ፍትሃዊ ስምምነት" እንዲደረስ ጥሪ አቅርበዋል ሲሉ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ አወደሱ።
ትራምፕ ሰኞ፣ ሐምሌ 7/2017 ዓ.ም. አሜሪካ የ[ሕዳሴ] ግድብን አገራቸው "በገንዘብ ደግፋለች" እንዲሁም ግድቡ "ወደ ናይል የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ" ነው የሚሉ አወዛጋቢ ንግግር ዋሺንግተን ውስጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው ናይል ለግብፅ ሕይወት ነው የሚለውን አጽንኦት በመስጠት "በናይል ወንዝ ውሃ እንዲኖር እየሠራን ነው" ብለዋል።
ይህንን ንግግራቸው ከግብፁ መሪ በኩል ከፍተኛ ሙገሳ ያስገኘላቸው ሲሆን፣ ትራምፕ የሰጡት አስተያያት "አሜሪካ በፕሬዚዳንት ትራምፕ አመራር ግጭቶችን ለመፍታት እና ጦርነቶችን ለማስቆም የምትሰጠውን ከፍተኛ ስፍራ የሚያሳይ ነው" ሲሉ አል ሲሲ ማክሰኞ፣ ሐምሌ 8/2017 ዓ.ም. በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
አል ሲሲ አክለውም "ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢትዮጵያን ግድብ በተመለከተ የሁሉንም ወገኖች ጥቅም የሚያስጠብቅ ፍትሃዊ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያላቸውን ፍላጎት እንዲሁም ናይል ለግብፅ የሕይወት ምንጭ አድርገው ዕውቅና መስጠታቸውንም ግብፅ ታመሰግናለች" ብለዋል በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት።
በተጨማሪ የትራምፕ ራዕይ "ፍትሃዊ ሰላምን፣ ደኅንነትን እና መረጋጋትን ለሁሉም የቀጣናው እና የዓለም አገራት ለማምጣት" በሚያከናውኑት ተግባር አገራቸው ከጎናቸው እንደምትሆን አረጋግጠዋል።
የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ወዳጅነት የተሞላበት ነው ቢባልም፤ ትራምፕ በመጀመሪያ ሥልጣናቸው ዘመን አል ሲሲን "የምመርጠው አምባገነን" ማለታቸውን ተከትሎ ግንኙነታቸው የተወሳሰበ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ተብሏል።
ትራምፕ ግብፅን በዋነኝነት በአጋርነት የሚያዩዋት ከጋዛ ጋር በተገናኘ ነው። ትራምፕ ወደ ሥልጣን በተመለሱ በመጀመሪያ ሳምንት በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሁኔታ እልባት ማበጀት የግብፅ እና የዮርዳኖስ ሁኔታ ነው የሚል አቋም ይዘዋል።
ፍልስጤማውያኑን ከጋዛ ለማፈናቀል አቅደው የነበሩት ትራምፕ ግብፅ እና ዮርዳኖስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን በአገራቸው እንዲቀበሉ ጫና እያደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህ ቀደም የአረብ መንግሥታት ትራምፕ ላቀረቡት የጋዛ መልሶ ግንባታ ዕቅድ አማራጭ የሆነውን ፍልስጤማውያን ባሉበት እንዲቆዩ ለሚያስችለው የግብፅን የ53 ቢሊዮን ዶላር ዕቅድ ድጋፍ አድርገዋል።
ማንኛውንም የፍልስጤም ሕዝብ የማፈናቀል ዕቅድ የዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት ነው ሲሉ ሙሉ በሙሉ የአረብ መንግሥታቱ ውድቅ አድርገውታል።
ይህንን የግብፅ ዕቅድ የፍልስጤም አስተዳደር እና ሐማስ ድጋፍ የሰጡት ቢሆንም አሜሪካ እና እስራኤል በጋዛ ውስጥ ያለውን እውነታ መፍታት የማይችል ሲሉ አልተቀበሉትም።
ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ላይ ለግብፅ የሚወግኑት እንዲሁም ሌሎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉት ከጋዛ ጋር በተገናኘ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
ትራምፕ ሰኞ፣ ሐምሌ 7/2017 ዓ.ም. ከኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሐውስ ባደረጉት ውይይት ግብፅን እንዲሁም [የሕዳሴ] ግድብን አንስተው ተወያይተዋል።
በዚህ ንግግራቸው የኢትዮጵያን ስም ያልጠሩ ሲሆን "የግብፅ ጎረቤት፤ ጥሩ ጎረቤት" ሲሉ ነው የጠሯት።
ይህችን ጎረቤት ሲሉ የጠሯትን ኢትዮጵያን "ጓደኞቼ ናቸው" ሲሉም ትራምፕ ጠቅሰዋል።
"ከግብፅ እና ከአጎራባቿ፣ ጥሩ ከሆነችው ጎረቤቷ ጋር በተያያዘ ሠርተናል" ብለዋል።
"ጓደኞቼ ናቸው፤ ነገር ግን ናይል ተብሎ ወደሚጠራው ወንዝ የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ ግድብ ገነቡ" ብለዋል።
ትራምፕ በስም ያልጠሩት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ ግብፅ በተደጋጋሚ ከናይል ወንዝ በምታገኘው የውሃ መጠን ላይ አደጋ የጋረጠ ስትል በተደጋጋሚ ክስ የምታቀርብበት ነው።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ስትወተውት የቆየችው ግብፅ ከሰሞኑም ይህንኑ በመድገም አስጠንቅቃለች።
በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ግብፅ "የሕዳሴ ግድብን ልታፈነዳ ትችላለች" በሚል አወዛጋቢ ንግግር የተናገሩት ትራምፕ፤ በአሁኑም ለግብፅ ወገንተኝነታቸውን በግልጽ ባንጸባረቀ መልኩ ንግግር ከማድረግ በተጨማሪም አንዳንድ ንግግራቸውም አሳሳችና ግራ ያጋባ ሆኗል።
"የሕዳሴ ግድብ ወደ ናይል የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ ነው" የሚለው ንግግራቸው ከግብፅ በኩል እንኳን ውሃውን ይቀንሰዋል እንጂ "ይዘጋዋል" ወይም ናይልን ያደርቀዋል በሚል የሚቀርብ አይደለም።
ትራምፕ አክለውም "እኔ ግብፅን ብሆን በናይል ወንዝ ውስጥ ውሃ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። እሱ ላይ እየሠራን ነው። ችግሩ መፍትሄ ያገኛል" ብለዋል።
ግብፅ ትራምፕ እንደሚሉት "በናይል ወንዝ ውሃ" ስለሌላት ወይም ደርቆ ሳይሆነ ድርሻዬ የምትለው 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዳይቀንስ ነው እየጠየቀች ያለችው።
ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ቆይታለች።
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው አንድም ጊዜ የኢትዮጵያን ስም ያልጠቀሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለማለትም "ከግብፅ ትንሽ ወጣ ብሎ" የሚል አገላለጽን መርጠዋል።
"ከግብፅ ትንሽ ወጣ ብሎ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ ግድቦች አንዱን ገነቡ። ስለዚህ ጉዳይ ታውቃላችሁ። ይህ ትልቅ ችግር ሆኗል" ብለዋል።
አክለውም "አላውቅም። አሜሪካ ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገች ይመስለኛል" ብለዋል።
ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ለሕዳሴ ግድቡ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረጉ የገለጹት፣ ከዚህ ቀደምም እንዲሁ ከአንድ ወር በፊት አገራቸው ግድቡን በገንዘብ እንደረዳች እና የናይል ፍሰትን ይቀንሰዋል ሲሉ የተሳሳተ መረጃ ሰጥተዋል።
አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የተበጀተለት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ የተገነባው ሕዝቡ ባወጣው ገንዘብ እና አገር ውስጥ ባለ ሃብት ሲሆን ይህም በተደጋጋሚ የተገለጸ ነው።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የትራምፕን ይህንን የገንዘብ ድጋፍን አስመልክቶ በይፋ ትክክል እንዳልሆነ እስካሁን የገለጹት ነገር የለም።
ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው ናይል ለግብፅ "ሕይወት ነው" ያሉ ሲሆን፣ የናይል መነሻ የሆነችው እና የመጀመሪያዋን ግድብ በናይል ላይ የሠራችውን ኢትዮጵያን አልጠቀሱም።
"ግድቡን ከመገንባታቸው በፊት ይህንን ችግር ለምን እንዳልፈቱት አላውቅም፤ ነገር ግን ናይል ውሃ ሲኖረው ጥሩ ነው። አስፈላጊ የገቢ ምንጭ ነው፤ የግብፅ ሕይወት ነው እና ያንን መንጠቅ አስገራሚ ነው። ይህ በፍጥነት የምንፈታው ይመስለኛል" ብለዋል።
በአምስት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥሮ በመጪው አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በይፋ እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።