የሩሲያ የጦር ጀት ከዩኬ አውሮፕላን አጠገብ ሚሳኤል ተኮሰ

ኤስዩ-27 የጦር ጀት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ኤስዩ-27 የጦር ጀት

የሩሲያ የጦር ጀት ከዩናይትድ ኪንግደም አየር ኃይል አውሮፕላን አቅራቢያ ሚሳኤል መተኮሱን ዩኬ አስታወቀች።

የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚንስትር ቤን ዋለስ የሞስኮ ጀት ሚሳኤል የለቀቀው ካልታጠቀው እና በጥቁር ባሕር ላይ ቅኝት ሲያደርግ ከነበረ የዩኬ አውሮፕላን አቅራቢያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሩሲያ መስከረም 19/2015 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ የአየር ክልል ላይ ክስተቱ ያጋጠመው ‘በቴክኒክ ችግር’ ነው ብላለች።

ይህን ክስተት ተከትሎ ዩኬ በጥቁር ባሕር ላይ ታደርግ የነበረውን የቅኝት ስራ አቁማ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ቅኝት የሚያደርጉ አውሮፕላኖች በጦር ጀት ታጅበው ሥራቸውን ጀምረዋል ተብሏል።

ቤን ዋለስ ለዩኬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሲናገሩ፤ አገራቸው ክስተቱን የጠብ አጫሪነት ድርጊት አድርጋ ባትመለከተውም የሩሲያ ተግባር ግን “ነገሮች እንዴት አገደኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሳያ ነው” ብለዋል።

ቤን ዋለስ ይህን ለምክር ቤት የተናገሩት ለአስቸኳይ የሥራ ጉዳይ ካቀኑበት አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ነው። መከላከያ ሚንስትሩ ከአሜሪካው አቻቸው ጋር በዩክሬን ስላለው ሁኔታ እና የሩሲያ የኒውክለር ጦር መሳሪያ የመጠቀም ዛቻን በተመለከተ መክረዋል ተብሏል።

ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ ክስተቱ ሲያጋጥም በአየር ክልሉ ውስጥ ከነበሩት ሁለት የሩሲያ ኤስዩ-27 የጦር ጀቶች መካከል አንዱ ወዳልታጠቀው እና ቅኝት ላይ ወደነበረው የዩኬው አርሲ-135 አውሮፕላን አቅራቢያ ሚሳኤል ለቅቋል።

በጥቁር ባሕር ላይ ያጋጠመውን ክስተት ተከትሎ ቤን ዋለስ የተሰማቸውን ቅሬታ ለሩሲያው መከላከያ ሚንስትር ደብዳቤ መላካቸውን ገልጸዋል።

ክስተቱን በተመለከተ የሩሲያ መከላከያ ሚንስትር በሰጡት ምላሽ ጦራቸው በጉዳዩ ላይ ምርመራ ማካሄዱን እና የሩሲያው ጀት ባጋጠመው ቴክኒክ ችግር ሚሳኤሉ መተኮሱን ገልጸውልናል ሲሉ ቤን ዋለስ ተናግረዋል።

ክስተቱ ያጋጠመው በዓለም አቀፉ የአየር ክልል ውስጥ መሆኑንም የሩሲያ ባለስልጣናት አረጋግጠዋል ብለዋል መከላከያ ሚንስትሩ።

በጥቁር ባሕር ላይ የተከሰተው ነገር የሩሲያ ጦር ስህተት ሊሰራ እንደሚችል ወይም ሕግ እነሱ ላይ ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይችል እንደሚያስቡ ያሳየ ነው ሲሉ ቤን ዋለስ ጨምረው ተናግረዋል።