ዩክሬን በክሪሚያ አቅራቢያ የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ሩሲያ ገለጸች

የሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ያለበት የነዳጅ ጫኝ መርከብ በክሪሚያ አቅራቢያ ዩክሬን በፈጸመችው ጥቃት መመታቱን ባለቤትነቱ የሩሲያ መንግሥት የሆነው ታስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በሌሊት በተፈጸመው ጥቃት የነዳጅ ጫኝ ታንከሩ የሞተር ክፍል መጎዳቱን እና በውስጡ ከነበሩት 11 ሰዎች መካከል ግን ጉዳት የደረሰበት እንደሌለ የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

ብዙዎቹ የሩሲያ የበይነ መረብ ጸሐፊዎች ነዳጅ ጫኝ መርከቡ የተመታው ከክሪሚያ ድልድይ ብዙም ሳይርቅ በዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን መሆኑን ገልጸዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት አቅራቢያ የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውን ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ ዩክሬን እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

የባሕር ላይ ድሮኖች በመጠናቸው ትንሽ ሲሆኑ በውሃ ውስጥ ወይም ደግሞ በአየር ላይ ሆነው በመብረር ጥቃት የሚፈጽሙ ናቸው።

ታስ የዜና ወኪል ከሩሲያ የባሕር አደጋ ሰራተኞች መካከል ያናገረው ሙያተኛ የነዳጅ ጫኝ መርከቡ ሞተሩ ላይ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም ያን ያክል የከፋ አይደለም ብሏል።

ስለታንከሩ ዝርዝር ሁኔታ እና ንብረትነቱ ግን ሙያተኛው ከማብራራት ተቆጥቧል።

ጥቃቱ የደረሰበት ልዩ ቦታ የከርች ወሽመጥ ይባላል። ይህ ቦታ ጥቁር ባሕርን እና አዞቭ ባሕርን የሚያገናኝ ሲሆን ክሩሚያን እና የሩሲያዋን ታማን የባሕር ሰላጤን የሚለይም ነው።

ታስ የዜና ወኪል በተጨማሪም በክሪሚያ ድልድይ ላይ መብራት ጠፍቶ የነበረ ሲሆን ጥቃት ይፈጸማል በሚል የትራፊክ መስተጓጎል እንደነበረም ዘግቧል።

በዚህ አካባቢ እንደዚህ አይነት ጥቃት ሲደርስ ይህ የመጀመሪያ ነው።

አንድ የዩክሬን የጸጥታ ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደግሞ በትናንትናው ዕለት በሩሲያ የጥቁር ባሕር ወደብ ኖቮሮሲስክ አካባቢ አንድ የሩሲያ ተዋጊ መርከብ በዩክሬን የባሕር ድሮን ከፍተኛ ጥቃት ተፈጽሞበታል።

በኋላም ድሮኑ የመርከብ ማረፊያ ቦታውን ሲመታ የሚያሳይ ምስል በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን ሲዘዋወር ነበር።

ነገር ግን የሩሲያ የመከላከያ ሚንስትር በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት ለጥቃት የመጡትን ድሮኖች መከላከላቸውን ገልጸዋል። ደረሰ የተባለውን ጥቃትም አስተባብለዋል።

ኖቮሮሲስክ በከርች ወሽመጥ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ የሚገኝ ሲሆን የሩሲያ ዋነኛው ምርቶችን ወደ ውጭ የመላኪያ ወደቧ ነው።

ዩክሬን የእህል ምርቷን በጥቁር ባሕር በኩል እንድትልክ በተባበሩት መንግሥታት አሸማጋይነት ተደርሶ የነበረውን ስምምነት ሩሲያ ካፈረሰች ወዲህ የባሕር ላይ ጥቃቶች በእጅጉ ጨምረዋል።

የዩክሬን ወደቦች በሩሲያ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶች ጋይተዋል። ዩክሬን በአንጻሩ ጥቃቱን እንደምትበቀል ዝታለች።

በሌላ በኩል በዩክሬን ያለው ጦርነት በሚቋጭበት ሁኔታ ሳኡዲ አረቢያ ዛሬ [ቅዳሜ] ከተለያዩ አገራት ጋር ንግግር ትጀምራለች።

የውይይት ግብዣው ለ30 አገራት የተላከ ሲሆን ሩሲያ ግን የለችበትም። ውይይቱ የሚደረገው በቀይ ባሕሯ የሳዑዲ ከተማ ጂዳ ነው።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ያወጀችው በየካቲት 2022 ነበር።