ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል ተፈጻሚ በሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን ይጠበቃል?
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከአማራ ክልል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ በክልሉ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ባደረገው ውይይት በአማራ ክልል የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ ተሸጋግሯል በማለት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ተደንግገው የነበሩ ሲሆን፣ ካለፉት ልምዶች በመነሳት አሁን በሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ላይ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምንን ሊያስከትል ይችላል?
ከአዋጁ መደንገግ በኋላ ምን ይጠበቃል?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ስለማይገኝ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 93/2/ሀ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምክር ቤቱ በ15 ቀናት ውስጥ ቀርቦ ሁለት ሦስተኛ በሆነ ድምጽ መጽደቅ ይኖርበታል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ይሁንታን ካገኘ በኋላ ተፈጻሚ ሆኖ የሚቆየው ለስድስት ወራት ነው።
ምክር ቤቱ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ አዋጁ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል።
ከአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ድንጋጌው በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ ይተላለፋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል እና በበላይነት የሚመራ አካል (ኮማንድ ፖስት) ይመሠረታል።
አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት በአማራ ክልል የአገር መከላከያ ጨምሮ የፌደራል መንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ሊሰማሩ ይችላሉ። በክልሉ ያለው የደኅንነት ስጋት መጠን አድማስ እየቀነሰ የሚሄድ ከሆነ የአዋጁ መመሪያ እንደ አስፈላጊነቱ ሊላላ ይችላል።
ምን አይነት እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ?
በየትኛውም የክልሉ ስፍራዎች የአገር መከላከያ ኃይልን ጨምሮ የፌደራል ፀጥታ ተቋማት በማሰማራት ሰላም እና ፀጥታ እንዲያስከብሩ ሊያደርግ ይችላል።
የሰዓት እላፊ ገደብ ሊጣል ይችላል።
የሰዎች እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ እና ክልከላ ሊጣል ይችላል።
በየትኛውም መልኩ ሕገ-ወጥ በሚባሉ እንቅስቃሴዎች የተሳተፉ ሰዎችን በምክንያታዊ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እና በ48 ሰዓታት ፍርድ ቤት የመቅረብ መብትን በመሻር አዋጁ ተፈጻሚ ሆኖ እስከሚቆይበት ድረስ ሊያዙ ይችላሉ።
የዜጎችን መሠረታዊ መብት ሊገድብ በሚችለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ወቅት ብርበራዎች ሊከናወኑ ይችላሉ።
አስፈጻሚው አካል ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የጠረጠረውን ግለሰብ አስቁሞ ማንነት መጠየቅ፣ መፈተሽ እንዲሁም በፍተሻ የተያዙ መሳሪያዎችን ሊወርስ ይችላል።
የአካባቢ ሲቪል አመራር መዋቅርን በሙሉ ወይም በከፊል በወታደራዊ አመራር ሊተካ ይችላል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሕግ አስከባሪ አካላት ሕግ ለማስከበር ተመጣጣኝ ኃይል እንዲጠቀሙ ፍቃድ ይሰጠቸዋል።
ይሁን እንጂ ኢሰብዓዊ አያያዝን የሚከለክለው አንቀጽ 18፣ የእኩልነት መብትን የሚጠብቀው አንቀጽ 25 እንዲሁም በአንቀጽ 39 የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች መብት ሥር የተጠቀሱት አንቀጽ 1 እና 2 ሊገደቡ አይችሉም።
ሊከለከሉ የሚችሉ ተግባራት አሉ?
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተግበሪያ መመሪያ የተከለከሉ ተግባራትን እና ግዴታዎችን ይዞ ይመጣል።
ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ መመሪያዎችን የመቀበል ግዴታ ይኖርባቸዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በየትኛወም መንገድ የሚቃረን ተግባር የተከለከለ ይሆናል።
የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ይሆናል።
ፍቃድ ካላቸው የመንግሥት የፀጥታ አካላት ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ይሆናል።
ዜጎች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ይዘው መንቀሳቀስ ግዴታቸው የሚሆን ሲሆን፣ መታወቂያ የሌላው በአስቸኳይ ከቀበሌው ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት መያዝ ግዴታው ሊሆን ይችላል።
አዋጁን ማን ያስፈጽመዋል?
በአማራ ክልል ተፈጻሚ የሚሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልሉ መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት በጥምረት በበላይነት ሊያስፈጽሙት ይችላል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱ እና ከሕግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ይቋቋማል።
ቦርዱ በአዋጁ ምንክያት የታሰሩ ሰዎችን ማንነት ይፋ ማድረግ፣ የሚወሰዱ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠር እና እርምጃዎች ኢሰብዓዊ ከሆኑ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ሃሳብ መስጠት እና ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያደርጋል።