ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገ
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከአማራ ክልል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ በክልሉ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገ።
ለሳምንታት የቆየው በአማራ ክልል ያለው አለመረጋጋት መባባሱን ተከትሎ የክልሉ መስተዳደር ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር ትናንት፣ ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ ጠይቋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ውይይት በአማራ ክልል የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተሸጋግሯል በማለት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ተገልጿል።
ይህም የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ደረጃ በማወክ “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ፤ የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር” የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ነው ብሎ ወስኗል።
ለዚህ ውሳኔም ያጋጠመው ቀውስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን በመግለጽ፣ ያለው ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ የአማራ ክልል ጥያቄ ማቅረቡ ተጠቅሷል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዳለው መንግሥት ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድን እንዲከተሉ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቶ፣ ነገር ግን ይህ ጥሪ ተቀባይነት ሳያገኝ ችግር መፈጠሩን ገልጿል።
“የታጠቁ ፅንፈኛ ቡድኖች እየፈፀሙ ባለዉ ጥቃት ምክንያት በክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል” ብሏል።
በዚህም “ይህንን ፈር የለቀቀ እንቅስቃሴ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሁኔታ በመፈጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ” ውሳኔ መሳለፉን ገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱ፣ ሕገ መንግሥቱ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የተቃጣ አደጋን በመደበኛ የሕግ ሥርዓት ለመቆጣጠር ባልተቻለ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ከአደጋ ለመጠበቅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በአማራ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ደንግጓል።
የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚያዘው መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ስላልሆነ በ15 ቀናት ውስጥ ለምክር ቤቱ ቀርቦ መጽደቅ አለበት።
አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ
ቢቢሲ የተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ዛሬ ጠዋት ለአካባቢው ነዋሪዎች ደውሎ የነበረ ሲሆን፣ ሁኔታዎች ባለፉት ቀናት ባሉበት መሆናቸውን መረዳት ችሏል።
የክልሉ ርዕሰ ከተማ የሆነችው ባሕር ዳር ያለው የፀጥታ ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑን የገለጹት ቢቢሲ የጠየቃቸው ነዋሪ፣ ምንም የተለየ አንቅስቃሴ አንደሌለ እና መደበኛ ሕይወት ባለበት መቀጠሉን ተናግረዋል።
እንዲሁም በጎንደር ከተማ ያለው የፀጥታ ሁኔታ የተረጋጋ ነው ያሉት የከተማዋ ነዋሪ፣ ነገር ግን በከተማ መውጫ አካባቢ አልፎ አልፎ ተኩስ አንደሚሰማ ገልጸዋል።
በላሊበላም እንዲሁ ምንም ዓይነት ተኩስ የማይሰማ ሲሆን፣ የተለየ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ዛሬ አርብ ጠዋት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ ገልጸዋል።
ባለፉት ቀናት በአማራ ክልል እየተባባሰ የሄደውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የኢንተርኔ አገልግሎት መቋረጡን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት በበርካታ የአማራ አካባቢዎች ያለውን መደበኛ ሕይወት የገታው ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎችም የመንግሥት ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመግታት ወጣቶች መንገዶችን በመዝጋታቸው እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል።
በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ያሳሰባቸው አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያ ዜጎቻቸው ወደ አማራ ክልል እንዳይሄዱ፣ እዚያም ያሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ለመሄድ የሚፈልጉም ምክር እንዲጠይቁ አሳስበዋል።
ካናዳ ዜጎቿ በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ባለችው የፀጥታ ችግር ምክንያት የግድ አስፈላጊ አስካልሆነ ድረስ ወደ አገሪቱ እንዳይጓዙ መክራልች። ያለው የደኅንነት ሁኔታ ያለቅድሚ ማስጠንቀቂያ ወደ አሳሳቢ ደረጃ ሊደርስ ስለሚችል፣ የአማራ ክልልን ጨምሮ ዜጎቿ ወደ በርካታ የኢትዮጵያ ክልሎች ከመጓዝ እንዲቆጠቡ መክራለች።
በአማራ ክልል ያለው ፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆኑን የገለጸው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ዜጎቹ ወደ ክልሉ እንዳይሄዱ መክሯል። በግጭቶች አካባቢ ያሉ ዜጎቹም ስፍራውን ለቀው መውጣት መሞከር ያለባቸው የፀጥታው ሁኔታ ሲሻሻል ብቻ መሆኑን አሳስቧል።
ዩናይትድ ኪንግደምም ዜጎቿ ባለፉት ቀናት እየተስፋፋ የሄደ ግጭት ወደተከሰተበት የአማራ ክልል እንዳይጓዙ መክራለች።
አውስትራሊያ በበኩሏ በመላው አገሪቱ ባለየተቃውሞ እንቅስቃሴ እና የትጥቅ ግጭት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ የሚያደርጉ ዜጎቿ ዕቅዳቸውን እንዲያጤኑት አሳስባለች።