የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ታይተዋል ስለተባሉ ዩፎዎች ምንነት ሪፖርት አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን ለበርካታ ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላትን (ዩፎ) መታየታቸውን በተመለከተ የማጠቃለያ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ።
በተለይ በአውሮፓውያኑ የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር የታዩት እና ዩፎዎች ናቸው ተብለው የተደመደሙት በራሪ ነገሮች የአሜሪካ መንግሥት የሠራቸው የተራቀቁ የስለላ አውሮፕላኖች እና የህዋ ቴክኖሎጂ ሙከራ ውጤቶች ናቸው ብሏል።
የመከላከያ ባለሥልጣናት አክለውም የአሜሪካ መንግሥት ከሌላ ዓለም የመጡ እንግዳ ፍጡራን ማጋጠማቸውን በሚመለከት “ምንም ዓይነት” ማስረጃ የለም ብለዋል።
አርብ ዕለት ለአሜሪካ ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተው ዩፎ ተብለው መታየታቸው ከተገለጹት መካከል አብዛኞቹ ክስተቶች ከምድር ላይ የተነሱ የተለመዱ ነገሮች ናቸው ብሏል።
ነገር ግን የተደረገው ምርመራ ውጤት በሕዝቡ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ዩፎዎችን በተመለከተ ያለውን እምነት በቀላሉ የሚለውጠው እንዳልሆነ የፔንታገን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ሪፖርቱ ባለሥልጣናት “ምንነታቸው ያልታወቁ ያልተለመዱ ክስተቶች” የሚሏቸውን በራሪ አካላትን በተመለከተ ምርመራ በማድረግ ለመገንዘብ በአሜሪካ መንግሥት የተደረገ ሙከራ ነው።
ሪፖርቱ የዩፎዎችን መኖር በተመለከተ በሕዝቡ ውስጥ ጠንካራ እምነት እንዳለ እና ለዚህም ፊልሞች፣ መጻሕፍት፣ ሙዚቃዎች እና ሌሎችም የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ያለውን አመለካከት በቀላሉ መለወጥ አዳጋች ነው ብሏል።
በተለይም በምድር ላይ ተገኝተዋል የተባሉ የበራሪ አካላቱ እና የእንግዳ ፍጡራን ቅሪትን በተመለከተ ተደርገዋል የተባሉ ምርመራዎችን መንግሥት ምሥጢራዊ ማድረጉ ብዙዎች የተደበቀ ነገር እንዳለ እንዲያስቡ አድርጓል እንዳደረገ ተገልጿል።
የፔንታገን ቃል አቀባይ አስካሁን የተደረጉት ሁሉም ምርመራዎች እና ዝርዝር መረጃዎች በአብዛኛው እንግዳ ፍጡራን ወደ ምድር ስለመምጣታቸው የሚያመለክቱ ምንም ማስረጃዎች የሉም በማለት “ታዩ የተባሉት ነገሮችም የተለመዱ ነገሮች እና በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት የመነጩ ናቸው” ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2021 ጋሉፕ ባሰባሰው የሕዝብ አስተያየት ከ40 በመቶ የሚበልጡ አሜሪካውያን ከሌላ ዓለማት የመጡ በራሪ አካላት ምድርን ጎብኝተዋል ብለው እንደሚያስቡ ያመለከተ ሲሆን፣ ይህ የሕዝብ ብዛትም ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረበት 33 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጿል።
ዩፎዎችን በተመለከተ በፔንታገን የተደረገው ምርመራው ከ1945 (እአአ) ጀምሮ ያሉ መዛግብትን እና ምሥጢራዊ ሰነዶችን ጨምሮ በመንግሥት የተደረጉ ይፋዊ ምርመራዎችንም መለስ ብሎ ቃኝቷል።
በርካቶች ዩፎዎች ናቸው ያሏቸው ነገሮች ክብ በራሪ ነገሮችን ሲሆኑ፣ እነዚህ ግን በዚያ ዓይነት ቅርጽ ተሠርተው ሙከራ ሲደረግባቸው የነበሩ አውሮፕላኖች መሆናቸውን ሪፖርቱ በካናዳ የተሠራውን ተመሳሳይ ቦምብ ጣይ አውሮፕላንን በምሳሌነት ጠቅሷል።
ለረጅም ዓመታት የአሜሪካ መንግሥት እነዚህን ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላትን በተመለከተ በርካታ የምርምር ፕሮግራሞችን አካሂዷል፤ ነገር ግን አብዛኞቹ በእንግዳ ፍጡራን ዙሪያ የተደረጉ ምርምሮች በምሥጢር ተይዘው ቆይተዋል።
አሁንም ድረስ በርካቶች እንግዳ ፍጡራን እንዳሉ የሚያምኑ ሲሆን፣ በአንድ ወር ውስጥ ከ50 አስከ 100 የሚደርሱ ዩፎዎችን መታየታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ይቀርባሉ።
መንግሥት እነዚህን ክስተቶች ይደብቃል የሚለው ግምትም አሁንም መቀጠሉን ሪፖርቱ አመልክቷል።
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የቀድሞው የአሜሪካ የስለላ መኮንን ዴቪድ ግሩሽ በአሜሪካ ምክር ቤት ኮሚቴ ፊት ቀርቦ የአሜሪካ መንግሥት የእንግዳ ፍጡራን አካላትን እና በራሪ ነገሮችን ይዞ እንደሚገኝ እንደሚያምን መስክሯል።
ግለሰቡ ይህ እምነቱ እና ለምክር ቤቱ የሰጠው ቃል በሰነዶች ላይ ያሉ መረጃዎችን፣ የድምጽ ቅጂዎችን እና ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ያደረገውን ውይይቶችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን ተናግሮ ነበር።












