ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወታደራዊ ኪሳራ እያጋጠማቸው ያሉት ፑቲን አዳዲሶቹን ግዛቶች በፊርማቸው አጸደቁ
ሩሲያን ተቀላቅለዋል በተባሉት አዳዲስ ግዛቶች በወታደራዊ ዘመቻቸው ኪሳራን እያስተናገዱ ያሉት ፑቲን ከዩክሬን የጠቀለሏቸውን አራት ግዛቶች የሩሲያ አካል መሆናቸውን የተመለከተው ሰነድ ላይ የመጨረሻውን ፊርማ አኑረዋል።
ፑቲን የፈረሙበት ሰንድ ሉዋሃናስክ፥ ዶንቴስክ፥ ዛፖርዚያ እና ኬርሶን የተባሉት የቀድሞ የዩክሬን ግዛቶች “ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር ለመቀላቀል ወስነዋል” የሚል ነው።
ሆኖም ዩክሬን በሁለቱ ግዛቶች [ሉዋሃናስክ እና ኬርሶን] ስር ያሉ መንደሮችን መልሼ መቆጣጠር ችያለሁ ብላለች።
በተጨማሪም ፑቲን በዛፖርዚያ ግዛት ያለውን የኒውክሌር ጣቢያ ሩሲያ እንደወረሰችው የሚገልጽ አዋጅንም በፊርማቸው አጽድቀዋል።
ባለፈው አርብ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቢሯቸው በተካሄድ ስነሰርዓት ላይ በሞስኮ በተሾሙ ከአራቱ አዳዲስ ግዛቶች መሪዎች ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይህ መርሃግብር የተዘጋጀው በአራቱ ግዛቶች ህዝበ ውሳኔ ተካሂዷል መባሉን ተከትሎ ሲሆን ይህንን ውሳኔ በምዕራባውያን ሀገራት “አሳፋሪ’ ነው ተብሏል።
የዩክሬን ሃይሎች ግን በደቡብ እና ምስራቅ የጦር አውዶች ወታደራዊ የበላይነት እያእመዘገቡ ነው።
በዩክሬን ሉዋሃናስክ ግዛት አስተዳዳሪ ሴሪ ሃይዲ ለቢቢሲ ሲነገሩ ትላንት እሮብ የሀገራቸው ጦር ስድስት መንደሮችን ማስለቀቁን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ቆየት ብለው በሰጡት አስተያየት ዩክሬን ተጨማሪ ሶስት መንደሮችን ነጻ ማውጣቷን ገልጸዋል።
የዩክሬን ሃይሎች ከዚህም ቀደም ብለው ዳቪዲቭ የተሰኘቸውን መንድር መቆጣጠርን ጨምሮ ተከታታይ ድል አግኝቷል።
በሌላ በኩል በደቡባዊቷ ዛፖርዚያ ታላቅ ፍንዳታ መሰማቱ የተነገረ ሲሆን የአከባቢው አስተዳዳሪዎች ሰባት የሩሲያ ሚሳኤሎች የመኖሪያ መንደሮችን ደብደበው ነዋሪዎች ፍርስራሾች ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በአባባቢው ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን የወጣው መረጃ የለም።
የፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዩክሬን ተሸንፋ የምትለቀውን ማንኛውም ግዛት መልሳ ትይዛለች ብለዋል።
በአዳዲሶቹ ግዛቶች ሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ሽንፈት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እስከመጨረሻው ከሩሲያ ጋር ይቆያሉ። ይመላሳሉ” ብለዋል።
በመምህራን ቀን ለመመህራን ንግግር ያደረጉት ፑቲን አዳዲሶቹን ግዛቶች “በተረጋጋ መንገድ ይበለጽጋሉ” ሲሉ ገልጸዋል።