በአሜሪካ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ የመጀመሪያ ናቸው የተባሉ ሁለት ልጆች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ውስጥ በሕጻናት ላይ የመጀመሪያ የሆኑ ሁለት በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ልጆች መገኘታቸውን የጤና ባለሥልጣናት አሰታወቁ።
በሽታው በአገሪቱ ውስጥ እየተስፋፋ ነው እየተባለ ባለበት በአሁኑ ወቅት በበሽታው የተያዙት ሁለቱ ሕጻናት የተገኙት ካሊፎርኒያ ውስጥ ነዋሪ በሆነ እና በሌላ በዋሽንግተን በኩል ሊያልፍ የነበረ የአገሪቱ ዜጋ ባልሆነ ልጅ ላይ ነው።
የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) እንዳለው ሁለቱ ሕጻናት በአሁኑ ጊዜ “በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው።”
ከስምንት ዓመት በታች ባሉ ሕጻናት ላይ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ማዕከሉ ጨምሮ አመልክቷል።
በመላዋ ዩናይትድ ስቴትስ እስካሁን ድረስ ከ2,500 በላይ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸው ተገልጿል።
አብዛኞቹ የዚህ በሽታ ክስተት የተመዘገበው በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች መካከል ነው ተብሏል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ ነው ተብሎ የተለየ አይደለም። በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር በሚኖር የቀረበ ንክኪ እንደሚተላለፍ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቫይረሱ በጣም የሚያሳክክ እና ህምም ያለው ሽፍታ እና ቁስለትን የሚያስከትል ሲሆን በመላው አካል ላይ በመስፋፋት ሌሎች ውስብስብ የጤና ችግሮችን ያስከትላል።
በሽታው በአዋቂ ሰዎች ላይ ምንም አይነት ህክምናም ሆነ ሆስፒታል መግባት ሳያስፈልግ በራሱ ጊዜ የሚድን ሲሆን፣ ነገር ግን በታዳጊ ሕጻናት ላይ ግን እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።
ቫይረሱ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ጤና አደጋ እንደሆነ ለመወሰን በዚህ ሳምንት ስብሰባ ማድረግ ጀምሯል።
በሽታው በአሜሪካ ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱ በግብረ ሥጋ እንደ 'ሚተላለፉ ሌሎች የአባለዘር በሽታዎች እንዲታይ ሊያደርገው ይችላል እየተባለ ነው።
የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት ይህ በሽታ ወደ ወረርሽኝ ሊሰፋ እንደሚችልና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።












