አሜሪካ በግዛቶቿ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት ልታከፋፍል ነው

በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዋይት ሀውስ የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመቆጣጠር በሺዎች የሚቆጠሩ ክትባቶች በአሜሪካ ግዛቶች እንደሚያከፋፍል አስታወቀ።

ምርመራ የሚያካሂዱና ክትባቱን የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምርም ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም አፍሪካ ውስጥ በመሰራጨት የሚታወቀው ቫይረሱ በአሜሪካ እና በአውሮፓ በፍጥነት እየተሰራጨ ይገኛል።

በአሜሪካ እስካሁን 306 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። የሞተ ሰው ግን የለም።

የአገሪቱ የጤና ባለሥልጣኖች እንዳሉት፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በይፋ ከተነገረውም በላይ ሊሆን ይችላል።

ካለፈው ወር ጀምሮ በ49 አገራት 4,700 ኬዞች ተመዝግበዋል።

ለዝንጀሮ ፈንጣጣ የመጋለጥ ዕድል ያላቸው ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ የአሜሪካ ፌደራል መንግሥት አሳስቧል።

ከዚህ ቀደም ክትባቱን እንዲወስዱ የሚመከሩ ሰዎች በቀጥታ ለቫይረሱ ተጋላጭነት እንዳላቸው የተረጋገጠ ሰዎች ነበሩ።

አሁን ግን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ወንዶች እና ቫይረሱ በተገኘባቸው ከተሞች ከሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ወይም ወሲብ የፈጸሙም ክትባቱን እንዲወስዱ ተመክሯል።

እስካሁን ድረስ አሜሪካ ውስጥ የተገኙት ኬዞች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ወንዶች ቢሆኑም፣ ማንኛውም ሰው በበሽታው ሊያዝ እንደሚችል ተገልጿል።

በሽታው የተስፋፋበት ይህ ወቅት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን የሚዘክረው ‘ፕራይድ መንዝ’ በተከበረበት ወቅት ነው።

የአሜሪካ የጤና አገልግሎት ክፍል 56,000 ክትባቶችን እንደሚያከፋፍል አስታውቋል። ክትባቶቹ ባቫሪያን ኖርዲክ በተባለው ተቋም የተመረቱና ጂኖስ የተባሉ ናቸው።

አሜሪካ 64,000 የጂኖስ ክትባት ቢኖራትም ተጨማሪ ክትባት እንዲመጣ አዛለች።

በቀጣይ ወራት በአገሪቱ 1.25 ሚሊዮን ክትባቶች የማስገባት ዕቅድ አለ።

ይህ ክትባት አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ በኋላ በሽታውን ለማከም ይውላል።

ኤካም2000 የተባለ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ክትባትም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል።

በሳምንቱ መባቻ ኒው ዮርክ እና ዋሽንግተን ክትባቱን ማሰራጨት ቢጀምሩም በአጭር ጊዜ አልቆባቸዋል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ባይሆንም፣ በቆዳ ንክኪ፣ በልብስ፣ በደም እና በመሳሰሉት ሊሰራጭ ይችላል።

በሰውነት ላይ የሚያስከትለው ጠባሳ ከ14 እስከ 21 ቀናት ይሽራል።