አደገኛ ጉዳትን የሚያስከትለው የሴቶች የዐይን ሽፋሽፍት መቀጠል

የዓይን ሽፋሽፍት በተፈጥሯዊ ይዞታው ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በዐይን በኩል የሚገባ አደገኛ ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶችን ይከላከላል።

እነዚህ ጎጂ ነገሮች ወደ ዐይን ብሌን ዘልቀው እንዳይገቡ የሚከላከለው ሽፋሽፍት ነው።

የዐይን ሽፋሽፍት በመርገብገብ ሂደት ውስጥ በዐይን ዙሪያ የሚንሳፈፉ አደገኛ ነገሮችን ወደ ዐይን እንዳይገቡ ያግዳል። በተጨማሪም ዐይን ፈሳሽ እንዲኖረው በማድረግ ድርቀት እንዳይፈጠርም ያደርጋል።

የዐይን ሽፋሽፍትን በሰው ሠራሽ መንገድ ለማስረዘም የሚደረግ ሂደት (Eyelash extensions) በተፈጥሯዊ የዓይን ሽፋሽፍት ላይ ተጨማሪ ሰው ሠራሽ የዓይን ሽፋሽፍቶችን መጨመርን የሚያካትት ነው።

ሰው ሠራሽ የዐይን ሽፋሽፍቶች እንደ ክር፣ የፈረስ ጭራ እና ፕላስቲክን ከመሳሰሉ ግብዐቶች ይሠራል።

የዓይን ሽፋሽፍከመተከሉ በፊት በክንድ ላይ ወይም ከጆሮ ጀርባ የማጣበቂያው ሙከራ ይደረጋል። ይህም ሰው ሠራሽ ቅንድቡ ሲተከል ጥቅም ላይ የሚውለው ማጣበቂያ በተጠቃሚዋ ላይ አለርጂ እንደማያስከትል ለመሞከር ነው።

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍትን ለማጣበቅ የሚውሉት ኬሚካሎች ለዐይን ጎጂ ናቸው። ኬሚካሎቹ ዐይን ላይ ከባድ ጫናም ያሳድራሉ።

በዚህም ሳቢያ ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ሲያስተክሉ ቅንድባቸው የተጣበቀባቸው ተጣብቆ ለጉዳት የተዳረጉ ሴቶች እንዳሉ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ሌሎችም ተጨማሪ የጤና እክሎች ሪፖርት ተደርገዋል።

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ሲተከል የዐይን ብሌን ጋር መጠጋት የለበትም።

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ከዐይናቸው ጋር ከተነካካ በኋላ የዐይን ብሌን መለብለብ (keratoconjunctivitis) እንደገጠማቸው ከ60 በመቶ በላይ ሴቶች ገልጸዋል።

ቅንድቡን ለማጣበቅ የሚውለው ኬሚካል የአለርጂ ችግር እንዳስከተለባቸው 40 በመቶ ሴቶች ተናግረዋል።

ጥፍር ለማጣበቅ የሚውል ሙጫ ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍትን ለማጣበቅ ሲውልም ይስተዋላል።

አንዲት ሴት በጣም ጠንካራ የሆነ ሙጫ በመጠቀም ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ለማጣበቅ ስትሞክር ተፈጥሯዊ ቅንድቧ ተጣብቆ ቀርቷል።

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍትን ለማጣበቅ የሚውለው ኬሚካል

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍትን ለማጣበቅ የሚውለው ኬሚካል ፎርማልዲሃይድ (formaldehyde) ይባላል። ይህም ለካንሰር ከሚያጋልጡ ኬሚካሎች አንዱ ነው።

አንድ ጥናት 37 ለንግድ እና ለሙያዊ አገልግሎት የተሠሩ ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ማጣበቂያዎችን ዳስሶ ለጤና አደገኛ ውጤት እንዳላቸው ደርሶበታል።

ለሙያዊ አገልግሎት ከተሠሩ 20 ማጣበቂያዎች መካከል 75 በመቶ ያህሉ ለካንሰር የሚያጋልጠው ኬሚካል ተገኝቶባቸዋል። ለንግድ ከሚውሉ 17 ማጣበቂያዎች መካከል በአራቱ ውስጥ ኬሚካሉ ተገኝቷል።

ከእነዚህ ማጣበቂያዎች መካከል ደግሞ ይህ አደገኛ ኬሚካል በውስጣቸው እንደሚገኝ ለተጠቃሚዎች በይፋ ያልገለጹ ይገኙበታል።

ይህ የሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ማጣበቂያ በሚጠቀሙት ሴቶች የዐይን ብሌን ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ዕይታን እስከማወክ ሊደርስ ይችላል።

በዋነኛነት ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ከማስተከል ጋር በተያያዘ የሚነሳው የጤና ጉዳት ብሌፋሪቲስ (blepharitis) ይባላል። ይህም የዐይን ሽፋሽፍት እብጠት እና መለብለብን የሚያስከትል ከባድ ችግር ነው።

በዐይን ጫፍ ላይ ያሉ ተፈጥሯዊ ኬሚካል አመንጪ ክፍሎች ዐይን ውስጥ ባክቴሪያዎች እንዳይጠራቀሙ የሚከላከለውን ንጥረ ነገር በማመንጨት ይለቃሉ። ይህ የዐይን ክፍል ሽፋሽፍት የሚበቅልበትም ቦታ ነው።

በተፈጥሯዊ የዐይን ሽፋሽፍት ላይ የሚደረጉ ሰው ሠራሽ ለውጦች እነዚህ ኬሚካሎች ቀንሰው ባክቴሪያ እንዲከማች መንገድ ይከፍታሉ።

ባክቴሪያ ዐይን ላይ ሲከማች በዐይን ሽፋሽፍት ላይ ስታይስ (styes) የተባለ እብጠት እና ቁስለትን በማስከተል አሳሳቢ የጤና እክል እንዲፈጠር ያደርጋል።

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ሲተከል ንጽህናው በጎደለ ስፍራ እና መገልገያ ከተከናወነ ደግሞ ነፍሳት ዐይን ላይ እንዲከማቹም ዕድል ይፈጠራል።

በተለይም ዴሞዴክስ (demodex) በመባል የሚታወቁት ነፍሳት በዐይን ዙርያ ይሰባሰባሉ። ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ሲተከል ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፉም ይችላሉ።

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ሲነሳም በተገቢው ሙያተኞች ቢካሄድ እንኳን ተፈጥሯዊ ሽፋሽፍት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

ሽፋሽፍት ለማስረዘም የሚውሉ ኬሚካሎች

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ከማስተከል ይልቅ ሽፋሽፍት እንዲረዝም የሚረዱ ኬሚካሎች (eyelash serums) የሚጠቀሙም አሉ።

ሽፋሽፍትን የሚያረዝሙ፣ የሚያወፍሩ ወይም የሚያጠቁሩት እነዚህ ኬሚካሎች ሰውነት ላይ የተለያየ ጉዳት የሚያደርስ ንጥረ ነገር (prostaglandin) በውስጣቸው ይዘዋል።

በዐይን ውስጥ የፈሳሽ ክምችት ግላኮማ ሲያስከትል ለማከም የሚውሉ ንጥረ ነገሮች ናቸው። ታካሚዎች ረዥም፣ ወፍራም እና ጥቁር ሽፋሽፍት እንዲኖራቸው ሲያደርጉም ተስተውለዋል።

ሆኖም ግን የጤና እክል ያስከትላሉ።

የዐይን ሕዋስን በመጉዳት ቀለሙን እንዲለውጥ ያደርጋሉ። በዐይን ዙሪያ የሚፈጠረውንም ጥቁረት ያባብሳሉ።

ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት ለማስቀጠል ንጽሕናው የተጠበቀ አገልግሎት ሰጪ ጋር መሄድ የግድ ነው።

ተፈጥሯዊ ሽፋሽፍት ያላቸው ሰዎች ሰው ሠራሽ ሽፋሽፍት አዘውትረው ባያስተክሉ በማለት ባለሙያዎች ይመከራል።