ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዳዲሶቹ ፍለርት የኮቪድ-19 ዝርያዎች ምን ያህል አሳሳቢ ናቸው?
ከጥቂት ዓመታት በፊት መላውን ዓለም አዳርሶ ሚሊዮኖችን በመያዝ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለሞት የዳረገው ኮቪድ 19 ጉዳቱ ቢቀንስም አሁንም የሰው ልጅ የጤና ስጋት መሆኑ አላበቃም።
ይህ በትንፋሽ የሚተላለፈው ቫይረስ ባለፉት ዓመታት ዝርያውን እና የጉዳት አቅሙን እየቀያየረ ይገኛል። አሁን ደግሞ የቫይረሱ አዲስ አይነት ዝርያ መገኘቱ እየተነገረ ነው።
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ ፍለርት (FliRT) የሚል ስም የተሰጣቸው አዲስ ዝርያዎች በዓለም ላይ በጣም ዋናዎቹ የኮቪድ-19 ዝርያዎች ሆነዋል። በዚህ ዙሪያ ማወቅ የሚገባዎትን መረጃ አጠናቅረናል።
አዳዲሶቹ የኮቪድ ዝርያዎች ምንድናቸው?
ፍለርት ለአዲሶቹ የኮቪድ ቫይረስ ዝርያዎች ይፋዊ ያልሆነ ቅጽል ስም ነው። ይህም በቫይረሱ ዘረመል ውስጥ ካሉ ለውጦች የተገኘ ስም ነው።እነዚህም ጄንጄ.1 (JN.1) የተባሉት ዝርያዎች ስብስብ ናቸው። የተገኙትም ኦሚክሮን ከተሰኘው የኮቪድ ዝርያ ልውጦች ነው።
በፕሮቲናቸው ላይ ሦስት ቁልፍ ልውጦች ስላላቸው የሰውነተን በሽታ የመላከል ሥርዓትን እንዲያመልጡ ሊረዳቸው ይችላል ሲል ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ገልጿል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጤና ጥበቃ ኤጀንሲ በበኩሉ ምን ያህል ከባድ እና ተላላፊ መሆናቸውን ለመረዳት በአዲሶቹ ዝርያዎች ላይ “ተጨማሪ መረጃ” እንደሚያስፈልገው ተናግሯል። በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እየተላለፉ ካሉ ሌሎች ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸር ከባድ ስለመሆኑ ምንም ማስረጃ የለም ሲል አክሏል።
የኮቪድ ጉዳዮች እየጨመሩ ነው?
በኮቪድ ዙሪያ እስካሁንም ተከታታይ ሪፖርት የሚያቀርቡ አገራት አሉ። እነዚህን ሪፖርቶች ተንተርሶ ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ከሚያዝያ እስከ ግንቦት ድረስ የተመዘገቡ ቁጥሮችን ተመልክቷል። የተገኘው የበሽታው ሃዝ ቀደም ካለው ወር አንጻር ቀንሷል።
የኮቪድ ምርመራ እና ሪፖርት የማድረግ ሥራው እንደበፊቱ አለመሆኑ ትክክለኛውን ምሥል ለማግኘት ከባድ ያደርገዋል።
በአንዳንድ አገሮች ግን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ተዘግቧል። የብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል “በግንቦት እና በሰኔ ወራት እንግሊዝ ውስጥ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል” ብሏል።
“በሌሎች የአውሮፓ ክፍሎችም በኮቪድ ተያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።”
“በአሜሪካም በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። በሰኔ ወር ሦስተኛ ሳምንት በምርመራው ቫይረሱ እንዳለባቸው ያወቁ ሰዎች ቁጥር በ1.4 በመቶ ከፍ ብሏል።”
የኮቪድ ክስተት ቁጥር ዓመቱን በሙሉ ከፍ እና ዝቅ ይላል። ይህ አሳሳቢ ላይሆን ቢችልም ግን የጤና ባለሙያዎች የሚያዙ ሰዎችን በተከታታይ ይቆጣጠራሉ።
የፍለርት ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?
የዚህ አዲሱ የኮቪድ በሽታ ምልክቶች ከከዚህ ቀደም ከነበሩት ሌሎች የኮቪድ-19 ዓይነቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት “ብዙውን ጊዜ ሰዎች ለቫይረሱ ከተጋለጡ ከ5 እስከ 6 ቀናት ውስጥ ምልክቶቹ መታየት የሚጀምሩ ሲሆን፣ ከ1 እስከ 14 ቀናት የሚቆዩ ናቸው” ብሏል።
በጣም የተለመዱት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡
- ትኩሳት
- ብርድ ብርድ ማለት
- ጉሮሮ ህመም
ብዙም ያልተለመዱት ምልክቶቹ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡
- የጡንቻ ህመም እና የእጆች ወይም የእግሮች መክበድ ስሜት
- ከባድ ድካም
- የአፍንጫ ፍሳሽ መኖር ወይም መዘጋት ወይም ማስነጠስ
- ራስ ምታት
- የዐይን ህመም
- መፍዘዝ
- አዲስ እና የማያቋርጥ ሳል
- በደረት ላይ ድርቅ የማለት ስሜት ወይም የደረት ሕመም
- ትንፋሽ ማጠር
- የድምጽ መጎርነን
- የመፍሰዝ ወይም የመደንዘዝ ስሜት
- የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ የሆድ ህመም ወይም ተቅማጥ
- ጣዕም ወይም የማሽተት ስሜት መጥፋት ወይም መለወጥ
- የእንቅልፍ ችግር
የዓለም ጤና ድርጅት የሚከተሉትን ምልክቶች የሚያሳዩ ሰዎች አፋጣኝ የሕክምና ክትትል እንዲያደርጉ ይመክራል።
- የመተንፈስ ችግር፤ በተለይም ትንፋሽ ቁርጥ ቁርጥ ማለት
- መፍዘዝ ወይም ግራ መጋባት
- እንቅልፍ ማጣት ወይም ትኩረት ማጣት
- የደረት የማያቋርጥ ህመም ወይም ግፊት
- የቆዳ መቀዝቀዝ ወይም ወደ መገርጣት ወይም ወደ ሰማያዊ ቀለም መለወጥ
- የመናገ ወይም የእንቅስቃሴ ችግር
አሁን ያሉት ክትባቶች ለፍለርት ዝርያዎች ይሠራሉ?
አሁን ያሉት ክትባቶች በአዳዲሶቹ ዝርያዎች ላይ የተወሰነ ጥቅም ሊኖራቸው ይችላል ሲሉ በኒው ዮርክ የሚገኘው የማውንት ሲናይ ሳውዝ ናሶ ሆስፒታል የተላላፊ በሽታዎች ኃላፊ እና የአሜሪካ ተላላፊ በሽታዎች ማኅበር ቃል አቀባይ የሆኑት ዶክተር አሮን ግላት ተናግረዋል።
ከ2022 ጀምሮ የጤና ተቆጣጣሪዎች የክትባት አምራቾችን አዳዲስ በስፋት የሚሰራጩ የኮቪድ-19 ዝርያዎችን ከግምት በማስገባት ክትባቶችን እንዲያዘጋጁ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ተቆጣጣሪ ክትባት ሠሪዎች የጄኤን.1 ዝርያ ላይ ማነጣጠር አለባቸው ብሏል።
የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎችም ክትባቶቹ በጄኤን.1 ውስጥ ያሉ ዝርያዎች ላይ እንዲያነጣጥሩ ጠይቀዋል። ዒላማ እንዲያደርጉ የመረጡት ደግሞ የኬፒ.2 የተባለው እና በሰኔ ወር በስፋት ሲሠራጭ በነበረው ዝርያ ላይ ነው።