ራሳችንን የጉበት በሽታ ከሆነው ሄፒታይትስ እንዴት መከላከል እንችላለን?

በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሄፒታይትስ በሽታ እንዳለባቸው ስለማያውቁ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የጤና ኃላፊዎች እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ሐምሌ 21 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሄፒታይትስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት መልዕክት ነው።

ሄፒታይትስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች ሞት ምክንያት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል።

ሄፒታይትስ ምንድን ነው? ምን ያህልስ ገዳይ ነው?

የሄፒታይትስ በሽታ በጉበት ላይ የሚከሰት ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በቫይረስ የሚመጣ ነው።

የጉበት ካንሰር፣ የጉበት ሥራ ማቆም እና ሌሎች በርካታ የጉበት በሽታዎችንም ሊያስከትል ይችላል።

ከኤ እስከ ኢ ድረስ ተሰየሙ አምስት ዓይነት የሄፒታይትስ የቫይረሱ ዓይነቶች አሉ።

ሄፒታይትስ ቢ እና ሲ በጣም ጎጂ የሚባሉት ናቸው። እንደ ዓለም የጤና ድርጅት ግምት ከሆነ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 1.3 ሚሊዮን በሁለቱ የሄፒታይትስ ዓይነቶች ይሞታሉ። ይህም በየ30 ሰከንድ አንድ ሰው ይሞታል እንደማለት ነው።

ሄፒታይትስ ምን ያህል ተስፋፍቷል?

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ 254 ሚሊዮን ሰዎች ሥር ከሰደደ የሄፒታይትስ ቢ እንዲሁም 50 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ሥር ከሰደደ የሄፒታይትስ ሲ ጋር አብረው እንደሚኖሩ ገልጿል። በየዓመቱም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ይያዛሉ ብሏል።

የሄፒታይትስ ቢ ሥርጭትን በተመለከተም፡

  • በዓለም የጤና ድርጅት ምዕራባዊ ፓስፊክ ክልል (ቻይና፣ ጃፓን እና አውስትራሊያን ይጨምራል) ሥር በሰደደ በሽታ የተያዙ 97 ሚሊዮን ሰዎች አሉ
  • በአፍሪካ ውስጥ 65 ሚሊዮን ሰዎች
  • 61 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ደቡብ-ምሥራቅ እስያ ክልል (ሕንድ፣ ታይላንድ እና ኢንዶኔዢያን ጨምሮ) ይገኛሉ

የዓለም ጤና ድርጅት አክሎም ሄፒታይትስ ኢ በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ 20 ሚሊየን ሰዎችን ያጠቃል። በ2015 (አአአ) ብቻ የ44 ሺህ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ይህም በደቡብ እና ምሥራቅ እስያ የተስፋፋ የሄፒታይትስ ዓይነት ነው።

ሄፒታይትስ እንዴት ይይዛል?

ሄፒታይትስ ኤ በአብዛኛው የሚይዘው በምግብ ወይም በመጠጣት ወይም በዐይነ ምድር በተበከለ ውሃ ወይም ደግሞ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በቀጥታ በመገናኘት ነው።

ደካማ የንፅህና አጠባበቅ ባለባቸው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች በብዛት ይገኛል።

ምልክቶቹ ብዙም ሳይቆዩ ይጠፋሉ። ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ ከበሽታው ያገግማል። ሆኖም ለሞት የሚዳርግ የጉበት አለመሥራት ሊያስከትል ይችላል።

ሄፒታይትስ ኤ የተበከለ ምግብ ወይም ውሃ ባለባቸው ቦታዎች በወረርሽኝ መልክ የመቀስቀስ አዝማሚያ አለው። ለምሳሌ በቻይናዋ ሻንጋይ እአአ በ1998 ብቻ 300 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

ሄፒታይትስ ቢ በብዛት የሚተላለፈው፡

  • በወሊድ ወቅት ከእናት ወደ ልጅ
  • በንክኪ ደግሞ ከልጅ ወደ ልጅ
  • ከተበከሉ መርፌዎች፣ ንቅሳት ሲሠራ፣ እንደ ጆሮ መበሳት ያሉት ሲከናወኑ ወይም በተበከለ ደም እና የሰውነት ፈሳሽ (ለምሳሌ በወሲብ ወቅት) ይተላለፋል።

ሄፒታይትስ ሲ እና ዲ የሚተላለፉት ከተበከለ ደም ጋር ንክኪ ሲኖር ነው። ለምሳሌ መርፌ በመጋራት ወይም የተበከለ ደም በመውሰድ ነው።

ሄፒታይትስ ቢ ያለባቸው ሰዎች ብቻ በሄፒታይትስ ዲ ይያዛሉ። ይህ የሚከሰተው ሥር የሰደደ ሄፒታይትስ ቢ ካላቸው 5 በመቶ ያህሉ ላይ የሚከሰት እና ለከባድ ህመም ሊዳርጋቸው ይችላል።

ሄፒታይትስ ኢ የተበከለ ምግብ ከመብላት እና ውሃ ከመጠጣት ይመጣል። በደቡብ እና በምሥራቅ እስያ በጣም የተለመደ ሲሆን፣ በተለይ ለነፍሰ ጡር ሴቶች ጎጂ ሊሆን ይችላል።

ሄፒታይትስ እንዳለበዎ እንዴት ማወቅ ይችላሉ?

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት ከሆነ የሄፒታይትስ ምልክቶች የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፡

  • ትኩሳት
  • ድካም
  • የምግብ ፍላጎት ማጣት
  • ተቅማጥ
  • ማቅለሽለሽ
  • በሆድ አካባቢ የሚኖር ህመም
  • ጥቁር ቀለም ያለው ሽንት እና ዐይነ ምድር
  • መገርጣት (የቆዳ ቢጫ እና የዐይን ነጭ መሆን)

ይሁን እንጂ ሄፒታይትስ ያለባቸው ብዙ ሰዎች ቀላል ወይም ምንም ምልክት አያሳዩም።

በ2022 የወጣው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በዓለም ዙሪያ ሥር የሰደደ ሄፒታይትስ ቢ ካለባቸው ሰዎች መካከል 13 በመቶዎቹ እና ሥር የሰደደ ሄፓታይተስ ሲ ካለባቸው ሰዎች ደግሞ 36 በመቶዎቹ ብቻ ህክምና አግኝተዋል።

አስጊው ነገር ሳያውቁ በሽታውን ሊያስተላለፉ መቻላቸው ነው። ለዚህም ነው የዓለም ጤና ድርጅት እና የህክምና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰዎች እንዲመረመሩ የሚያሳስቡት።

የሄፒታይትስ ምርመራ እና ሕክምና አለው?

ለሄፒታይትስ ኤ፣ ቢ እና ሲ የደም ምርመራ ማድረግ ይችላሉ።

ለሄፒታይትስ ኤ የተለየ ህክምና የለም። ነገር ግን አብዛኞቹ በሽታው ያለባቸው ሰዎች በፍጥነት ከመዳናቸውም በላይ የበሽታውን መከላከያ ያዳብራሉ።

ሥር የሰደደ የሄፒታይትስ ቢ እና ሄፒታይትስ ሲ በፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ሊታከሙ ይችላሉ። ይህም የሲሮሲስን ዕድገትን ከመቀነስ ባለፈ በጉበት ካንሰር የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል።

የሄፒታይትስ ኤ እና ቢ መከላከያ ክትባቶች አሏቸው። ለጨቅላ ህጻናት ሲወለዱ የሚሰጠው የሄፒታይትስ ቢ ክትባት በሽታው ከእናቶቻቸው እንዳይተላለፍ ከመከላከል ባለፈ ሄፒታይትስ ዲ'ንም ይከላከላል።

ለሄፒታይትስ ሲ ክትባት የለም። የሄፒታይትስ ኢ ክትባት ደግሞ በስፋት አይገኝም።

ሄፒታይትስን እንዴት ማስወገድ ይቻላል?

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት ከሆነ የሄፒታይትስ ኤ ሥርጭትን በሚከተሉት መንገዶች መከላከል ይቻላል፡

  • ከምግብ በፊት እና ወደ መጸዳጃ ቤት ከሄዱ በኋላ አዘውትሮ እጅን መታጠብ
  • በቂ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማግኘት
  • የፍሳሽ ቆሻሻን በተገቢው መንገድ ማስወገድ

የዓለም የጤና ድርጅት ሄፒታይትስ ቢ፣ ሲ እና ዲ'ን በሚከተሉት መንገዶች በተሻለ መንገድ ማስወገድ ይችላሉ ይላል፡

  • ደኅንነቱ የተጠበቀ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ፣ ኮንዶም መጠቀም እና የወሲብ አጋሮችን ቁጥር መቀነስ
  • ለአደንዛዥ ዕፅ፣ ለመበሳት ወይም ለንቅሳት በሚል መርፌዎችን አለመጋራት
  • ለሄፒታይትስ ቢ ከደም፣ ከሰውነት ፈሳሾች ወይም ከተበከሉ ነገሮች ጋር ንክኪ ከተፈጠረ በኋላ እጅን መታጠብ
  • ለሄፒታይትስ ቢ ድግሞ ክትባት መውሰድ። ትልቅ ከሆኑ እና በጤና ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ከሆነም ክትባቱን መውሰድ። ምክንያቱም በተወለዱበት ጊዜ የሚሰጠው ክትባት ለ20 ዓመታት ብቻ ሊቆይ ይችላል።

ሄፒታይትስ ኢ'ን በጥሩ ንፅህና አጠባበቅ እንዲሁም ከመመገብ በፊት የእንስሳትን (በተለይም የአሳማ) ጉበትን በደንብ በማብሰል መከላከል ይቻላል።

ሄፒታይትስን ለማስወገድ ምን እየተሞከረ ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት እአአ በ2030 በሄፒታይትስ ቢ እና ሲ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በ90 በመቶ መቀነስ እና የሚሞቱትን ሰዎች ቁጥር ደግሞ በ65 በመቶ መቀነስ እንደሚፈልግ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ በሄፒታይትስ ቫይረሶች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል። እአአ በ2019 በዓለም ዙሪያ 1.1 ሚሊዮን የነበረው የሟቾች ቁጥር በ2022 ወደ 1.3 ሚሊዮን ማደጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዓለም ዙሪያ ካሉ አገሮች 60 በመቶ ያህሉ ብቻ ነፃ ወይም በድጎማ ምርመራ እና ሕክምና ስለሚሰጡ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሄፒታይትስ ምርመራ ማድረግ ከባድ ሆኖባቸዋል። አፍሪካ ውስጥ ይህንን የሚያቀርቡት አገራት አንድ ሦስተኛው ብቻ ናቸው።