42 ሴቶች መግደሉን አምኗል የተባለው ተጠርጣሪ ቃሉን የሰጠው በፖሊስ ስቃይ ተፈጽሞበት ነው ተባለ

በርካታ ሴቶችን ገድሏል የተባለው ኬንያዊ ተጠርጣሪ ቃሉን የሰጠው በፖሊስ ስቃይ ከደረሰበት በኋላ መሆኑን ጠበቃው ተናገሩ።

ከሁለት ቀናት በፊት የኬንያ ፖሊስ የ33 ዓመቱ ኮሊንስ ካሃሉሻ ከእአአ 2022 ጀምሮ ባለቤቱን ጨምሮ 42 ሴቶቸን መግደሉን አምኗል ሲል መግለጫ ሰጥቶ ነበር።

ፖሊስ የዚህን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋል የገለጸው ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ የበርካታ ሴቶች የተቆራረጡ አካላት በማዳበሪያ ተጥሎ መገኘቱን ተከትሎ ነበር።

ይህ የሴቶች አካላት ተጥሎ መገኘት ኬንያውያንን ያስቆጣ ሲሆን፣ ተጠርጣሪው 42 ሴቶችን ገድያለሁ የማለቱ ዜናም እንዲሁ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት በቀረበ ወቅት የእምነት ቃሉን የሰጠው በፖሊስ ድብደባ መሆኑ ገልጿል።

የተጠርጣሪው ጠበቃ ጆን ዴንግዋ ደንበኛቸው ቃሉን የሰጠው በፖሊስ አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞበት መሆኑን ተናግረው በጫና ስር ሆኖ የሰጠው ቃል በፍርድ ቤት መዝገብ እንደማይመዘገብ ተስፋ አለኝ ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግ ግን ተጠርጣሪው አካላዊ ጥቃት ደርሶበታል የሚለውን አቤቱታ አስተባብሏል።

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው ለአራት ሳምንታት በቁጥጥር ስር ሆኖ ፖሊስ ምርመራውን እንዲቀጥል ወስኗል።

ከፍርድ ቤት ውሎ በኋላ ጠበቃው “ወንጀሉን እንደፈጸመ እንዲያምን አንቀውት ነበር። ከፍተኛ ፍርሃት እና ጫና ውስጥ እንደነበረ በግልጽ መመልከት ይቻላል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃው ጨምረው ደንበኛቸው ለአስቸኳይ ሕክምና ወደ ሆስፒታል እንዲወሰድ ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው እሁድ ሐምሌ 7 በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜን እየተመለከተ ሳለ ነበር በፖሊስ የተያዘው።

ከዚያም ተጠርጣሪው ፖሊሶችን ወደ መኖሪያ ቤቱ ከመራ በኋላ በቤቱ 10 ስልኮች፣ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር፣ መታወቂያ ካርዶች እና የሴቶች ልብሶች ማገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፖሊስ ከተጠርጣሪው ቤት ለወንጀል ድርጊት ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበሩ ያላቸው ገጀራ፣ ጓንት እና ከረጢቶች ማግኘቱን አስታውቋል።

ፖሊስ በመዲናዋ ናይሮቢ የሴቶች አስክሬን ተጥሎ የተገኘበትን ቆሻሻ መጠያ ስፍራ ከልሎ ምርመራ እያደረገ ይገኛል።

እንደ ፖሊስ ከሆነ በቆሻሻ ስፍራው እስካሁን ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 የሆኑ ሴቶች አስክሬንን መሰብሰቡን አስታውቆ፤ ሁሉም ሴቶች በተመሳሳይ ሁኔታ የተገደሉ ናቸው ብሏል።

የሴቶቹ ግድያ ኬንያውያንን ከማስደንገጡ በተጨማሪ በፖሊስ ላይ ቁጣን አስነስቷል። የተጠርጣሪው መኖሪያ እና የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በአካባቢው ካለ ፖሊስ ጣቢያ በቅርብ ርቀት ሆኖ ሳለ ተጠርጣሪው ሳይያዝ እንዴት ቆየ የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪም አንዳንዶች በሴቶቹ ግድያ ውስጥ የመንግሥት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም የሚል መላ ምት እየሰጡ ይገኛሉ።

በቅርቡ በፀረ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ የነበሩ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ አድራሻቸው እንደጠፋ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ተገድለው አስክሬናቸው ተጥሎ ተገኝቷል።