የዓለም ዋንጫ ደጋፊዎች የፍፃሜውን ጨዋታ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
በዓለም ላይ ያሉ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በፈረንሳይና በአርጀንቲና መካከል የሚደረገውን የዋንጫ ፍልሚያ ለማየት በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
የኳታሯ ዶሃ ከተማም አይረሴ ተብሎ የሚጠበቀውን የዛሬውን ጨዋታ የምታስተናግድ ይሆናል።
ፈረንሳይና አርጀንቲና ዋንጫዎችን በማግኘት ታሪክ ያላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ማን አሸናፊ ሊሆን ይችላል የሚለውን የበለጠ ተጠባቂ አድርጎታል።
ፈረንሳይ በ92 የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ ሶስተኛ ዋንጫዋን ለማግኘትና በዚህም የጣልያንና የብራዚልን ፈለግ ለመከተልም አቅዳለች።
በአውሮፓውያኑ 1998 ፈረንሳይ ዓለም ዋንጫውን ስታሸንፍ ቡድኑን በአምበል የመራው የአሁኑ አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕስ ተከታታይ ዋንጫዎችን ለማሸነፍም አነጣጥሯል።
ከዚህ ቀደም ተከታታይ ዋንጫዎችን ያገኘው ጣሊያናዊው ቪቶሪዮ ፖዞ በአውሮፓውያኑ 1938 ነው።
ለአርጀንቲና የአገሪቱ ተስፋ እና ህልም በአንድ ተጫዋች ላይ ይህም በሊዮኔል ሜሲ ትከሻ ላይ ተጭኗል።
የምንጊዜም የአለማችን ምርጥ ተጫዋች የሚባለው የ35 አመቱ ሜሲ ይህም ለአገሩ የሚያደርገው የመጨረሻ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይፈልጋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በምጣኔ ኃብት ቀውስ ላለችው አርጀንቲና ተስፋን የጫረው ጨዋታ
በአርጀንቲና መዲና ቦነስአይረስ የሃገሪቱ የወደፊት ደስታ በዚህ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ላይ የተንጠለጠለ ይመስኣልለ።
አርጀንቲና በከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ቀውስ ተመትታለች። በሃገሪቱ ያለው የዋጋ ንረት የማይቀመስ ሆኗል። በርካታ ሚሊዮኖች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ቀን ተሌት እየታገሉም ይገኛሉ። በዚህ ሁሉ የኢኮኖሚ ውሽንፍር ውስጥ ግን ሊዮኔል ሜሲ እና የአርጀንቲና ቡድን በአለም ዋንጫው ያደረጉት ግስጋሴና ዋንጫውን ለማሸነፍ ያላቸው ተስፋ በርካቶችን ለጊዜው ጭንቀታቸውን ገሸሽ እንዲያደርጉም ምክንያት ሆኗቸዋል።
በአሁኑ ወቅት አርጀንቲናውያን በጉጉትና በተስፋ የሚጠብቁት ዋንጫውን ማሸነፋቸው ነው።
“ይህች ሃገር በምጣኔ ኃብት ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ ተመትታለች። የዓለም ዋንጫ ጨዋታው አንድ እያደረገን ነው። በዓለም ላይ ምርጥ የሆነ ተጫዋች አለን። በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ነው” ሲል የቡና ቤት ባለቤት የሆነው ሉዊስ ሳርኒ
ከሜሲ ባሻገር ቡድኑ አገሩን አኩርቷል ብሏል።
በፈረንሳይ ለሚኖረው ለአርጀንቲናዊው ማርቲን ሮጃስ በአሁኑ ወቅት ለበዓል ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ወደ ትውልድ ስፍራው የመጣ ሲሆን የእሁዱ ጨዋታም ትልቅ ትርጉም አለው።
በ1990ዎቹ ከመወለዱ ጋር ተያይዞ አርጀንቲና የዓለም ሻምፒዮና ሆና አይቶ አያውቅም እናም “ህልሜ ነው” ይላል።
በተለይም ለሜሲ የመጨረሻው የዋንጫ ጨዋታው ከመሆኑ አንጻር በድል ቢያጠናቅቅ ደስታውን አይችለውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳያውያን ዋንጫውን እንደሚያነሱት ተማምነዋል
በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ የዋንጫ ጨዋታው በጉጉትና በደስታ እየተጠበቀ ይገኛል።
ፈረንሳይ በሰባት የዓለም ዋንጫዎች ውስጥ ይህ አራተኛዋ ነው የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ስትደርስ። የፈረንሳይ ደጋፊዎች አገራቸው ከደቡብ አሜሪካ ሃገራት ጋር ባደረገችው ያለፉት 10 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ሽንፈት እንዳላስተናገደች እየተናገሩ ነው። የመጨረሻውን ሽንፈት ያስተናገደችው በአውሮፓውያኑ 1978- ይህም በአርጀንቲና ነበር።
በዚህ ዓመትም ኪሊያን ምባፔ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ እንደ አውሮፓውያን "የላቀ" አይደለም ምክንያቱም እዚያ ያለው ውድድር "ዝቅተኛ" ነው የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
ምባፔ ይህንን አስተያየቱን የሰጠው ለመጨረሻ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያነሳችው የደቡብ አሜሪካ ቡድን ብራዚል ስትሆን ይህም በአውሮፓውያኑ 2002 ስትሆን አርጀንቲናም ከአውሮፓውያኑ 1986 ጀምሮ ማሸነፍ አለመቻሏን በመጥቀስ ነበር። በተጨማሪም ፈረንሳይና አርጀንቲና በ2018 ባካሄዱት የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ፈረንሳይ 4ለ3 በሆነ ውጤት ስታሸንፍ ምባፔ ራሱ ሁለት ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል። በነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ፈረንሳይ ዋንጫውን እንደምታነሳ ከፍተኛ የራስ መተማመን ላይ ብትሆንም አርጀንቲና በበኩሏ እነዚህን ሁሉ ቁጭቶች ለመወጣት ምክንያት ይሆናታል ተብሏል።
በዚህ የፍጻሜ ጨዋታ ውድድር ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ባለቤታቸው ብሪጊት ይገኛሉ።
በዚህ ወር መጀመሪያ የወንዶች የአለም ዋንጫ ጨዋታን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት የሆነችውን ዳኛ ስቴፋኒ ፍራፕፖርትን ጨምሮ ከፍተኛ የሃገሪቱ የስፓርት ባለስልጣናት አብረዋቸው ጨዋታውን ይከታተላሉ።












