በዓለም ዋንጫ ታሪክ ታላቅ የተባሉት የውድድሩ አስር አሸናፊ አገራት እነማን ናቸው?

አሸናፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታላቁ የእግር ኳስ መድረክ የዓለም ዋንጫ በአየራት ዓመቱ እየመጣ የማይረሳ ክስተት ትቶ ያልፋል።

ነገር ግን አስካሁን በተካሄዱት ዓለም ዋንጫ ውድድሮች ታሪክ ታላቁ ድል የማነው?

ጋሪ ሊኒከር፣ አለን ሺረር እና ሚካህ ሪካርድስ እነሆ አስሩ ድንቅ የዓለም ዋንጫ ድሎች እነዚህ ናቸው ይላሉ።

አርጀንቲና - 1978 (10ኛ)

አርጀንቲና ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ያነሳችው በፈረንጆቹ 1978 ነበር።

የማራዶና ቡድን በወቅቱ ኔዘርላንድስን 3 ለ 1 በማሸነፍ ታላቁን የእግር ኳስ ዋንጫ ማንሳት የቻለው በማሪዮ ኬምፔስ እና በዳኒኤል ቤርቶኒ ጎሎች ነው።

እንግሊዛዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሊኒከር በወቅቱ ማሪዮ ኬምፔስ ብዙ ጎሎች አስቆጥሮ የወርቅ ጫማ ሲቀበል ያስታውሳል።

አርጀንቲና ዋንጫውን ለማንሳት ከኔዘርላንድስ የገጠማት ፈተና ቀላል የሚባል አልነበረም።

አርጀንቲና ኔዘርላንድስን አሸንፋ ዋንጫ ስትወስድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አርጀንቲና ኔዘርላንድስን አሸንፋ ዋንጫ ስትወስድ

ፈረንሳይ - 2018 (9ኛ)

የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ፈረንሳይ ክሮሺያን 4 ለ 2 አሸንፋ ነው ዋንጫውን ያነሳችው።

ሩሲያ ባዘጋጀችው በዚህ የዓለም ዋንጫ በአሠልጣኝ ዲዲዬ ዴሾ የተመራው ቡድን አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ፣ አልፎም በዙር 16 አርጀንቲናን 4 ለ 3 በመርታት ነው ለፍፃሜው የደረሰው።

አለን ሺረር የ2018ቱ የፈረንሳይ ቡድን በጣም ጠንካራ እንደነበር የሚረሳ አይደለም፤ ዋንጫውን ማንሳትም ይገባቸው ነበር ይላል።

ሚካህ ሪካርድስ በበኩሉ በፈረንሳይ ቡድን ውስጥ ከበረኛው አንስቶ እስከ አጥቂው መልካም ብቃት ላይ እንደነበሩ ያወሳል።

ሊነከርም በሙያ አጋሮቹ ሐሳብ ይስማማል።

ፈረንሳይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጣልያን - 1982 (8ኛ)

ጣልያን በ1982 የዓለም ዋንጫን በማንሳት ከብራዚል ጋር እኩል ሦስት ጊዜ ዋንጫውን የግሏ ያደረገች ሆና ተመዝግባለች።

ጣልያን በወቅቱ ስፔን ማድሪድ ላይ በተስተናገደው የፍፃሜ ጨዋታ ምዕራብ ጀርመንን 3 ለ 1 በመርታት ነው ባለድል የሆነችው።

በጊዜው የጣልያን ግብ ጠባቂ እና አምበል የነበረው የ40 ዓመቱ ዲኖ ዞፍ በዕድሜ ትልቁ የዓለም ዋንጫ ተሰላፊ ሆኖ ታሪክ ሠርቷል።

በ1982 የወርቅ ጫማውን የወሰደው ፓውሎ ሮሲ ነበር።

ሺረር እንደሚያስታውሰው ጣልያን በጊዜው የመጀሪያዎቹን ሦስት ጨዋታዎች አቻ ከወጣች በኋላ አርጀንቲና እና ብራዚልን በመርታት ነው ለፍፃሜው የደረሰችው።

ጣሊያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስፔን - 2010 (7ኛ)

ቲኪ-ቲካ በተሰኘው የእግር ኳስ ስልት የሚታወቀው የ2010 የስፔን ብሔራዊ ቡድን የተመልካቾችን ቀልብ የሳበ ነበር።

ስፔን ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታዋን በስዊትዘርላንድ ተሸንፋ ነው የጀመረችው።

በፍፃሜው በተጨማሪ ሰዓት ኔዘርላንድስን 1 ለ 0 በመርታት የዋንጫ ባለድል የሆነችው ስፔን አንድሬስ ኢኒዬስታ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ነው።

ሺረር እንደሚያስታውሰው ስፔን ከመጀመሪያ ጨዋታቸው በኋላ በጣም ልዩ ሆነው ነው የቀረቡት።

ስፔን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምዕራብ ጀመርን - 1990 (6ኛ)

ምዕራብ ጀመርን ከምሥራቁ ክፍል ጋር ከመዋሃዷ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያነሳችው የዓለም ዋንጫ ሲሆን፣ ከዚያ ቀድም ሁለት ጊዜ ዋንጫ አንስታለች።

በፍፃሜው ከአርጀንቲና የገጠመችው ምዕራብ ጀርመን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በመርታት ነው ዋንጫውን ከፍ ያደረግችው።

ምዕራብ ጀርመን ለዋንጫ ለመድረስ በነበረው የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ እንግሊዝን በፍፁም ቅጣት ምት መርታቷን ሊኒከር ያስታውሳል።

“ጨዋታውን እንግሊዝ ልታሸንፍ እንደምትችል ሳስብ ምናልባት ለፍፃሜ ደርሰንስ ቢሆን ኖሮ ብዬ አስባለሁ” ይላል ሊኒከር።

ፈረንሳይ ያዘጋጀችውን የዓለም ዋንጫ በወሰደችበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፈረንሳይ ያዘጋጀችውን የዓለም ዋንጫ በወሰደችበት ወቅት

ፈረንሳይ - 1998 (5ኛ)

ፈረንሳይ በ1998 ያዘጋጀችውን የዓለም ዋንጫ ራሷ በማንሳት ለመጀመሪያ ጊዜ ባለድል መሆኗን ብዙዎች ያስታውሱታል።

በፍፃሜው ከተቆጠሩት ሦስት ጎሎች ሁለቱን ዚነዲን ዚዳን ነበር ማስቆጠር የቻለው።

ፈረንሳይ በዚህ የዓለም ዋንጫ በአንድም ጨዋታ ሽንፈት አላጋጠማትም።

ነገር ግን በሩብ ፍፃሜው እና በዙር 16 ከ90 ደቂቃ አልፎ ተጨማሪ 30 ደቂቃ እንዲሁም የፍፁም ቅጣት ምት አስፈልጓት ነበር።

ዲያጎ ማራዶና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማራዶና

አርጀንቲና - 1986 (4ኛ)

አርጀንቲና ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ማንሳት የቻለችው በ1986 ነበር።

በሜክሲኮ የተዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ምዕራብ ጀርመንን 3 ለ 2 በመርታት ዋንጫውን አንስታለች።

ይህ የዓለም ዋንጫ የማይዘነጋው ማራዶና ‘የእግዚያብሔር እጅ’ የተሰኘችውን ጎል በሩብ ፍፃሜው እንግሊዝ ላይ ያስቆጠረበት በመሆኑ ነው።

ጋሪ ሊኒከር በወቅቱ ስድስት ጎሎች በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል።

ሊኒከር እንደሚያስታውሰው አርጀንቲና፤ ማራዶና ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ድንቅ የነበሩ ተጫዋቾች የነበሩበት ቡድን ይዛ ነው የመጣችው።

የማራዶና ተዓምር ግን የሚረሳ አልነበረም ይላል ሊኒከር።

ካፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ብራዚል - 2002 (3ኛ)

ብራዚል አምስተኛ የዓለም ዋንጫዋን ያነሳችበት ዓመት ነበር 2002።

በውድድሩ ሰባቱንም ጨዋታዎች በመርታት ዋንጫውን ያነሱት ብራዚሎች አሠልጣኝ የነበሩት ሉዊዝ ፊሊፔ ስኮላሪ ነበሩ።

በአምበሉ ካፉ እየተመሩ አምስተኛ ዋንጫቸውን ያጣጣሙት ብራዚሎች በፍፃሜው ጀርመንን 2 ለምንም ረትተዋል።

ጃፓን ባዘጋጀችው በዚህ የዓለም ዋንጫ ሮናልዲንሆ እንግሊዝ ላይ ያስቆጠራት የቅጣት ምት የምትታወስ ናት።

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በ1966 (እአአ) ዋንጫ ባነሳበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በ1966 (እአአ) ዋንጫ ባነሳበት ጊዜ

እንግሊዝ - 1966 (2ኛ)

እንግሊዝ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያነሳችው በ1966 ነበር።

በወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ አልፍ ራምሴ፤ አምበሉ ደግሞ ቦቢ ሙር ነበሩ።

በገዛ አገሯ የተጫወተችው እንግሊዝ በፍፃሜው ምዕራብ ጀርመንን 4 ለ 2 በመርታት ዋንጫውን ከፍ አድርጋለች።

ሊኒከር፤ “ምናልባትም ምርጡ እንግሊዛዊ አጥቂ ነው ብዬ የማምነው ጂሚ ግሪቭስ በወቅቱ ድንቅ ነበር” ይላል።

የምንጊዜም ታላቁ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን የተባለለት ስብስብ የዓለም ዋንጫን ባሸነፈበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የምንጊዜም ታላቁ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን የተባለለት ስብስብ የዓለም ዋንጫን ባሸነፈበት ጊዜ

ብራዚል - 1970 (1ኛ)

ብራዚል ሦስተኛ የዓለም ዋንጫውን ያነሳችው በአሠልጣኝ ካርሎስ አልቤርቶ እና በአምበሉ ፔሌ እየተመራች ነበር።

የወቅቱ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ምናልባትም የምንም ጊዜም ታላቁ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ።

ሁሉንም ጨዋታዎች አሸንፈው ለፍፃሜ የደረሱት ብራዚሎች ጣልያንን 4 ለ 1 በመርታት ዋንጫውን ከፍ አድርገዋል።

በርካታ ያልተጠበቁ ነገሮች የታዩበት በኳታር የተስተናገደው የዓለም ዋንጫስ ስንተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጥ ይሆን?