መንገደኞች ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን እንዳንጓዝ ተከለከልን አሉ

የፎቶው ባለመብት, dw
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ትኬት የቆረጡ ተጓዦች አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ደርሰው እንዳይጓዙ መከልከላቸውን ገለጹ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው መንገደኞች የአየር መንገዱን ትኬት ቢቆርጡም ወደ አየር ማረፊያው በሄዱበት ወቅት ግን አየር ማረፊያውን በሚጠብቁ የፀጥታ ኃይሎች እንዳይጓዙ መከልከላቸውን ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋርጦ የነበረውን ወደ ትግራይ የሚያደርገውን በረራ መጀመሩ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ቅዳሜ እና እሁድ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ትኬት የቆረጡ መንገደኞች በተለይ ወጣቶች ከመቀለው የአሉላ አባነጋ እና ከሽረ የአየር ማረፊያዎች ከጉዞ መከልከላቸውን የሚገልጹ መረጃዎች ሲወጡ ነበር።
ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ በቢቢሲ የተጠየቁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የፌደራል ፖሊስ ግን እየቀረበ ስላለው ቅሬታ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል።
ወጣት መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ እንዳይጓዙ የተከለከሉት በፌደራል መንግሥቱ መሆኑን እና በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣንት ጋር የክልሉ አስተዳደር እየተናጋገረበት እንደሆነ ህወሓት መግለጹን የድርጅቱ ቴሌቪዥን ድምጺ ወያነ ዘግቧል።
የፌደራል ኃይሎች ከመቀለ ከመውጣታቸው በፊት ወደ ትግራይ እንደሄደ የሚናገረው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደ አንድ መንገደኛ፣ የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን ሲቆጣጠሩ መንገዶች በመዘጋታቸው ምክንያት ቋሚ መኖሪያው ወደ ሆነችው አዲስ አበባ መመለስ አለመቻሉን ይገልጻል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ሳምንታት በረራ ሲጀምር ትኬት ቆርጦ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ወደ አየር ማረፊያው በሄደበት ወቅት የአየር ማረፊያውን በሚጠብቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት መከልከሉን ተናግሯል።
“በረራዬ ትናንት (እሁድ) ነበር፤ ነገር ግን ከ16 ዓመት በላይ እና ከ64 ዓመት እድሜ በታች እንዲሁም ወጣቶች መሄድ አትችሉም አሉን። የልጆች እናት፣ የህክምና ሪፈር ያላቸው እና በእድሜ የገፉት ግን መሄድ እንደሚችሉ ነው የፌደራል ፖሊስ አባላቱ የነገሩን።” ብሏል።
“አዲስ አበባ ነው የምኖረው፣ መታወቂያዬም የአዲስ አበባ ነው። ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ነበር የሄድኩት” የሚለው ይኸው መንገደኛ፣ አስፈላጊውን መረጃ ባቀርብም ሊቀበሉኝ አልቻሉም” ሲል ተናግሯል።
የአየር መንገዱ ሠራተኞችም ክልከላው ከቁጥጥራቸው ውጪ እንደሆነ ነግረውናል ይላል።
“በእኔ ግምት ከ200 እስከ 300 የሚሆን ሰው ነበር። ዛሬ ግን ቁጥሩ ቀንሷል” ሲልም አሁንም አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ሆኖ የሚለወጥ ነገር ካለ እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልጿል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያደቻ ስለተባለው ነገር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
“እኛ የምናውቀው ነገር የለም። እንደምታውቁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእድሜና ጾታ ክልከላ የለውም። ምክንያቱም በሕግ እና በሥርዓት ነው የሚተዳደረው። እስከ ዛሬ እንዲህ አይነት ክልከላ የለንም። ወደ ድረ ገጻችን ብትገቡም ምንም አይነት ክልከላ እንደሌለ ታያላችሁ” የሚል መልስ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ለአየር መንገዱ ከመንግሥት በኩልም ቢሆን ምንም አይነት ክልከላን የሚመለከት መመሪያ እንዳልተሰጠው ኃላፊው ገልጸዋል።
“ምናልባት የአካባቢው መመዘኛ ወጥቶ እንደሆነ የክልሉ ባለሥልጣናትን ብትጠይቁ የሚሻል ይመስለኛል። በእኛ በኩል ግን እስካሁን የደረሰን ምንም አይነት መረጃ የለም።ከመንግሥት የተሰጠ ትዕዛዝም የለም።”ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገረው እና መጀመሪያ ከመቀለ በረራ ተከልክሎ የነበረ አንድ ግለሰብ አዲስ አበባ ውስጥ የሚያስተዳድረው ተቋም እንዳለው የሚያረጋግጥ መረጃ ካቀረበ በኋላ እንዲጓዝ እንደተፈቀደለት ተናግሯል።
የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት በደረሱት ስምምነት መሰረት የፌደራል ፖሊስ በክልሉ የሚገኙ የፌደራል መንግሥት ተቋማትን ተረክቦ መጠበቅ እና ማስተዳደር ከሳምንት በፊት መጀመሩ መገለጹ ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎም በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ የሚገኘው የአሉላ አባነጋ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ በፌደራል ፖሊስ አባላት እየተጠበቀ ይገኛል።
የፌደራል ፖሊስ አባላት በሽረ እና መቀለ በሚገኙ የአየር ማረፊያዎች ወጣት መንገደኞች እንዳይጓዙ ከልክለዋል መባሉን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት ቢቢሲ የፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ጄይላን አብዲን ጠይቆ መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ተጓዦች በእድሜ ተለይተው በአውሮፕላን እንዳይጓዙ ተከልክለዋል የሚለውን መረጃ “አሁን ከእናንተ ነው የምሰማው” በማለት ዝርዝሩን ለማወቅ እንደሚያጣሩ የሚገልጽ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
የህወሓት ንብረት የሆነውና በትግራይ ክልል የሚገኘው ድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ባሰራጨው ዘገባ የትግራይ መንግሥት ኃላፊዎች “ስለ ክልከላው የምናውቀው ነገር የለም፤ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንነጋገርበታለን” የሚል መልስ መስጠታቸውን ገልጿል።
ህወሓትን ጠቅሶ ድምጺ ወያነ እንደዘገበው ክልከላው ከፌደራል መንግሥቱ የመጣ መሆኑን ከክልሉ ባለሥልጣንት መረዳታቸውን ገልጸው፣ ስለሁኔታው ከፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣንት ጋር እየተናጋገሩ መሆናቸው ተዘግቧል።
ለሁለት ዓመት የቆየው ደም አፋሳሹ ጦርነት ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ከተባባሰ በኋላ ክልሉ በትራንስፖርትም ሆነ በኮምዩኒኬሽን ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ጋር ለረጅም ጊዜ ተቆራርጦ መቆየቱ ይታወቃል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት አመራሮች መካከል በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ጦርነቱን በዘላቂነት ለማቆም እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ከተስማሙ በኋላ የአየር ትራንስፖርት የጀመረው ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ነበር።
ይህ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል የሚያደርገው በረራ በተጀመረበት ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተጓዥ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ፣ እንዲሁም ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ትኬት በመቁረጡ በቀን አንድ ጊዜ የነበረው የበረራ መረሃ ግብር በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ሁለት ከፍ እንዲል ተደርጓል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከክልሉ ዋና ከተማ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ወደ ሽረ እንዳሥላሴ ባለፈው ሳምንት በረራ ማድረግ መጀመሩ ይታወሳል።












