ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን መቀለ አረፈ

ተጓዦች መቀለ ሲደርሱ

የፎቶው ባለመብት, Tigrai Television

የምስሉ መግለጫ, ተጓዦች መቀለ ሲደርሱ

ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያውን የመንገደኞች ጉዞውን ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ አደረገ።

የፈደራል መንግሥቱ ሠራዊት መቀለን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ለ18 ወራት ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን እነሆ መልሶ ጀምሯል።

ዛሬ ረቡዕ ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው የተጓዦች አውሮፕላን በትግራይ መዲና መቀለ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ደርሷል።

የአውሮፕላን በረራዎችን አሁናዊ መረጃ የሚያስቃኘው ከ'ፍላይትራዳር24' የተገኘው መረጃ፣ ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ እኩለ ቀን ላይ የተነሳው የበረራ ቁጥር ኢቲ 104 ቦይንግ 737 አውሮፕላን መቀለ ማረፉን አመልክቷል።

የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያም ተጓዦችን ያሳፈረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መቀለ መድረሱን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትናንት ታኅሣሥ 18/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከረቡዕ ታኅሣሥ 19 ጀምሮ ወደ መቀለ መደበኛ በረራ ማድረግ እንደሚጀምር አስታውቆ ነበረ።

አየር መንገዱ በረራው እንደሚጀምር የገለጸው የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚን ያካተተ የፌደራል መንግሥቱ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑክ ቡድን ወደ መቀለ ተጉዞ፣ ከትግራይ አመራሮች እና ከማኅብረሰብ አባላት ጋር ከተወያየ በኋላ ነው።

አየር መንገዱ ወደ መቀለ በረራ እንደሚጀምር ከተገለጸ በኋላ ወደ ትግራይ መጓዝ በሚፈልጉ ሰዎች የአየር መንገዱ ቲኬት ቢሮዎች ተጨናንቀው ነበር።

ተጓዦች

የፎቶው ባለመብት, ena

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ እንዲሁም ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ የሚያስችሉ ቲኬቶች ተቆርጠው ማለቃቸውን የአየር መንገዱ ድረገጹ ያሳያል።

አየር መንገዱም ወደ መቀለ ለሚያደርገው ጉዞ ያቀረበው የጉዞ ትኬት እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ በፍጥነት ተሸጦ ማለቁን ገልጾ፣ የመንገደኞችን ፍላጎት ለማሟላት አየር መንገዱ የበረራዎችን ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀለ በረራውን የሚያደርገው በእርስ በርስ ጦርነቱ ለሁለት ዓመታት ሲፋለሙ የቆዩት የትግራይ ኃይሎች እና የፌደራሉ መንግሥት የሰላም ስምምነት ከደረሱ በኋላ ነው።

ከሁለት ወራት ገደማ በፊት ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆም መስማማታቸው ይታወሳል።

በዚህ ስምምነት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲቀላጠፍ፣ የፌደራሉ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ተስማምተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ነገ ሐሙስ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ወደ መቀለ እንደሚገባ እና የህወሓት ተዋጊዎች ከባድ መሳሪያዎችን ማስረከብ እንሚጀምሩ ገልጸዋል።

ወደ መቀለ የሚደረገው የመንገደኞች የአውሮፕላን በረራ መጀመሩ ሁለቱ አካላት የደረሱት የሰላም ስምምነት አፈጻጸም አዎንታዊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ወደ መቀለ የሚደረገው በረራ መጀመሩ ተራርቀው የነበሩ የቤተሰብ አባላትን እንደሚያገናኝ እና የንግድ ግንኙነቶችን ለማስቀጠል እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ የሚያደርገው በረራ በአገር ውስጥ ከሚደረጉት ውስጥ በብዛት ቀዳሚው የነበረ ሲሆን፣ ወደ መቀለ በቀን ከ10 እስከ 14 በረራዎች ይደረጉ ነበር።

ከመቀለ በተጨማሪ ወደ ሽረ ከተማ ዕለታዊ በረራ ይደረግ የነበረ ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ወደ ምትገኘው ታሪካዊቷ የአክሱም ከተማ ደግሞ በቀን እስከ ሁለት በረራዎች ይደረጉ ነበር።

ከአየር በረራው በተጨማሪ የባንክ እና የቴሌኮሙኒኬን አገልግሎቶች በአንዳንድ ቦታዎች ተጀምረዋል።

በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራው ልዑክ ወደ መቀለ ተጉዞ ከህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር በተገናኙ ወቅት የሰላም ስምምነቱ አዎንታዊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በሁለቱም አካላት ተገልጿል።

ይሁን እንጂ ደብረጽዮን የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ሚሊሻዎች ከያዟቸው የትግራይ አካባቢዎች ለቅቀው ካልወጡ ሙሉ ሰላም አይኖርም ሲሉ ተናግረዋል።

የኤርትራ ጦር በሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፎ የተዋጋ ቢሆንም በአፍሪካ ኅብረት አዳራዳሪነት የተደረሰው የሰላም ስምምነት አካል ሳይሆን ቀርቷል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ ለረሃብ አደጋ አጋልጧል።