10 የተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ አቋቋሙ

አርማዎች

የፎቶው ባለመብት, SM

መንግሥት በጀመረው በአገራዊ የምክክር መድረክ አካሄድ ላይ መሠረታዊ ቅሬታ አለን ያሉ 10 የሚደርሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ አቋቋሙ።

በአገራዊ ምክክር መድረክ ላይ መሠረታዊ ልዩነት እንዳለቸው የገለጹት ፓርቲዎቹ "እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የሚፈጠጥር አገራዊ የውይይት አማራጭን ለማቅረብ የሚያስችል የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ (Caucus) አቋቁመናል" ሲሉ አሳውቀዋል።

ስብስቡ በመድረክ፣ ሕብር ኢትዮጵያ፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ የአፋር ፍትህ እና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ዓረና ትግራይ እና የዶንጋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መቋቋሙ ተገልጿል።

ፓርቲዎቹ በአገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶች እና ፖለቲካዊ ልዩነቶችን የተፈጠሩ “የከፉ የፖለቲካ አካሄዶችን እና ሕይወት እስከማሳጠት የደረሱ ግጭቶች” ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

በአገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ “ሁሉም ፓርቲዎች” ችግሩን ለመፍታት “የተሻለው አማራጭ” ብሔራዊ ምክክር መሆኑን ተስማምተዋል ብሏል መግለጫው።

አገራዊ ምክክሩ በምን መልኩ ይካሄድ በሚለው ላይ ውይይቶች እየተደረጉ ባለበት ወቅት "መንግሥት ሂደቱን የሚቆጣጠር ረቂቅ ሕግ በማዘጋጀት የአንድ ፓርቲ የበላይነት ባለው ፓርላማ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥያቄ እና ግብአት ችላ በማለት እንዲጸድቅ አድርጓል” ብሏል።

የብሔራዊ መግባባትን መሠረታዊ መርሆዎች በጣሰ መልኩም መንግሥት “አጠራጣሪ በሆነ ሂደት” የኮሚሽኑን አባላት ምርጫ አካሂዷል ሲል ጠቅሷል።

“ከዚህ ባለፈም ከመንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኙትን አካላት ኮሚሽኑ ለማነጋገር የሚያስችለው ድንጋጌ አልተቀመጠለትም” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአገሪቱ ያሉ ችግሮች የሚቀረፉት ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ወይይት በማካሄድ ብቻ ነው ሲልም አክሏል።

"አማራጭ" ባለው አዲስ የምክክር መድረክ በኩል የተለያዩ ምክረ ሃሳቦችንም አቅርቧል።

አፋጣኝ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚቆጣጠሩት የተኩስ ማቆም በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች እንዲተገበር፣ የኮሚሽኑ አባላት ነጻ፣ ገለልተኛ እና ሁሉን አቀፍ እንዲሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ትርጉም ያለው ሚና ሊኖራቸው ይገባል ያለ ሲሆን የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዙ ብቻ የሚሉ አይነት አንዳንድ ማነቆ ናቸው ያላቸው አንቀጾች እንዲወጡም ጠይቋል።

በአጀንዳ ቀረጻ ዙሪያም ያለው ሁኔታ ግልጽ እንዲሆን እና ሁሉንም ባለደርሻዎች ያካተት እንዲሆን ከመጠየቁ በተጨማሪ፣ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እንዲሳተፉ ይደረግ የሚሉ እና ሌሎችንም ምክረ ሃሳቦች አቅርበዋል።

በቅርቡ ይጀመራል የተባለውን አገራዊ ምክክር የሚያስተባብር ኮሚሽን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።

ነገር ግን በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አንዳንድ ወገኖች በኮሚሽኑ የማቋቋም ሂደት ላይ ጥያቄዎችን በማንሳት ተቃውሞ ከማሰማት ባሻገር በሂደቱ እንደማይሳተፉ ሲገልጹ ቆይተዋል።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት በማንኛውም ወገን የሚደረግ “የጦርነት ጉሰማን” እንደሚቃወሙ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

ጥምረቱ በኢትዮጵያ በአዲስ መልክ ያንዣበበው ጦርነት ዳግም እንዳይቀሰቀስ የጠየቀ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥት፣ ህወሓት እና “ኦነግ ሸኔ” የሰላም ጥሪን እንዲከተሉም አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረትም በመግለጫው ላይ “በማንኛውም ሁኔታ ለሚቀሰቀስ የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጎዱት ሴቶች ናቸው። ስለዚህም ያንዣበበው ጦርነት ዳግም እንዳይቀሰቀስ አጥብቀን እንጠይቃለን” ሲል አስፍሯል።

በነሐሴ 2013 ዓ.ም የተመሰረተው ይህ ጥምረት፤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ ሦስት መቶ ገደማ አባላትን በስሩ ያቀፈ መሆኑን አመልክቷል።