የሱዳን ዋነኛ የኃይል ማሠራጫ በድሮን በመመታቱ ካርቱም እና ፖርት ሱዳንን ጨለማ ዋጣቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ግዙፍ የሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫዎች ላይ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ምክንያት በትልልቆቹ የሱዳን ከተሞች ውስጥ መጠነ ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቋረጥ መከሰቱ ተዘገበ።
የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የተቋረጠባቸው ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር እየተፋለመ ያለው የሱዳን ጦር ሠራዊት የሚቆጣጠራቸው ዋና ከተማዋ ካርቱም እና የጄነራል አል ቡርሐን መቀመጫ የሆነችው የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳን ናቸው።
የዐይን እማኞች እንደተናገሩት በሱዳን ጦር ኃይል ቁጥጥር ሥር በምትገኘው በምሥራቃዊ ናይል ግዛት ውስጥ በምትገኘው አትባራ ጥቃት ከተፈጸመባቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ ማዕከላት ከፍተኛ የእሳት ነበልባል እና ጭስ አይተዋል።
ሱዳን የጦር ሠራዊቱን በሚመሩት በጄነራል አብደል ፋታህ አልቡርሐን እና በተቀናቃኛቸው ጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎ በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተራዘመ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።
ሁለቱ ኃይሎች በሚያካሂዱት ሦስት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ጦርነት በመሠረተ ልማቶች ላይ ከባድ ውድመት መድረሱ እየተዘገበ ነው።
አሁን በድሮን በተፈጸመው ጥቃት በሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውስጥ ወሳኝ ማዕከል የሆነው አል-ሙቅሪን የተባለው ማሠራጫ ማዕከል ዒላማ በመሆኑ ነው መጠነ ሰፊ የኃይል መቋረጥ በዋና ዋና ከተሞች ላይ ያጋጠመው።
አንድ የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣን ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደተናገሩት በኃይል ማሠራጫው ማዕከል ላይ የመጀመሪያው ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ እሳቱን ለማጥፋት የሞከሩ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ ሁለተኛው ዙር ጥቃት በተፈጸመበት ጊዜ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት ወሳኙ የሱዳን ኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ ማዕከል አል-ሙርቂን የሚያሠራጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚገኘው ከአገሪቱ ትልቁ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ነው።
ማዕከሉ ኤሌክትሪኩን ወደ በርካታ ቁልፍ የሱዳን አካባቢዎች የሚያሠራጭ በመሆኑ የደረሰበት የድሮን ጥቃት ያስከተለው ጉዳት ውጤቱ በብዙ ቦታዎች ላይ ኃይልን በማቋረጥ ከፍተኛ ጉዳትን ያደርሳል።
በጄነራል ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሱዳን ጦር ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ባሉ በርካታ አካባቢዎች በሚገኙ የሰላማዊ ሰዎች መገልገያ የሆኑ መሠረታ ልማቶችን በተደጋጋሚ ዒላማ በማድረግ የድሮን ጥቃት ይፈጽማል ተብሎ ይከሰሳል።
ከዚህ ቀደም በካርቱም እና በሁለተኛዋ ከተማ ፖርት ሱዳን አውሮፕላን ማረፊያዎችን ጨምሮ በርካታ ዒላዎችን በድሮን መምታቱን መግለጹ ይታወሳል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጦር ሠራዊቱ ተሸንፎ ከዋና ከተማዋ ካርቱም የወጣ ቢሆንም ሌሎች ወሳኝ የሱዳን ግዛቶችን ባለፉት ወራት ተቆጣጥሮ ይዞታውን እያሰፋ ነው።
በመጪው ሚያዝያ ሦስት ዓመት በሚሞላው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው እና 12 ሚሊዮን ሱዳናውያን ለመፈናቀል መዳረጋቸው ተዘግቧል።
በተጨማሪም ጦርነቱ የእርዳታ አቅርቦትን በማደናቀፉ በተለያዩ የሱዳን ክፍሎች ውስጥ ረሃብ ሊከሰት ይችላል በማለት ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የረድኤት ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ነው።















