ሂውማን ራይትስ ዎች ፓርላማው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያን ውድቅ እንዲያደርግ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, HOPR/FB
ሂዩማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ ሕግ አውጪዎች፣ ለመንግሥት የሲቪል ማኅብረሰብ ድርጅቶችን ለመገደብ ስልጣን የሚሰጠውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ ውድቅ ማድረግ አለባቸው ሲል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አጋሮች ገና ለፓርላማ ያልቀረበውን ረቂቅ ሕግ "እንዲያወግዙ" እና "ማንኛውም የሕግ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መስፈርቶችን ማክበር እንዳለበት" ግልጽ እንዲያደርጉ የመብት ተሟጋቹ ተቋም ጠይቋል።
ረቂቅ ማሻሻያው የውጭ አገር ድርጅቶች እና አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለ'ፖለቲካ አድቮኬሲ'፣ የመራጮች ትምህርት፣ ምርጫ መታዘብ እና ማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለመሥራት ከውጭ የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ እንዳይቀበሉ ይከለክላል።
ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች የማሻሻያ ረቂቁ፤ የመንግሥት ባለስልጣናት "ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና ይግባኝ የመጠየቅ መብት 'ብሔራዊ ደህንነት' ምዝገባን ለመከልከል፣ ለማገድ ወይም ለማፍረስ ምክንያት ይሆናል" ብሏል።
ሃሳቡ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ከሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ አስቀድሞ መቅረቡንም ተቋሙ ጠቁሟል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር "በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ ላይ የቀረቡት ማሻሻያዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ያወጀውን ለውጥ ያፈርሳል።
"እነዚህን ማሻሻያዎች መቀበል ለአገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የሲቪክ ምህዳር ጉዳት ነው" ብለዋል።
ማሻሻያዎቹ የቀረቡት ወትሮውንም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሲቪክ ምህዳሩ እና ገለልተኛ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ባሉበት መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።
ተቋሙ አክሎም "ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ የደህንነት እና የስለላ ኃይሎች በኢትዮጵያውያን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ድርጅቶች ላይ የሚያደርሱትን ዛቻ፣ ወከባ እና ማስፈራሪያ ጨምረዋል" ብሏል።
በሥራ ላይ ያለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ የገባው ጠ/ሚ ዐቢይ ሥልጣን ላይ ከወጡ አንድ ዓመት በኋላ ነው።
አዋጁ ከዚያ በፊት የነበረውን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን 'አያሠራም' የሚል ትችት ሲቀርብበት የነበረውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ሽሮታል።
ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን የሚመለከቱ አዋጆች እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል የሚል ግምት ተይዞ ነበር።
ነገር ግን ከስድስት ወራት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን "አላሠራ ያሉ አዋጆችን" እንዲያሻሽል "አቅጣጫ" ማስቀመጡ ይታወሳል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ "መሥሪያ ቤቱ የሚሠራቸው ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚያደርግ የሕግ ክፍተት" መኖሩን ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረው ነበር።
አቶ ሳምሶን አክለውም የሚመሩት መሥሪያ ቤት "አዋጁ እንዲሻሻል እየሠራ መሆኑን" ስለመናገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ማሻሻያዎቹን የያዘው ረቂቅ የሚጸድቅ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በወጣው የ2011 ሕግ የተመዘገቡትን ግኝቶች ይለውጣል ሲል ስጋቱን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ማሻሻያዎቹ በሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች ላይ ሰፊ ገደቦችን ፣ ከባድ የቢሮክራሲያዊ መሰናክሎችን ፣ ከባድ የወንጀል ቅጣቶችን እና ጣልቃ ገብ ክትትልን የጣለውን የአገሪቱን የቀድሞውን የ2001 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት አዋጅን እንደሚመስል ተቋሙ አስገንዝቧል። የ2001ዱ ሕግ አብዛኛዎቹ ነጻ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንቅስቃሴያቸውን "እንዲዘጉ ወይም እንዲቀንሱ" እንዳስገደዳቸው ሂዩማን ራይትስ ዎች አስታውሷል።
ከዚህ በተጨማሪም ረቂቅ ማሻሻያው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣናት የቦርድ አባላትን ቁጥር በመቀነስ "ለጉልህ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በር ይከፍታል" ብሏል።
በማሻሻያው መሠረት 11 የነበሩት የቦርድ አባላት ወደ ሰባት የተቀነሰ ሲሆን፤ ከሰባቱ የቦርድ አባላት አራቱ በፍትህ ሚኒስትሯ የሚሰየሙ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች ይሆናሉ።
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የመንግሥት ተወካዮች ቁጥር ሦስት ነበር። ሶስት የነበሩት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሚሰየሙት የቦርድ አባላት በማሻሻያ ረቂቁ ወደ ሁለት ዝቅ ተደርገዋል።
በመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ ማሻሻያ ረቂቁ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል።
በተጨማሪም ውጭ አገር ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ድርጅቶች 'ፖለቲካል አድቮከሲ'፣ የመራጮች ትምህርት፣ ከምርጫ ክትትል እና ከምርጫ ጋር በተያያዙ ሥራዎች እንዳይሰሩ በግልፅ ይከለክላል።
አገር በቀል ድርጅቶችም የፖለቲካ አድቮኬሲ፣ በመራጮች ትምህርት፣ በምርጫ መታዘብ ወይም ማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዘ ሥራዎችን ለመስራት ለማከናወን "ከውጭ የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ ወይም ሃብት መቀበል አይችልም።"
ሂዩማን ራይትስ ዎች "ረቂቁ የ"ፖለቲካዊ አድቮኬሲ"ን ትርጉም አይገልጽም፤ ይህን ቃል ለመንግሥት የዘፈቀደ ትርጉም ክፍት አድርጎታል" ብሏል።
ባለሥልጣኑ ድርጅቶችን ለማገድ ሊጠቀምባቸው የሚችላቸውን አዳዲስ አሰራሮች በረቂቁ ቀርቧል ሲል የመብት ተሟጋቹ ተቋም ተችቷል።
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሰረት ባለሥልጣኑ ምርመራ በሚያከናውንበት ወቅት "ከባድ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያረጋግጥ" እንዲሁም "የድርጅቱ እንቅስቃሴ ማገድ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው" ዋና ዳይሬክተሩ ከሦስት ወር ላልበለጠ ጊዜ የዕገዳ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል።
ማሻሻያ ረቂቁ ይህን ድንጋጌ "ከባድ የሕግ ጥሰት ስለመፈጸማቸው አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም" እንዲሁም "ድርጅቱ ካልታገደ የማይመለስ ጉዳት ይደርሳል ብሎ ካመነ" በሚሉ ሐረጋት ለውጦታል።
ከዚህ በተጨማሪ ማሻሻያ ረቂቁ የምርመራ ሥራው በሦስት ወር የዕግድ ጊዜ ካልተጠናቀቀ ቦርዱ ለተጨማሪ ሦስት ወራት ሊያራዝመው እንደሚችል ያትታል።
ባለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አምስት ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን "ግልጽ ባልሆነ እና በፖለቲካዊ ምክንያቶች" አግደው እንደነበር ሂዩማን ራይትስ ዎች አስታውሷል።
የመንግሥት ባለስልጣናት እና ኤጀንሲዎችም ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ ተቃዋሚ አባላትን ጨምሮ ነፃ እና ተቺ ድምጾችን በማሰር፣ በርካቶችን አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርገዋል ሲል የመብት ተሟጋቹ ወቅሷል።
እአአ ከ2020 ጀምሮ ቢያንስ 54 ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሠራተኞች ከአገር መሰደዳቸውን ሲፒጄን ጠቅሶ አስታውቋል።
ፓርላማው በጋዜጠኞች፣ በሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች እና በመብት ተሟጋቾች ተቃውሞ ሲገጥመው የነበረውን የመገናኛ ብዙሃን ማሻሻያ አዋጅ ባለፈው ሚያዝያ ወር ማጽደቁን ሂዩማን ራይትስ ዎች አስታውሷል።
ሕጉ የሚዲያ ፍቃድን የማገድ ወይም የመሰረዝ ስልጣንን ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ቦርድ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወደ ሚሾሙት ዋና ዳይሬክተር በማዘዋወር "የመንግሥት ቁጥጥርን ያሳድጋል ብሏል።
"አገሪቱ በበርካታ ቀውሶች ስትታገል፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች፣ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው አለመግባባት እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በገባችበት ወቅት ነፃ የሕዝብ ምልከታ እና የኢትዮጵያን የመብት ሁኔታ መሰነድ ወሳኝ ናቸው" ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች አሳስቧል።
"በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የመብት ሁኔታን ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት በጸዳ ሁኔታ በሲቪል ማኅበራት እና በገለልተኛ ሚዲያዎች ክትትል ማድረግ እጅግ ወሳኝ ያደርገዋል" ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።















