በአራት አገራት የሚፈለገውን ዕጽ አዘዋዋሪ ለመያዝ በቦሊቪያ መጠነ ሰፊ አሰሳ ተጀመረ

በአደገኛ ዕጽ ዝውውር እና በሌሎችም ወንጀሎች በአራት አገራት የሚፈለገውን አደገኛ ተጠርጣሪን ለመያዝ ከፍተኛ የተባለውን ዓለም አቀፍ አሰሳ ቦሊቪያ ማድረግ ጀመረች።

ሴባስቲያን ማርሴት የተባለው የ32 ዓመት ተፈላጊ በበርካታ ቶኖች የሚመዘን ኮኬይን የተባለውን ዕጽ ከደቡብ አሜሪካ ወደ አውሮፓ በማዘዋወር በጥብቅ እየተፈለገ ነው።

ተፈላጊው ከዕጽ ዝውውሩ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት በጫጉላ ሽርሽር ላይ የነበሩትን የዕጽ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ የሆኑትን ግለሰብ ኮሎምቢያ ውስጥ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል ተብሎም ተከሷል።

በደቡብ አሜሪካዋ አገር ቦሊቪያ ውስጥ እንደሚገኝ የተነገረው ተፈላጊውን ለመያዝ ከ2,250 በላይ የፖሊስ መኮንኖች ሳንታ ክሩዝ በተባለችው ከተማ ላይ ተሰማርተዋል።

ግለሰቡ ከቦሊቪያ በተጨማሪ በብራዚል፣ በፓራጓይ፣ በኡራጓይ እና በአሜሪካ ፖሊሶች እየተፈለገ ይገኛል።

ሴባስቲያን ማርሴት በዜግነት ኡራጓያዊ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ በፖሊስ እየተፈለገ ቢሆንም ተሰውሮ ይገኛል።

ግለሰቡ ከቤተሰቦቹ ጋር በአሁኑ ወቅት በቦሊቪያዋ የኢኮኖሚ ማዕከል ሳንታ ክሩዝ በተባለችው ከተማ ውስጥ በአንድ ቅንጡ ቤት እንደሚገኝ ቅዳሜ ዕለት ፖሊሶች ደርሰውበት ነበር።

ነገር ግን ፖሊሶች ተፈላጊውን ለመያዝ ሳይችሉ በመቅረታቸው ነው አሁን መጠነ ሰፊ አሰሳን የከፈቱት።

የፖሊስ አዛዡ ዩሞር ጁስቶ ኮንዶሪ እንደተናገሩት፣ ግለሰቡን ለመያዝ ከተሰማሩት ፖሊሶች መካከል አንዱን ጠባቂዎቹ በማገታቸው ለማምለጥ የቻለ ሲሆን፣ ፖሊሱ ግን ተለቋል።

ፖሊስ እንደሚለው ሴባስቲያን ማርሴት ከነበረበት ቤት ከወጣ በኋላ ሚስቱን እና ሦስት ልጆቹን በመኪና ይዞ ወደ አጎራባች የቦሊቪያ ግዛት ሳያመልጥ እንዳልቀረ ይታመናል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ተሰማርተው እየተካሄደ ባለው አሰሳ በበርካታ ቤቶች ላይ ፍተሻ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም የጦር መሳሪያዎች እና የጥይት መከላከያ ጃኬቶች መያዛቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ሴባስቲያን ማርሴት ‘ፒሲዩ’ የተባለን በኡራጓይ የመጀመሪያው የሆነውን እና የኮኬይን ዕጽን ከፓራጓይ በኡራጓይ በኩል ወደ አውሮፓ በድብቅ የሚያስተላለፍ ዓለም አቀፍ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድንን ይመራል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ግለሰቡ ከፖሊሶች በተደጋጋሚ የማምለጥ ታሪክ አለው። ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2013 ለመጀመሪያ ጊዜ የተያዘው ወደ ኡራጓይ ማሪዋና የተባለውን አደገኛ ዕጽ እንዲሁም የጦር መሳሪያ በማስገባት ነበር።

በ2018 ከእስር ሲለቀቅ ወደ ጎረቤት ፓራጓይ በመሄድ ሐሰተኛ ማንነት እየተጠቀመ ወደ በርካታ አገራት ለመጓዝ እንደቻለ ይታመናል።

በ2021 (እአአ) ዱባይ ውስጥ ሐሰተኛ የፓራጓይ ፓስፖርት በመጠቀም ለአጭር ጊዜ ከታሰረ በኋላ፣ ከኡራጓይ ባለሥልጣናት ትክክለኛ የጉዞ ሰነድ ማግኘት በመቻሉ ተለቋል።

ግለሰቡ ላይ በበርካታ አገራት ውስጥ ምርመራ እየተደረገበት እያለ እንዴት ከኡራጓይ አዲስ ፓስፖርት ሊያገኝ እንደቻለ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል።

የሴባስቲያን ማርሴት ስም የበለጠ ትኩረት ማግኘት የቻለው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔድሮ፣ የፓራጓይ ዕጽ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ላይ ኮሎምቢያ ውስጥ ለተፈጸመው ግድያ ተጠርጣሪ መሆኑን ከገለጹ በኋላ ነው።

ሟች ዐቃቤ ሕግ በፓራጓይ ታሪክ ከፍተኛ በተባለው የፀረ ኮኬይን እና የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ዘመቻ ላይ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ሲሆን፣ ግድያውም ይህ የወንጀል እንቅስቃሴ የተደናቀፈባቸው የፈጸሙት በቀል እንደሆነ ይታመናል።

የቦሊቪያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሴባስቲያን ማርሴት ወደ አገራቸው የገባው ለዐቃቤ ሕጉ ገዳዮች ገንዘብ በመክፈል ዋነኛ ተጠርጣሪ መሆኑ ይፋ ከተደረገ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነው።

ሴባስቲያን ማርሴት ቦሊቪያ ውስጥ የቅንጦት ሕይወት ይመራ የነበረ ሲሆን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብም የተለያዩ ንብረቶችን እና የሁለተኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ቡድንን ለመግዛት አውሏል።