የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ዳግም ከአልሻባብ ታጣቂዎች ጋር መዋጋቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Somali Regional Communication/fb
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው ከገቡ የአልሻባብ ታጣቃዎች ጋር ሰኞ ዕለትም መዋጋታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሲናገሩ የክልሉ መንግሥትም ይህንን አረጋግጧል።
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ የአልሻባብ ታጣቂዎች ከሶማሊያዋ ባኩል ግዛት ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን በመግባት ጥቃት ከፍተው እንደነበር ይታወሳል።
ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በሶማሌ ክልል ከፌርፌር ወረዳ ብዙም ሳይርቅ በሚገኘው ላስቁሩን በተባለ ስፍራ የልዩ ኃይል አባላት ከሶማሊያው እስላማዊ ቡድን ታጣቂዎች ጋር መዋጋታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል መስተዳደር ሰኞ ምሽት ላይ እንዳሳወቀው የክልሉ ልዩ ኃይል “ዳግም ድንበር አቋርጦ ለመግባት የሞከረውን አሸባሪውን የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ደመሰሰ” በማለት የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን መማረኩን ገልጿል።
የአልሻባብ ታጣቂዎች ከአጎራባች ሶማሊያ ሂራን ግዛት ተነስተው ድንበር በማቋረጥ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ፌርፌር ወረዳ ለመግባት እንደሞከሩና በልዩ ኃይሉ ኤል ቁዱን በሚባል ቦታ ላይ በተደረገ ውጊያ መመታቱን አመልክቷል።
ክልሉ እንዳለው በዚህ ውጊያ ከተገደሉት በተጨማሪ በርካቶች መማረካቸውን እንዲሁም የጦር እና የመገናኛ መሣሪያዎች መያዛቸው ተነግሯል።
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ባለፉት ቀናት በበርካታ መኪኖች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ከገቡት የአልሻባብ አባላትን ጋር ተዋግተው በርካታ የቡድኑን አባላት መግደላቸውን ገልጸው ነበር።
ነዋሪዎች በልዩ ኃይሉና ድንበር ተሻግሮ በገባው ቡድን መካከል ዛሬ በተደረገው ውጊያ ምክንያት የተኩስ ድምጽ ከአካባቢው ርቀው በሚገኙ ቦታዎች ጭምር ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል።
ነገር ግን በዚህ ውጊያ ስለደረሰ ጉዳት እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሶማሌ ክልል እንዳስታወቀው፣ ወደ ክልሉ ዘልቆ በገባው የአልሻባብ ቡድን ታጣቂዎች ላይ በሚካሄደውን ዘመቻ ለመሳተፍ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ክልሉ ተሰማርተዋል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ሙሐመድ ከድንበር ተሻግሮ የገባውን ቡድን ለመዋጋት የተሰማራውን የአገር መከላከያ ሠራዊት መጎብኘታቸውም ተነግሯል።
ባለፉት ቀናት ወደ አፍዴር ዞን ገብቶ ከነበረው የአልሻባብ ቡድን ጋር ሁልሁል በተባለው ስፍራ ልዩ ኃይሉ ባደረገው ውጊያ ከአንድ መቶ በላይ ታጣቂዎች መገደላቸውን የክልሉ መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በሁልሁል ዘመቻ ላይ የተሳተፉት የልዩ ኃይል አባላትን ለሌላ ግዳጅ ወደ ድንበር መሸኘታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ በመግባት በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ሁልሁል በሚባል ንዑስ ቀበሌ ውስጥ የነበሩ በርካታ የአልሻባብ ታጣቂዎች በክልሉ ልዩ ኃይል ተከበው ሁሉም መደምሰሳቸውንና 13 የቡድኑ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውም ተገልጿል።
በሶማሊያ እና በጎረቤት አገራት ውስጥ ከባድ ጉዳት ያደረሱ የሽብር ጥቃቶች ሲፈጽም የቆየው አልሻባብ በኢትዮጵያ ላይ ግን ከሙከራ ያለፈ ጥቃት አድርሶ አያውቅም ነበር።
ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ በርካታ ተዋጊዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በማስገባት የፈጸማቸው ጥቃቶች፣ ከክልሉ ልዩ ኃይል በኩል ከባድ የመልሶ ማጥቃት ምላሽ እንደገጠመው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
አልሻባብ ባለፈው ሳምንት የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በርካታ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት መግደሉን ለሮይተርስ ዜና ወኪል ቢናገርም፣ ነዋሪዎች ግን የቡድኑ አባላት በተለይ ሁልሁል በተባለው አካባቢ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።












