ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና በትንፋሽ የሚወሰድ አዲስ ዓይነት የኮቪድ-19 ክትባት አስተዋወቀች
ቻይና በትንፋሽ የሚሰጥ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት በሽታውን ለመከላከል እንዲውል ፈቃድ ሰጠች።
ይህንን አዲስ ዓይነት የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ተግባራዊ እንዲሆን በመፍቀድም የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
ካንሲኖ በተባለው ተቋም የተሰራው ይህ ለየት ያለ ክትባት በመርፌ ከሚሰጠው ጋር ተመሳሳይ ግብአቶችን ይጠቀማል። በዚህም በሽታውን ከሚያመጣው ቫይረስ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የዘረመል መዋቅር ያለው፣ ነገር ግን ጉዳትን የማያስከትል ቫይረስን በውስጡ ይዟል።
ይህ በትንፋሽ የሚወሰድ የኮቪድ ክትባት እንደ ሌሎቹ ክትባቶች ሰውነት ለኮሮናቫይረስ በሚጋለጥበት ጊዜ የተፈጥሮ የመከላከያ ሥርዓት እንዴት ቫይረሱን እንደሚዋጋና እንደሚያስወግድ ያለማምደዋል።
እንደ የአስም ህመም ማስታገሻ በትንፋሽ የሚወሰደው ይህ ክትባት ‘ኮንቪዴሺያ ኤር’ የሚባል ሲሆን አንድ ጊዜ በትንፋሽ ወደ ውስጥ ከተሳበ በኋላ የመከላከል አቅም እንደሚፈጥር አምራቹ ኩባንያ ገልጿል።
ከዚህ ቻይና ውስጥ ፈቃድ ካገኘው በትንፋሽ የሚወሰድ የኮቪድ መከላከያ ክትባት በተጨማሪ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ ያሉ ተመራማሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም በአፍንጫ የሚረጭ ተመሳሳይ ክትባት ላይ ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት እንዲህ ዓይነቶቹ ክትባቶች በአፍንጫ እና በአፍ ላይ ሲረጩ፣ የኮቪድ ቫይረስ በዋናነት ወደ ሰውነት በሚገባባቸው በአፍንጫ ውስጥ እና በሌሎች የመተንፈሻ ክፍሎቻችን ሽፋን ላይ ቫይረሱን የመከላከል አቅምን ይጨምራሉ።
የቻይና የጤና ጉዳዮች ተቆጣጣሪ አካል የሆነው ብሔራዊ የህክምና ምርቶች አስተዳደር፣ ‘ካንሲኖ’ የተባለውን በትንፋሽ የሚወሰድ የኮቪድ ክትባት በመጀመሪያ በማጠናከሪያ ክትባትነት እንዲሰጥ ፈቃድ ሰጥቷል።
ይህ አዲሱ ዓይነት ክትባት ቀደም ሲል በመርፌ የሚሰጠውን ክትባት የወሰዱ ሰዎችን ከበሽታው እንዲጠበቁ የመከላከል አቅማቸውን እንደሚያጠናክር የተደረጉ ሙከራዎች አመልክተዋል።
በመላው ዓለም ተከስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረገው ኮሮናቫይረስ በአሁኑ ጊዜ እየተሰጡ ባሉት ክትባቶች ምክንያት መስፋፋቱና ገዳይነቱ የቀነሰ ቢሆንም አሁንም የምድራችን የጤና ስጋት ነው።
ወረርሽኙ መከሰቱን ተከትሎ በአስቸኳይ ተዘጋጅተው ለአገልግሎት የዋሉ በርካታ ዓይነት ክትባቶች ቢኖሩም ሁሉም በመርፌ የሚሰጡ መሆናቸው ይታወቃል።
ነገር ግን በሌላ ዓይነት መልኩ ክትባት ለማዘጋጀት ተመራማሪዎች ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ አሁን ቻይና ለአገልግሎት እንዲውል የፈቀደችው በትንፋሽ የሚወሰደው የኮቪድ ክትባት ከሌሎቹ የተለየ ነው ተብሏል።