ዝነኛው ራፐር ዲዲ ከከባድ ክሶች ነጻ ቢባልም ዋስትና ተከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጥቁር አሜሪካዊውን ሙዚቀኛ ሾን 'ዲዲ' ኮምብስን የክስ ሂደት የተከታተለው የዳኞች ቡድን ሴቶችን ለወሲባዊ ንግድ በማዘዋወር ጥፋተኛ ብሎ፤ከፍተኛ ከሆኑት ከማጭበርበር እና ከወሲብ ንግድ ጋር በተያያዙ ክሶች ነጻ ቢለውም የዋስትና መብት ተከለከለ።
የሙዚቀኛው ጠበቆችም የዲዲ የግል ጄት በሃዋይ ተከራይቶ እንደሚገኝ በመጥቀስ ከእስር ቢለቀቅ የሚያመልጥበት ዕድል የለም ሲሉ ተከራክረዋል።
ሆኖም ዳኛ አሩን ሰብራማኒያን የኮምብስን የጥቃት ታሪክ በማንሳት ሙዚቀኛው ሃያ ዓመት እስር በሚጠብቀው እና በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ፍርድ እስከሚተላለፍበት ድረስ እስር ቤት ነው ማሳለፍ ያለበት ሲሉ ብይን ሰጥተዋል።
ወደ ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ በኒው ዮርክ ከተማ በተካሄደው የፌደራል ችሎት ኮምብስ እውቅናውን እና ሃብቱን በመጠቀም ለወሲብ ንግድ ሴቶችን የሚያዘዋውር የወንጀል ቡድን መርቷል ሲሉ ዐቃቤያነ ሕጎች ክስ አቅርበውበታል።
12 አባላት ያሉት ክሱን የሰሙ የዳኞች ቡድን ኮምብስን ከባድ ከሆኑ አምስት ክሶች ነጻ ያሉት ለ13 ሰዓታት ያህል ከተከራከሩ በኋላ ነበር።
ሆኖም ዋና ዳኛው ያስተላለፉትን ውሳኔ ተክትሎ ኮምብስ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በቁጥጥር ሥር በሚገኝበት በብሩክሊ በሚገኘው የፌደራል እስር ቤት ይቆያል ተብሏል።
በክሱ ላይ ፍርድ ለመስጠትም በመጪው ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም. በጊዜያዊነት ቀጠሮ ተሰጥቷል።
የኮምብ ጠበቃ ማርክ አግኒፊሎ ዳኛው ደንበኛቸውን እንዲለቁ በስሜት ተከራክረዋል።
ተከላካይ ጠበቃው ኮምብስ ከመታሰሩም በፊት ክሱን ለማሻሻል የቤት ውስጥ ጥቃት ወንጀለኞች ፕሮግራም ላይ ተሳትፏል፤ ከአውሮፓውያኑ 2018 ወዲህም ምንም የፈፀመው ወንጀል የለም ብለዋል።
"ልናምነው ይገባል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል ጠበቃው አግኒፊሎ።
ሆኖም የኮምብስ የቀድሞ ፍቅረኛ የሆነችው ሙዚቀኛዋ ካሳንድራ ቬንቹራ የሂፕ ሃፕ ሙዚቀኛው ከእስር የሚለቀቅ ከሆነ አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ በጻፈችው ደብዳቤ አስጠንቅቃለች።
ራፐሩ የቤት ውስጥ ጥቃት መፈፀሙን አምኖ የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን ያለ ፈቃድ ምንም ዓይነት ወሲባዊ ድርጊት ወይም ገንዘብ ለማግኘት ሲል ሕገ ወጥ ድርጊት አለመፈፀሙን ገልጿል።
ዳኛ ሰብራማኒያን ራፐሩ በግላዊ ግንኙነቱ ጥቃት መፈፀሙን በማመኑ ዋስትናውን መከልከሉን አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኮምብስ ከተከሰሰባቸው ከባድ ወንጀሎች እና የወሲባዊ ዝውውር ድርጊቶች ነጻ መባሉን ዳኞች ሲያሳውቁ ችሎቱ ውስጥ የነበረው ድባብ ስሜታዊነት የታየበት ነበር።
የወሲብ ንግድ ዝውውር እና ለገንዘብ ሲባል ወንጀል መፈፀም እስከ ዕድሜ ልክ እስራት የሚስቀጣ ነው።
ኮምብስ ፍርዱን ከሰማ በኋላ "ጉልበቱን ይዞ እና ፊቱን ወደ ወንበሩ አዙሮ የሚፀልይ ይመስል ነበር" ሰውነቱ ሲንቀጠቀጥም ነበር።
ውሳኔው የተላለፈው የክሱን ሒደት የሰሙ የዳኞች ቡድን በወሲብ ንግድ ዝውወር እና በወሲብ ንግድ ሴቶችን በማጓጓዝ በቀረበበት ክሶች ላይ የደረሱበትን ውሳኔ ለፍርድ ቤቱ ካሳወቁ በኋላ ሲሆን፣ ለገንዘብ ሲባል በፈፀማቸው ወንጀሎች ላይ ውሳኔ ላይ መድረስ አልቻሉም ነበር።
የዳኞቹ ቡድን እንዳለው በራፐሩ ላይ ከቀረቡት መካከል በጣም ውስብስብ የሆኑትን ክሶቹን በተመለከተ በተለያዩ ጎኖች በተነሱ ሃሳቦች ላይ የማያሳምኑ ሃሳቦች ነበሩ።
ለገንዘብ ሲባል የሚፈፀም ወንጀል ወይም ሕገ ወጥ ተቋምን መምራት መደበኛው የክሱ ስም ነው።
በዚህ ክስ ኮምብስ ላይ ፍርድ ለማስተላለፍ ዐቃቤያነ ሕጉ ለወሲብ ንግድ ሴቶችን ማዘዋወርን፣ ጠለፋን፣ በእፅ ማደንዘዝን እና ፍትህን ማደናቀፍን ጨምሮ ይህንን የወንጀል ተቋም ለመምራት የተጠቀመባቸውን የተባባሪ ሰንሰለቶች ማረጋገጥ ነበረባቸው።
የተከሳሹ ጠበቃም የኮምብስ ባልደረቦች እያወቁ ተባባሪ ካልሆኑ ክሱ በዚህ ሕግ መሠረት ሊታይ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።
ዐቃቤያነ ሕጎች ግን ለሰባት ሳምንታት በተካሄደው ችሎት ቬንቹራን፣ ራፐር ኪድ ኩዲ፣ በርካታ የቀድሞ ሠራተኞች እና የሆቴል የጥበቃ ሠራተኞችን ጨምሮ በጉዳዩ ላይ ከ30 በላይ ምስክሮችን አቅርበዋል።
መንግሥት በበኩሉ ቪንቹራ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ሆና በሰጠችው ቃል ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ ኮምብስ በወሲባዊ ድርጊቶች ላይ እንድትሳተፍ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት እና ይህንን የማታስተባብል ከሆነም የቀረፀውን ምሥል እንደሚለቀው እንዳስፈራራት ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።
ቬንቹራም ረቡዕ ዕለት በነበረው ችሎት ራፐሩ በዋስትና የሚለቀቅ ከሆነ አደጋ እንደሚፈጥር አስጠንቅቃለች።
ለፍርድ ቤቱ በተጻፈው ደብዳቤ፣ ጠበቃዋ ዳግላስ ዊግዶር "ኮምብስ እርሷን እንዲሁም ማኅበረሰቡን ጨምሮ በክሱ ላይ ምስክርነት በሰጡ ሰዎች ላይ አደጋ እንደሚፈጥር ቪንቹራ ታምናለች" ብሏል።
የክሱ ማጠንጠኛ የሆነው ቪዲዮ ላይ ራፐሩ በአውሮፓውያኑ 2016 በሎስ አንጅለስ በሚገኝ ሆቴል ቪንቹራን ሲደበድባት እና ሲጎትታት ከደኅንነት ካሜራዎች የተገኙ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
የደኅንነት ሠራተኞች እነዚህን ቪዲዮዎች እንዲያጠፏቸው ለዚህም እንደሚከፍላቸው እንደሞከረ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
የኮምብ ጠበቆች ደንበኛቸው በሴቶች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አምነው፤ ነገር ግን በአደንዛዥ እፅ እና በቅናት ተነሳስቶ የፈፀማቸው ናቸው፤ ከፍተኛ የሆነ የወሲብ ዝውውር እና የወንጀል ሰንሰለቶች ጋር ፈፅሞታል በሚል ለቀረቡበት ክሶች የሚያሳዩ ማስረጃዎች የሉም ሲሉ ተከራክረዋል።
ኮምብስ ከወሲባዊ ትንኮሳ እና ጥቃት ጋር የተያያዙ በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።
በሀርለም የተወለደው ራፐሩ ኖቶሪዮስ ቢአይጂን እና አሸርን ጨምሮ በሂፕ ሃፕ ትልቅ ስም ያላቸውን ሙዚቀኞች የሚወክል እና በሙዚቃ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነው ባድ ቦይ ሪከርድስ የተባለ ተቋም መሥርቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ሲን ጆን የተባለ የልብስ ብራንድ እንዲሁም የሽቶዎች እና የአልኮል ንግዶች ላይ የተሰማሩ ተቋማት ያሉት ሲሆን፣ የሚዲያ ተቋምም አለው።















