ዲዲ ከቀድሞው ፍቅረኛው ጋር ግንኙነት ያለውን ራፐር ለመግደል ማሴሩ በፍርድ ቤት ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊው ራፐር ሾን ኮምብስ 'ዲዲ' ከቀድሞው ፍቅረኛው ግንኙነት ያለውን ራፐር ኪድ ኩዲን ለመግደል በማሴር የቀድሞ ረዳቱን አፍኖ መውሰዱን ከሰሞኑ በነበረ ችሎት ተሰምቷል።
የዲዲ የቀድሞ ሰራተኛው በሰጠችው ምስክርነት ባላንጣዬ ነው ያለውን ራፐሩን ለመግደል ቤቱን ሰብሮ ገብቷል ብላለች።
ከአስር ዓመታት በላይ ለራፐር ዲዲ የሰራችው ካፕሪኮርን ክላርክ ዲዲ እና አንድ የጥበቃ ሰራተኛ በአውሮፓውያኑ 2011 ወደ ቤቷ መጥተው ወደ ኪድ ኩዲ ቤት አብራቸው እንድትሄድ እንዳስገደዷት ገልጻለች።
ኪድ ኩዲን ለመግደል ወደ ቤቱ ሊሄዱ ስለሆነ "ልብስሽን ልበሽ" ሲል በወቅቱ ዲዲ እንዳዘዛት ካፕሪኮርን ለፍርድ ቤቱ ገልጻለች።
ስራ በጀመረችበት የመጀመሪያዋ ዕለት እሷን ሊገድላች እንዳዘተባት ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።
የ55 አመቱ ዲዲ በበኩሉ ለቀረቡበት ለወሲብ ንግድ ሰዎችን በህገወጥ መንገድ በማዘዋወር፣ የወሲብ ብዝበዛ፣ በመመሳጠር እና የግድያ ሙከራ ወንጀለኛ አይደለሁም ሲል ተከራክሯል።
ራፐር ኪድ ኩዲ ወይም ስኮት መስኩዶ ባለፈው ሳምንት በነበረ ችሎት ላይ በራፐር ዲዲ ላይ ምስክርነት ለመስጠት ተገኝቶ ነበር።
ኪድ በዚህ ምስክርነቱ ላይ ከቀድሞው የዲዲ ፍቅረኛ የአርኤንድቢ ሙዚቀኛዋ ካሳንድራ 'ካሲ' ቬንቱራ የነበረውን ግንኙነት አስረድቷል።
በተጨማሪም ዲዲ በሎስ አንጀለስ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሰብሮ እንደገባና እንዲሁም ፖርሽ የተሰኘው መኪናንም በተቀጣጣይ ፈንጂ ጉዳት አድርሶበታል ብሏል።
ዲዲ ወንጀለኛ ሆኖ ከተገኘ የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቀዋል።
ባድ ቦይ የተሰኘው የኢንተርቴይንመንት ኩባንያ የምርቶች ዳይሬክተር የነበረችው ካፕሪኮርን፤ ዲዲ፣ ኪድ ከካሲ ቬንቱራ ጋር ያለውን የፍቅር ግንኙነት ማወቁን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2011 ቤቷ መምጣቷን አስረድታለች።
ቤቷ ሲደርስም ሽጉጥ ይዞ ነበር በማለት ለፍርድ ቤቱ ምስክርነት የሰጠችው ካፕሪኮርን በከፍተኛ ሁኔታ ተናዶ እንደነበር እና ኪድን "እንገድለዋለን " በማለት ሲዝት ነበር ብላለች።
ኪድ ቤት ሲደርሱም ዲዲ እና የጥበቃ ሰራተኛው ወደ ውስጥ ሲገቡ ግለሰቧ ለካሲ ደውላ እየሆነው ስላለው ነገር መናገሯን ጠቅሳለች።
ስልክ ስታወራ ያገኛት ዲዲም በጣም እንደተናደደ የገለጸችው ካፕሪኮርን ኪድ ወደ ቤቱ ሲመለስም በፍጥነት መውጣታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።
የአርኤንድቢ ሙዚቀኛዋ ካሳንድራ 'ካሲ' ቬንቱራ በቅርቡ ለአራት ቀናት ምስክርነቷን መስጠቷ ይታወሳል። ለዓመታት ይደበድባት እንደነበር በፍርድ ቤት በስሜት ተሞልታ ተናግራለች። በወሲብ ንግድ ከተሰማሩ ሴቶች ጋር ዕፅ በመጠቀም ይፈጽም የነበረው ወሲብም ገልጻለች።
ለአሥርታት በዚህ የስቃይ ሕይወት ውስጥ መቆየቷን ካሲ ተናግራለች።












