በስፔን እና ፖርቹጋል በድንገት መብራት ጠፍቶ ሚሊዮኖች ጨለማ ውጧቸዋል

ድንገተኛ የኤሌክትሪክ መቋረጥን ተከትሎ ትናንት በስፔን፣ ፖርቹጋል እና የተወሰኑ የፈረንሳይ አካባቢዎች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መብራት ጠፍቶባቸዋል።

የዩርኤሌክትሪክ ሠራተኛ የሆኑት ክርስቲን ሩቢ እንደተናገሩት በፈረንሳይና ስፔን መካከል ያለ የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ችግር ገጥሟቸዋል።

የስፔን የኤሌክትሪክ መስመር ከተቀረው የአውሮፓ መስመር ጋር መቆራረጡንም አክለዋል። የዚህ መስመር መቋረጥ ብቻ ችግሩን እንዳላስከተለና ሌሎችም ነገሮች ተደማምረው ኤሌክትሪክ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የባቡር አገልግሎት ከመቋረጡ በተጨማሪ የትራፊክ መብራት ስለተቋረጠ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ የሚደረጉ ጉዞዎች ተስተጓጉለዋል።

የስፔን ትራንስፖርት ሚኒስትር ኦስካር ፑን 11 ባቡሮች መቆማቸውን ተናግረዋል። ቤቶች፣ ሱቆች፣ ሬስቶራንቶች በጨለማ ተውጠዋል።

አሳንሱር ውስጥ ሳሉ መብራት የጠፋባቸውም ሰዎች ብዙ ናቸው።

መብራቱ በጠፋበት ምሽት ላይ በስፔን 50 በመቶ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን መመለስ ተችሏል። በፖርቹጋል ደግሞ ለ750,000 ተገልጋዮች መብራት መመለስ መቻሉ ተገልጿል።

የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ኤሌክትሪክ የተቋረጠበት ምክንያት ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነና የበይነ መረብ ጥቃት መሆኑን የሚጠቁም ምልክት እንደሌለ ተናግረዋል።

መብራት መጥፋት የጀመረው ትናንት እኩለ ቀን ሲሆን በአፋጣኝ ተስፋፍቷል። የማድሪድ ነዋሪዎች ለድንገተኛ ጉዳይ ካልሆነ ባሉበት እንዲቆዩም ተነግሯቸዋል።

የስፔን ኤሌክትሪክ ኃይል ከ10 ሰዓታት በኋላ ኃይል መመለስ እንደሚችል ሲገልጽ የፖርቹጋል ኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ አንድ ሳምንት ሊወስድ እንደሚችል ጠቁሟል።

በካርድ ገንዘብ ለማውጣትና ነዳጅ ለመቅዳትም የተቸገሩ ሰዎች በርካታ ናቸው።

አንድ ነዋሪ "አብዛኛው ሰው ተደናግጦ ነበር። ባቡር ጣቢያው ውስጥ ትርምስ ነበር" ብላለች።

ስልክም አልሠራ ብሎ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ሰዎች ተቸግረው ነበር።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በ286 ሕንጻዎች ከአሳንሱር ውስጥ መውጣት ያልቻሉ ሰዎችን አውጥተዋል።

ሆስፒታሎችም አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም የጽኑ ሕሙማንን የመተንፈሻ ድጋፍ ለማስቀጠል ተቸግረዋል።

የስፔን የኒውክሌር ማብላያና ነዳጅ አምራች ድርጅት ሥራቸውን አቋርጠዋል።

በአንዳንድ አውሮፕላን ማረፊያዎች በረራዎች ተሰርዘዋል አልያም ዘግይተዋል። 96 ከፖርቹጋል እና 45 ከስፔን የሚነሱ በረራዎች ተቋርጠዋል።