የተጠበሱ፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና የታሸጉ ምግቦች ያለ ጊዜው ከሚከሰት ሞት ጋር ሊያያዙ ይችላሉ

በፋብሪካ የሚቀነባበሩ እና ብዙ ነጥረ ነገሮች የሚጨመርባቸው ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎች ያለ ጊዜያቸው የመሞት እድላቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ዩኬን እንዲሁም አሜሪካን ጨምሮ በስምንት አገራት የተደረገ ጥናት አመለከተ።

በዓለም ላይ በበርካታ ሰዎች ዘንድ እየተዘወተሩ የመጡት በፋብሪካ የሚቀነባበሩ ስጋዎች፣ ብስኩቶች፣ ለስላሳ መጠጦች፣ አይስ ክሬም እንዲሁም ለቁርስ የሚሆኑ ሲሪያሎች ብዙ ንጥረ ነገር የሚገባባቸው በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና የታሸጉ ምግቦች (UPF) ምሳሌ ናቸው።

እነዚህ በፋብሪካ የሚቀነባበሩ ምግቦች አብዛኛውን ጊዜ በቤት ውስጥ ምግብ በምናበስብለት ውስጥ የማንጠቀማቸውን ንጥረ ነገሮችን እና ኬሚካሎች ይይዛሉ።

እነዚህም የምግቡን ገጽታ ለማሻሻል የሚገቡ ቅመማ ቅመሞች፣ ማጣፈጫዎች እና ኬሚካሎች ናቸው።

አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በፋብሪካ የሚቀነባበሩ እና የሚታሸጉ ምግቦች ከጤና መጓደል ጋር ለምን እንደሚቆራኙ በግልጽ አይታወቅም።

ምግቦቹ በፋብሪካ በሚቀነባበሩበት ወቅት ካለው ሂደት ጋር እንደሚያያዝ የሚያሳዩ ጥቂት መረጃዎች ሲኖሩ፣ ምግቦቹ ውስጥ በሚገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ስብ፣ ጨው እና ስኳር መሆኑንም የሚያመለክቱ ጥናቶች ይፋ ሆነዋል።

"ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮች"

በ'አሜሪካን ጆርናል ኦፍ ፕሪቬንቲቭ ሜዲሲን' ላይ የታተመ ጥናት ከዚህ በፊት በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና በርካታ ንጥረ ነገሮች የገቡባቸው ምግቦች በሞት ላይ ያላቸውን ተጽእኖ ለመገምገም የተደረጉ ጥናቶችን ተመልክቷል።

ጥናቱ በፋብሪካ ተቀነባብሮ የታሸገ ምግብ ያለጊዜው ለሚከሰት ለሞት እንደሚዳርግ በእርግጠኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

ምክንያቱም አንድ ሰው የሚጠቀመው በፋብሪካ የተቀነባበረ እና የታሸገ ምግብ መጠን ከአጠቃላይ አመጋገቡ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ደረጃው፣ ከሰፊው የአኗኗር ዘይቤ እና ከሀብት ደረጃው ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ነው።

ጥናቱ በሰዎች አመጋገብ ላይ በስምንት አገራት የተደረጉ ጥናቶችን እና የሞት መረጃን ተመልክቷል።

እነዚህ ስምንት አገራት አውስትራሊያ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ሜክሲኮ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን የያዙ ናቸው።

በፋብሪካ የተቀነባበረ እና የተሻገ ምግብን በከፍተኛ ደረጃ በሚጠቀሙት ዩኬ እና አሜሪካ ያለ ጊዜው ከተከሰተ 14 በመቶ ሞት ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ይገምታል።

እንደ ኮሎምቢያ እና ብራዚል ባሉ አገራት ደግሞ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን የመጠቀም ልምድ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ፣ እነዚህ ምግቦች 4 በመቶ ከሚሆኑት ያለ ጊዜው ከሚከሰት ሞት ጋር የተገናኙ መሆናቸውን ገምቷል።

ጥናቱን በበላይነት ያካሄዱት ብራዚላዊ ዶ/ር ኤድዋርዶ ኒልሰን በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና የታሸጉ ምግቦች በጤና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ይላሉ።

"በኢንዱስትሪ ሂደት ወቅት በምግቦቹ ላይ በሚደረጉ ለውጦች እና የሚጨመሩ ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮች ማለትም ማቅለሚያዎች፣ አርቲፊሻል ጣዕሞች፣ ጣፋጮች፣ለማዋሀድ የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች እና ሌሎች ብዙ የሚገቡባቸው እና ማቀነባበር የሚያግዙ ኬሚካሎች ምክንያት ናቸው።"

ጥናቱን ያደረጉት ባለሙያዎቸ እንደ አውሮፓውያኑ 2018 በአሜሪካ ውስጥ በፋብሪካ በተቀነባበረ እና በታሸገ ምግብ ምክንያት124,000 ሰዎች ያለ እድሜያቸው ሲሞቱ በዩኬ ደግሞ 18,000 ያህል መሞታቸው ይታመናል።

ጥናቱ መንግሥታት ሰዎች እነዚህን ምግቦች እንዲቀንሱ የሚሰጡትን የአመጋገብ ምክር ማሻሻል አለባቸው ብሏል።

ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ቡድን በፋብሪካ የሚቀነባበሩ ምግቦች እና በጤና መጓደል መካከል ጠንካራ ግንኙነት ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ጠንካራ ማስረጃ የለም ብሏል።

በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና የታሸጉ ምግቦች የትኞቹ ናቸው?

በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና የታሸጉ ምግቦች ላይ ሁሉም ሰው የሚስማማበት አንድ ብያኔ የለም። ነገር ግን የዓለም ሥነ ምግብ ባለሙያዎች በሚጠቀሙበት ምደባ መሰረት

  • ኬኮች፣ ብስኩቶች
  • ክሪስፕ
  • ከሱፐር ማርኬት የሚገዙ ዳቦዎች
  • ሶሴጅ፣በርገሮች እና ቋሊማዎች
  • ኢንስታንት ሱፕ፣ ኑድልስ እና ጣፋጮች፣
  • ቺክን ናጌትስ
  • ፊሽ ፊንገር
  • የፍራፍሬ ጣዕም የገባባቸው እርጎዎች እና መጠጦች
  • ማርጋሪን እና ሌሎች ዳቦ ላይ የሚቀቡ
  • የሕጻናት ወተቶች

መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች

በጥናቱ ውስጥ የተጠቀሱት ቁጥሮች በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና የታሸጉ ምግቦች በሰዎች ጤና ላይ ያላቸውን ተፅእኖ በመመልከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

ኦፕን ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ስታቲስቲክስ ፕሮፌሰር የሆነው ኬቨን ማክኮንዌይ ጥናቱ ብዙ የሂሳብ ቀመሮችን በመጠቀሙ፣ ግኝቶቹ ምን ማለት እንደሆኑ እንዲጠይቅ አድርገውታል።

"አሁንም በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች ለጤና ጎጂ መሆናቸው ላይ ጥርት ያለ ምላሽ የለም ወይንም የትኛውም በፋብሪካ የተቀነባበረ ምርት ካለ እድሜ ሞት ጋር አንደሚያያዝ የተቀመጠ ነገር የለም። በዚህም የተነሳ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን በተለያየ መጠን በሚወስዱ ሰዎች መካከል ያለው የሞት ልዩነት በምግቦቹ ፍጆታ ልዩነት የተከሰተ ስለመሆኑ እርግጠኛ ለመሆን አይቻልም ማለት ነው።

"ከእንደዚህ ዓይነት ጥናት በትክክል ለግለሰቦቹ ሞት ምን መንስኤ እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም።"

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የአመጋገብ እና ውፍረት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኔሪስ አስትበሪ በምርምሩ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን ይስማማሉ።

ከዚህ በፊት በከፍተኛ ኃይል ሰጪ፣ ስብ እና ስኳር የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ ለስኳር በሽታ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ለልብ ህመም እና ለካንሰር በማጋለጥ ሰዎች ያለ እድሜያቸው እንዲሞቱ እንደሚያደርግ ይታወቃል ይላሉ።

"ብዙዎቹ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች በእነዚህ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ናቸው" ካሉ በኋላ እስከ አሁን የተደረጉ ጥናቶች በፋብሪካ የሚቀነባበሩ ምግቦች ቀጥተኛ ተጽእኖ "በኃይል የተሞሉ እና ከፍተኛ መጠን ያለው ስብ እና ስኳር የያዙ ምግቦች" ከማለት ባለፈ ምክንያት መሆናቸውን ምንም ሊያረጋግጡ አልቻሉም ብለዋል።

ይህ ዓይነቱ ጥናት በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን መመገብ ጎጂ መሆኑን ማረጋገጥ አይችልም ሲሉ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ስቴፈን በርገስ ይናገራሉ።

አምራቾችን የሚወክለው የምግብ እና መጠጦች ፌዴሬሽን ግን የምግብ አምራቾች የሚጠቀሙባቸው ንጥረ ነገሮች በሙሉ በምግብ ደረጃዎች ኤጀንሲ የፀደቁ በመሆናቸው ለመመገብ እና ለመጠጣት ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው ሲል ይከራከራል።