በለንደን ባቡር ውስጥ በተፈፀመ የስለት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ለሕይወት የሚያሰጋ ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው

ፖሊስ እና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ምላሽ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

በለንደን ካምብሪጅሸር በተባለ አካባቢ ባቡር ውስጥ በተፈፀመ የስለት ጥቃት 10 ሰዎች ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፤ ዘጠኙ ለሕይወት የሚያሰጋ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ፖሊስ ቅዳሜ ምሽት ከተፈፀመው ጥቃት ጋር ተያይዞ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ጉዳት ስለደረሰባቸው እና በቁጥጥር ሥር ስለዋሉ ሰዎች ማንነትም ሆነ የጥቃቱ መንስዔ ምን ሊሆን ይችላል በሚለው ዙሪያ አስተያየት አልሰጡም።

የብሪታኒያ ትራንስፖርት ፖሊስ "ትልቅ ክስተት" መከሰቱን እና ከሽብርተኛ መከላከል መኮንኖች ጋር በመሆን ጥቃቱን እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።

ፖሊስ የጅምላ ጥቃቱ የአደጋ ጥሪ ሲደርሰው እንደ "ሽብር ጥቃት" አድርጎ የተመለከተው ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ይህን ብያኔውን ሰርዟል።

የአካባቢው የፖሊስ አዛዥ ክሪስ ኬሲ የስለቱን ጥቃት "አስደንጋጭ ክስተት" በማለት ከዚህ ባሻገር በዝርዝር ምንም ማለት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

"ከዚህ በተጨማሪ ማረጋገጫ ከመስጠታችን በፊት ጊዜ ሊወስድ ይችላል" በማለት ትዕግሥት እና ትብብር እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በባቡሩ ውስጥ የነበሩ የዓይን እማኞች ጥቃቱ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ መቆየቱን ተናግረው ነገር ግን "የሕይወት ዘመን ያህል" የቆየ እንደመሰላቸው ገልፀዋል።

ሌሎች መንገደኞችም ባቡሩ ውስጥ የቆሰሉ ሰዎች ቢላዋ ከያዘ ሰው ሲሮጡ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በኤክስ ገፃቸው "በሃንቲግዶን አቅራቢያ ባቡር ላይ የተፈፀመው አስደንጋጭ አደጋ በጣም የሚያሳስብ ነው።

"ሃሳቤ ከተጎዱት ጋር ነው፤ እና የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ለሰጡት ምላሽ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ" ብለዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናትም በተመሳሳይ ጥቃቱን አስደንጋጭ እና በጣም አሳሳቢ ብለው የገለፁት ሲሆን ሀሳባቸው ከተጎጂዎች እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሆነ ገልፀዋል።

የብሪታኒያ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሳባና መሐሙድ በጥቃቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀው፤ ሰዎች አላስፈላጊ አስተያየቶችን እና ግምቶችን ከመስጠት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የአገሪቱ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ የሆኑር ኬሚ ባዴኖቺ "ፍፁም አስከፊ ጥቃት" ሲሉ የገለፁትን ክስተት አውግዘው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ጨምሮ በጥቃቱ ለተጎዱት ሁሉ በሀሳብ ከጎናቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።